እስራኤል አስካሁን ወደ ጋዛ ዘልቃ እንዳትገባ ያገዳት ምንድን ነው? አራት ቁልፍ ምክንያቶች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
እስራኤል ቆርጣለች። ሐማስን ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ሳላጠፋ እንቅልፍ አይወስደኝም ብላለች።
ለ300 ሺህ ተጠባባቂ ጦር “ምታ ነጋሪት፣ ክተት ሠራዊት” ብላለች።
ከጋዛ የሚጎራበተው የእስራኤል ድንበር እርሻ ቦታው ሁሉ የታንክ ጋጋታ ሞልቶታል።
ተወንጫፊ ሮኬቶች እና ሌሎች ጦር መሣሪያዎች ሁሉም አፈሙዛቸው ወደ ጋዛ ከፍተዋል።
የእስራኤል አየር ኃይል እና ባሕር ኃይል በእያንዳንዷ ደቂቃ ጋዛን እየደበደበ ነው። ሐማስ እና አጋሩ ኢስላሚክ ጂሃድ ይገኙበታል የሚባሉ ዒላማዎችን ቀን ተሌት ያለ እረፍት እያጠቁ ነው።
በዚህ ሂደት ጥቂት የሐማስ ኮማንደሮች እና በርካታ ንጹሐን ሙት እና ቁስለኛ ሆነዋል፤ እየሆኑም ነው።
በማክሰኞው የሆስፒታል ጥቃት ሁለቱም ወገኖች እርስ በእርስ እየተወነጃጀሉ ነው። ወደ 500 ሰዎች የተገደሉበት ይህ ጥቃት በመላው አረብ አገራት ከፍተኛ ቁጣ ቀስቅሷል።
አሁን ጥያቄው እስራኤል ወደ ጋዛ ሰተት ብዬ እገባለሁ ስትል የዛተችው መቼ ነው ተግባራዊ የሚሆነው? የሚለው ነው።
መቼ የሚለው ጥያቄ በሚከተሉት አራት ቁልፍ ሁኔታዎች ይወሰናል።
1-የባይደን ማሳሰቢያ
ባይደን ወደ ቴል አቪቭ የሄዱት ተጣድፈው ነው። ጥድፊያው የመጣው ኔታንያሁን አንድ ነገር ለማሳሰብ ነው ይላሉ ተንታኞች። እግረኛ ጦሯን ወደ ጋዛ ለማስገባት እንዳትቸኩል።
ዋይት ሐውስ ነገሮች እየሄዱበት ያለው ሁኔታ አሳስቧታል። በተለይ ሁለት ነገሮች። አንዱ ጋዛ ውስጥ ያለው የሰብአዊ ሁኔታ እየከፋ መሄድ ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ግጭቱ ወደ አካባቢው አገራት እንዳይዛመት መስጋታቸው ነው።
ባይደን በግልጽ እስራኤል ወደ ጋዛ እንዳትገባ አሳስበዋል። እስራኤል ከጋዛ የወጣቸው በ2005 ነበር። ተመልሳ ከገባች “ቀይ ስህተት” ይሆናል ብለዋል።
ባይደን በይፋ ለእሰራኤል ሁሉን አቀፍ የማያወላዳ ድጋፍ እያሳዩ ነው። ከመድረክ ጀርባ ግን የኔታንያሁን ቀኝ አክራሪ መንግሥት ነገሮችን ተረጋግቶ እንዲመለከት እያሳሰቡ ነው።
እስራኤል ጨክና ጋዛ ከገባችም መቼ ገብታ መቼ እንደምትወጣ ማወቅ ትፈልጋለች።
የባይደን ጉብኝት አል አህሊ አረብ ሆስፒታል ላይ በደረሰው አሰቃቂ ጥቃት መጥፎ ድባብ አጥልቶበታል። ይሁንና ባይደን በይፋ ጥቃቱ የተፈጸመው ከእስራኤል አይደለም ብለው ለቴላቪቭ ድጋፍ ሰጥተዋል።
2-ኢራን ብታመርስ
እስራኤል ወደ ጋዛ እንዳትገባ አንድ ስጋት የሆነችው ኢራን ናት። ኢራን ግጭቱ ከተጀመረ ወዲህ እስራኤል በንጹሐን ላይ የምትፈጽመውን ጥቃት ቆሜ አላይም ብላ ዝታለች። ይህ ዛቻዋ ደግሞ ዛቻ ብቻ ሆኖ ባይቀርስ? የሚለው ምዕራቡን ማስጨነቁ አልቀረም።
ኢራን በገንዘብም፣ በትጥቅም፣ በስንቅም ሒዝቦላህን እና ሐማስን ታግዛለች። ሒዝቦላህ በእስራኤል ሰሜናዊ ድንበር ቨቅርብ ርቀት ላይ ነው ያለው።
በ2006 (እአአ) እስራኤል ከሒዝቦላህ ጋር ባደረገችው ጦርነት ተፈትናበታለች። ሒዝቦላህ በደንብ በተጠኑ ዕቅዶች የእስራኤልን ታንኮች አውድሟል።
