90 ሰዎችን ያስጠለለው ባለአራት መኝታው የጋዛ መኖሪያ ቤት

ኢብራሂም አል አጋ እና ቤተሰቡ

የፎቶው ባለመብት, Ibrahim AlAagha

ኢብራሂም አል አጋ እና ሚስቱ ሐሚዳ ጋዛ ሽርሽር ላይ ሳሉ ነው እስራኤል የአየር ጥቃት የጀመረችው።

የአየርላንድ ዜግነት ያላቸው ጥንዶቹ ደብሊን የተወለዱ ሦስት ልጆቻቸውን ይዘው ወደ ጋዛ ያቀኑት ልጆቻቸው ቋንቋ እና ባሕላቸውን እንዳይረሱ በሚል ነው።

ነገር ግን እንደጠበቁት ከዘመድ አዝማድ ቁጭ ብሎ መጫወት ሳይሆን ቤተሰቡን ይዞ ከአየር ጥቃት እና ከፍንዳታ መሸሽ ዕጣ ፈንታቸው ሆነ።

“ፍንዳታ በፍንዳታ ነው በቃ። በቦምብ ላይ ቦምብ ሲፈነዳ ነው የሰነበተው። ቤታችን ሲንቀጠቀጥ ነበር” ይላል ኢብራሂም።

መስከረም 26/2016 ዓ.ም. የሐማስ ታጣቂዎች በፈፀሙት ጥቃት አስራኤል ውስጥ ከ1400 ሰዎች በላይ ተገድለዋል።

ይህንን ተከትሎ እስራኤል በጋዛ ላይ መልሶ ማጥቃት እያካሄድች ነው። ጋዛ ውስጥ የተገደሉ ሰዎች ቁጥር4300 በላይ ሆኗል።

እስራኤል እጀምረዋለሁ ካለችው የእግረኛ ወረራ በፊት 1.1 ሚሊዮን የሚሆኑ የሰሜናዊ ጋዛ ነዋሪዎች ወደ ደቡባዊ አቅጣጫ እንዲያቀኑ ትዕዛዝ ሰጥታለች።

ከዚህ ትዕዛዝ በኋላ ኢብራሂም እና ቤተሰቡ ጋዛ ከነበረው አፓርትመንታቸው ጓዛቸውን ሸክፈው ወጥተዋል።

ኢብራሂም ወላጆቹ ወደሚኖሩባት ደቡባዊቷ የኻን ዩኒስ ከተማ በማቅናት ተጠልሏል።

በርካታ ሰዎች ወደ ደቡብ ሲያቀኑ ዘመድ እና ጓደኛ የሌላቸው ሰዎች መጠለያ ስሌላቸው ይደጋገፋሉ።

አሁን የኢብራሂም ወላጆች ቤት 90 ሰዎች ተጠልለውበታል።

ኢብራሂም ወላጆቼ ወገኖቻቸው ላይ በፍፁም አይጨክኑም ይላል።

አራት መኝታ ክፍል ያላት ቤት 90 ሰው አቅፋለች። በአንድ ፍራሽ ላይ ሁለት ሰዎች ሆነው በፈረቃ ይተኛሉ።

ኢንጂነሩ ኢብራሂም ከቤቱ መስኮት ላይ መስታወቶችን ያነሳል። ይህን የሚያደርገው እንዳው ቤቱ በድሮን ጥቃት ቢደርስበት የሚደርሰውን አደጋ ለመቀነስ ነው።

ቢሆንም ምግብ፣ ውሃ እና የኤሌክትሪክ ኃይል በተነፈገችው ጋዛ ሕይወት ከቀን ወደ ቀን እየከበደ መጥቷል።

“ንጋት ተነስተን ማታ እስክንተኛ ድረስ ዓላማችን ሕይወታችንን ማትረፍ ነው” ይላል።

የተወሰኑ ሰዎች ወጣ ብለው የታሸገ ምግብ ፍለጋ ተዘዋውረው ይመለሳሉ። ምንም እንኳ እንጨት ለቅመው፤ ያለውን ዱቄት አቡክተው ዳቦ መጋገር ቢችሉም ቋት ውስጥ ያለው እህል አንድ ሰው በቀን ከአንድ ጊዜ በላይ እንዲመገብ የሚፈቅድ አይደለም።

