ፀረ - ሴማዊነት ምንድን ነው? ፀረ - ጽዮናዊነትስ?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ለሁለት ሳምንታት ከቀጠለው የእስራኤል-ጋዛ ግጭት ጋር ተያይዞ ፀረ - ሴማዊነት፣ ፀረ - ጽዮናዊነት የሚሉ እሳቤዎች መነጋገሪያ ሆነዋል።
በተለይም ለፍልስጥኤም የሚደረጉ ዓለም አቀፍ ድጋፎች በተበራከቱበት እና የእስራኤልን መንግሥት የሚቃወሙ ድምጾች መሰማትን ተከትሎ እነዚህ ሃሳቦችም እየተንሸራሸሩ ይገኛሉ።
እነዚህ እሳቤዎች ምን ማለት ናቸው?
- ፀረ - ሴማዊነት ማለት በአይሁዶች ላይ እንደ ሕዝብ ጭፍን ጥላቻን ወይም የተሳሳተ ዕይታ ማለት ሲሆን፣ ዘመናትን አስቆጥሯል።
- ፀረ - ጽዮናዊነት በበኩሉ የእስራኤልን መንግሥት ኅልውና መቃወም ተብሎ ሊገለጽ ይችላል።
ፀረ - ሴማዊነት ምንድን ነው?
አይሁዳውያን ለዘመናት፣ ጥላቻ፣ መሳደድ እና ጭቆናን አስተናግደዋል።
በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ስድስት ሚሊዮን አይሁዳውያን በናዚዎች በጅምላ ተጨፍጭፈዋል።
የዘመናችን ፀረ - ሴማዊነትስ እንዴት ይገለጻል? በርካታ መልኮች ሊኖሩት ይችላሉ።
አይሁዳውያን የዓለም አቀፉን የፋይናንስ ሥርዓት እና የመገናኛ ብዙኃንን ተቆጣጥረዋል የሚሉ የሴራ ጽንሰ ሃሳቦች፣ ወይም በምኩራቦች ላይ የሚሰነዘሩ ጥቃቶች፣ በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ ያሉ የጥላቻ ትርክቶች እና ንግግሮችን እንዲሁም ሌሎችንም ያጠቃልላል።
ሆኖም ፀረ - ሴማዊነት የሚለው እሳቤ ሁሉንም አካላት አያግባባም። አንዳንዶች የእስራኤልን መንግሥት መቃወም እንደ ፀረ - ሴማዊነት ከማየታቸው ጋር ተያይዞ እሳቤው መወዛገቢያ ሆኖ ቀጥሏል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ጽዮናዊነት ምንድን ነው?
ጽዮናዊነት በአውሮፓ በ19ኛው ክፍለ ዘመን የተጀመረ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ነው።
ፍልስጥኤም በምትባለውም ምድር የአይሁድ አገርን መመሥረት ዋነኛ ግቡ ነው።
ይህ እንቅስቃሴ የአይሁዳውያን የጥንት ርስት ናት የሚሏትን የአይሁዳውን አገር የሆነች እስራኤል ፍልስጥኤም ተብሎ በሚታወቀው መሬት የመመሥረት ፍላጎት የነበረው ነው።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትም ፍልስጥኤም ለሁለት ተከፍላ የአይሁዶች እና የአረቦች የተናጠል አገራት አንዲመሠረቱ ሃሳብ አቀረበ።
በአውሮፓውያኑ 1948ም እስራኤል በመካከለኛው ምሥራቅ ውስጥ በአገርነት መመሥረቷ ታወጀ።
በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ፍልስጥኤማውያን ከቀያቸው እና ከቤታቸው ተፈናቀሉ። ከዚያም በኋላ በ1967 (እአአ) የተደረገውን የስድስቱን ቀን ጦርነት ተከትሎ የፍልስጥኤም ግዛቶች የሚባሉትን ዌስት ባንክን እና ምሥራቅ ኢየሩሳሌምን እስራኤል በኃይል ተቆጣጥራ ትገኛለች።