ከሁለቱም ወገን በርካታ ወታደሮች እና ንጹሐን ተገድለዋል።
ሒዝቦላህ አሁን በሙሉ ኃይሉ ወደ ጦርነት አልገባም። ከ2006 ወዲህ ደግሞ ራሱን አደርጅቷል። ወደ 15ሺህ ሮኬት እና ሚሳኤል አጠራቅሟል። ብዙዎቹ ደግሞ ረዥም ርቀት መወንጨፍ የሚችሉ እና ዒላማቸውን የሚመቱ ናቸው።
ይህ እስራኤልን ቆም ብላ እንድታስብ ሳያደርግ አልቀረም።
እስራኤል ወደ ጋዛ ብትገባ እና ሒዝቦላህ በሰሜን ድንበር ጦርነት ቢከፍት በሁለት ድንበሮች ጦርነት ሊገጥማት ይሆናል እስራኤል።
ይሁንና የአሜሪካ አውሮፕላን ተሸካሚ ግዙፍ ሁለት መርከቦች ወደ ሜዲትራኒያን ባሕር ተጠግተው ባለበት ሁኔታ ወደ ጦርነት ይገባል ተብሎ አይታመንም።
ኢራን ይህን ጦርነት ከተዋጋች የምትዋጋው በሒዝቦላህ በኩል ነው ተብሎ ይጠበቃል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
3-የሰብአዊ እርዳታ ምስቅልቅል
እስራኤል ሐማስን ጨርሼ አጠፋለሁ ብላ ስትነሳ በጋዛ ያለውን የሰብአዊ እርዳታ ምስቅልቅል የተረዳችው አይመስልም።
ፍልስጥኤማውያን ሰላማዊ ዜጎች በከፍተኛ ቁጥር እየሞቱ እና የሰብአዊ ጥፋቱ ዓለምን እያነጋገረ መሆኑ ለእስራኤል ወደ ጋዛ ዘሎ አለመግባት አንድ ምክንያት ሆኖ ይጠቀሳል።
በሐማስ መብረቃዊ ጥቃት እና የሰላማዊ ሰዎች ግድያ ለእስራኤል ሐዘኔታ ያሳየው በርካታ የዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ፣ እስራኤል በጋዛ ንጹሐን ላይ ባደረሰችው እና እያደረሰች ባለው ሰብአዊ ቀውስ ፊቱን እያዞረባት ነው።
እስራኤል ጋዛ ከገባች ይህ ምስቅልቅል ይከፋል። ሰላማዊ ዜጎችም ስቃያቸው ይበዛል።
4-የእስራኤል የስለላ አቅም ጥያቄ ውስጥ መግባት
ታላቅ ስም የገነባው የእስራኤል የስለላ አቅም የሐማስን ጥቃት ተከትሎ ጥያቄ ውስጥ ወድቋል።
ሺን ቤት የሚባለው የአገር ውስጥ ደኅንነት መሥሪያ ቤት ሐማስ ጥቃት ሊሰነዝር እንደሚችል ቀድሞ ሊደርስበት አለመቻሉ በአያሌው አስተችቶታል።
ሺን ቤት በጋዛ ውስጥ በርካታ ሰላዮች እና ጥቆማ የሚሰጡ ወኪሎች እንዳሉት ነበር የሚታወቀው።
ሺን ቤት በጋዛ ውስጥ ነዋሪዎች የሚንሾኳሸኩትን ሳይቀር ይሰማል ነበር የሚባለው።
በጋዛ ሐማስ እና ኢስላሚክ ጂሃድ የሚለዋወጡትን የመልዕክት ቅጂ ያገኛል ነበር የሚባለው። ድምጽ ይጠልፋል አንድም አይቀረውም ነበር የሚባለው።
ሐማስ ጥቃት የፈጸመ ጊዜ የሆነው ግን ብዙዎችን አስደንግጧል። ይህ ለእስራኤል ጠዮም ኪፑር (በ1973 እአአ) ከተባለው የአርብ እስራኤል ጦርነት ወዲህ ትልቁ የደኅንነት እና ስለላ ውደቀት ሆኖ ተመዝግቧል።
አሁን የእስራኤል ስለላ መረብ ታጋቾቹ የት እንደሚገኙ እና የሐማስ መሪዎች የት እንደተደበቁ ለጦር ሠራዊቱ መረጃ በፍጥነት እያቀረበ እንደሆነ እየተነገረ ነው።
ይሁንና በጋዛ እግረኛ ሠራዊት ይዞ ለመግባት ከፍተኛ መጠን ያለው የውስጥ መረጃ መሰብሰብ ይፈልጋል። አለበለዚያ በእስራኤል ወታደሮች ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሊደርስ ይችላል።
አንድም የእስራኤልን ሐማስን ለማደን ወደ ጋዛ ዘው ብሎ መግባቷን ያዘገየው ይህ መረጃን ሰብስቦ የማጠናቀር ሂደት በመዘግየቱ ነው የሚሉ አሉ።