በተለይ ደግሞ ለ30 ሕፃናት ይህ ሕይወት እጅግ የከበደ ነው። ከ30ዎቹ አስሩ ዕድሜያቸው ከአምስት በታች ነው።

“ሁሌም ምግብ እና ውሃ ሲጠይቁን የምንችለውን ለማድረግ እንሞክራለን። በጣም ከብዶናል።

“እኛ ትላልቆቹስ ችግሩን እንችለዋለን። ቢርበንም እንወጣዋለን። ነገር ግን ሕፃናት ምግብ ሲጠይቁን እምቢ ልንላቸው አንችልም።”

ኢብራሂም የሰዎች ጤንነት ያሳስበዋል። ከመካከላቸው ነፍሰ-ጡሮች እና ዕድሜያቸው የገፋ ጤናቸው የተዳከመ ሰዎች አሉ።

ከሚያሳስበው ነገር አንዱ የመድኃኒት እጥረት ነው።

አንድ ሰው ድንገት በጠና ቢታመም ወደ ሆስፒታል ይዞ መሮጥ የሚታሰብ አይደለም።

የኢብራሂም አል አጋ ቤተሰቦች

የፎቶው ባለመብት, Ibrahim AlAagha

“ልጄ እጅግ ተጨንቋል”

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የኢብራሂም ልጆችም ቢሆኑ በክስተቱ እጅግ ተጎድተዋል። ኦማር እና አይሊን የሦስት እና የአራት ዓመት ልጆች ናቸው። የአየር ጥቃት አሊያም ፍንዳታ በሰሙ ቁጥር ይሳቀቃሉ።

ኢብራሂም እና ሚስቱ ሐሚዳ ልጆቻቸውን በማጫወት ሊያረሳሷቸው ይፈልጋሉ።

ሕፃናቱ ማታ ማታ ፍንዳታ ሲሰሙ ጭልጥ ብለው ከተኙበት ተነስተው ቤተሰቦቻቸውን ፍለጋ ይሯሯጣሉ። የስምንት ዓመቱ ሳሚ ድሮን ይመታኛል የሚል ስጋት አለው።

“እየሆነ ያለው ነገር ይገባዋል። ምን ዓይነት ጭንቀት ውስጥ እንዳለን ስለሚረዳ እሱም ተጨንቋል።”

በጋዛ ያለው ሁኔታ እየከፋ መጥቷል። ኢብራሂም እና ቤሰተቡ ወደ ደብሊን ለመመለስ እየሞከሩ ነው። ይህ እንዲሆን የአየርላንድ ኤምባሲን ሲያናግሩ ቆይተዋል።

ባለፈው ቅዳሜ “የመጣው ይምጣ” በማለት ከኻን ዩኒስ ተነስተው ከግብፅ ወደ ምትዋሰነው ራፋህ አቅንተው ነበር። ራፋህ ከጋዛ ሰርጥ ከሚያስወጡ ሁለት የየብስ አማራጮች አንዷ ናት።

በሺዎቹ የሚቆጠሩ ሰዎች ጋዛን ሸሽተው ለመውጣት ራፋህ ተሰባስበዋል።

ኢብራሂም ራፋህ ሲደርስ ከኤምባሲው ወደኋላ ተመለሱ የሚል መልዕክት ይመጣለታል።

በወቅቱ ድንበሩ ተዘግቶ ነበረ።

ነገር ግን ምናልባት ድንበር ቢከፈት ተመልሶ ለመሄድ የሚያስችል ነዳጅ የለውም። ነዳጅ ቢያገኝ እንኳ ከኤምባሲው ጋር የሚገናኝበት ኔትዎርክ ሊቋረጥ ይችላል።

“ተስፋ እየቆረጥኩ ነው” ይላል ኢብራሂም።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ቤሰተቡ ጭላንጭል ተስፋ ይዞ ይጠብቃል።

ባለፈው ማክሰኞ የአል-አህሊ አራብ ሆስፒታል በሚሳኤል ተመትቶ በመቶዎች የሚቆጠሩ ከሞቱ በኋላ የኻን ዩኒስ ነዋሪዎች እንቅልፍ አጥተዋል።

“ለሕይወታችን ሰግተናል። ማንኛውም ሰው፤ በማንኛውም ሰዓት ዒላማ ሊሆን ይችላል። ነገሮች ከጊዜ ጊዜ እየከፉ ነው።”