ባለፉት አምስት አስርት ዓመታትም በነዚህ ግዛቶች የአይሁዶች የሰፈራ መንደሮችን አቋቁማለች። 700 ሺህ የሚቆጠሩ አይሁዳውያን በእነዚህ ስፍራዎች አስፍራለች።
የተባበሩት መንግሥታትን ጨምሮ የተለያዩ ተቋማት እስራኤል በቁጥጥሯ ስር ባሉ ግዛቶች የሰፈራ መንደሮችን ማቋቋሟ ዓለም አቀፍ ሕግን የሚጻረር እና ሕገወጥ ነው ሲሉ ይጠሩታል።
የእስራኤል መንግሥት ምሥረታ በፍልስጥኤም የሚኖሩ አረቦችን መብት የነፈገ መሆኑን በመጥቀስ ፍልስጥኤማውያን እንዲሁም ሌሎች አረቦች ይቃወሙታል።
የጽዮናዊነትን እንቅስቃሴ የሚያቀነቅኑ አካላት እስራኤል እንደ አይሁድ ግዛትነቷ ጥበቃ ሊደረግላት እንዲሁም ልትስፋፋ ይገባል ብለው ያምናሉ።
አንዳንድ ጽዮናውያን እስራኤል ካላት ግዛት በተጨማሪ ሌሎች ግዛቶችንም የመቆጣጠር መብት አላት ብለው የሚከራከሩ ሲሆን፣ ሌሎች በዚህ ሃሳብ አይስማሙም።
አብዛኛው አይሁዳውያን ጽዮናውያን ቢሆኑም፣ ጥቂቶች በፖለቲካዊ እና በሃይማኖታዊ ምክንያቶች ጽንሰ ሃሳቡን ይቃወማሉ። አይሁዳዊ ያልሆኑ ሰዎች ጽዮናዊነትንም ማቀንቀን ይችላሉ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ፀረ - ጽዮናዊነት እንዴት ይገለጻል?
ስለ ጽዮናዊነት እንቅስቃሴ ካብራራን የጽዮናዊነት እሳቤን መቃወም ምን ማለት እንደሆነ እንመልከት።
ፀረ - ጽዮናዊነትን ጠቅለል አድርገን ስናየው የእስራኤልን መንግሥት መቃወም ተብሎ ሊገለጽ ይችላል።
የእስራኤል መንግሥት ዌስት ባንክን በኃይል መቆጣጠሩ ወይም ያደረገውን ወረራ የሚቃወሙ የጽዮናውያን ተቺዎች አሉ።
እነዚህ ተቺዎች የእስራኤል መንግሥት ፖሊሲዎችን የሚቃወሙ ሲሆን፣ ከእነዚህም ውስጥ እስራኤል በዌስት ባንክ እና አካባቢው የገነባችው የመለያያ አጥር ተጠቃሽ ነው።
እስራኤል ይሄንን ግንብ የገነባችው ከፍልስጥኤም አጥቂዎች ራሷን ለመከላከል ለደኅንነት ነው ብትልም፣ ፖሊሲዋን የሚቃወሙ እና የፍልስጥኤም ደጋፊዎች ተጨማሪ መሬት ለመውረር እና ለአይሁዳውያን የሰፈራ መንደር ለመገንባት ነው ይላሉ።
በአንዳንድ ሁኔታዎች እስራኤልን አጥብቀው የሚያወግዙ አካላት፣ ትችቱ ከፀረ - ሴማዊነት ጋር ይያያዝ ወይም ፖሊሲውን እንደሆነ ለማወቅ አስቸጋሪ ነው።
ፀረ - ጽዮናዊነት ወይም የአይሁድን መንግሥት አለመቀበል የዘመናችን ፀረ - ሴማዊነት መገለጫ ነው የሚሉ አልታጡም።
ዓለም አቀፉ የሆሎኮስት መታሰቢያም ከእስራኤል ጋር የሚያያዙ አንዳንድ ውንጀላዎች እና ክሶች ፀረ - ሴማዊነት ናቸው ሲል ፈርጇቸዋል።
ይህንን ፍረጃ የማይቀበሉ ሰዎች የእስራኤል ደጋፊዎች በእስራኤል ላይ የሚሰነዘረውን ምክንያታዊ ትችት ዝም ለማሰኘትም እንደ መሳሪያ ይጠቀሙበታል ይላሉ።
እስራኤል የምታደርገውን መቃወም “ዘረኝነት” አይደለም ይላሉ።
አንዳንዶች “ጽዮናዊነት” የአይሁድ ሕዝብን ለመቃወም ሽፋን ነው ሲሉ፣ ሌሎች ደግሞ የእስራኤል መንግሥት እና ደጋፊዎች ሆን ብለው ፀረ - ጽዮናዊነት እና ፀረ - ሴማዊነትን በማምታታት ትችት እንዳይሰነዘርባቸው እየሞከሩ እንደሆነም ይወቅሳሉ።












