የኔዘርላንድስ ንጉሥ አገራቸው በባሪያ ንግድ ላይ ለነበራት ተሳትፎ ይቅርታ ጠየቁ

ንጉሥ ዊሌም-አሌክሳንደር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ንጉሥ ዊሌም-አሌክሳንደር

የኔዘርላንድስ ንጉሥ ዊሌም-አሌክሳንደር አገራቸው በባሪያ ንግድ ላይ ለነበራት ተሳትፎ ይፋዊ ይቅርታቸውን አቀረቡ።

ንጉሥ ዊሌም-አሌክሳንደር ትናንት በኔዘርላንድ የባሪያ ንግድ የቆመበት 160ኛ ዓመት ሲዘከር ባደረጉት ንግግር የባሪያ ንግድን “እጅግ አስከፊ” ሲሉ ገልጸውታል።

ሆላንድ በ17ኛው ክፍለ ዘመን በዓለማችን በርካታ አካባቢዎችን በመቆጣጠር ቀዳሚ ከሚባሉ ቅኝ ገዢዎች መካከል አንዷ የነበረች ሲሆን 600ሺህ ያክል ሰዎችን በባሪያ ንግድ ስንሰለት ውስጥ ስለማዘዋወሯ ይገመታል።

ንጉሡ ይህን አስከፊ ተግባር የወቅቱ ንጉሥውያን ቤተሰቦች ለማስቆም ምንም አላደረጉም ብለዋል።

በቅርብ የተካሄደ አንድ ጥናት ከ1675 እስከ 1770 ባሉት ዓመታት የደች ንጉሥውያን ቤተሰብ አባላት ከባሪያ ንግድ ከግማሽ ሚሊዮን ዶላር በላይ ማግኘታቸውን አሳይቷል።

ንጉሥ ዊሌም-አሌክሳንድር ነገሥታቱ እና የሃውስ ኦፍ ኦሬንጅ መሪዎች የባሪያ ንግድን ለማስቆም ምንም አይነት እርምጃ አልወሰዱም ብለዋል።

“ዛሬ እዚህ ፊት ለፊታችሁ የቆምኩት እንደ ንጉሥሳችሁ እና መንግሥታችሁ ነው። ዛሬ እኔው ራሴ ይቅርታ ጠይቃለሁ። ዛሬ ግልጽ የሆነ እርምጃ መውሰድ ስላልተቻለ ለይቅርታ ቆሜያለሁ” ብለዋል።

ንጉሡ በንግግራቸው ሁሉንም የኔዘርላንድስ ዜጎች መወከል ባልችልም አብዛኛው የደች ዜጎች ግን የቆዳ ቀልም ወይም የሰዎችን የኋላ ማንነት ከግምት ሳያስገቡ ሁሉም ሰው እኩል እንደሆነ ያምናሉ ብለዋል።

ንጉሡ አክለውም ጥፋቱን ካመንን እና ይቅርታችንን ካቀረብን የደረሰውን ጉዳት በማከም እና ለማስታረቅ አብረን መስራት እንችላለን ብለዋል።

ደች በ17ኛው ክፍለ ዘመን አሁን ላይ ኢንዶኔዢያ፣ ደቡብ አፍሪካ እና ምዕራብ ፓፑአ ቅኝ ተብለው የሚጠሩ አገራትን በመግዛት በባሪያ ንግድ ላይ ቁልፍ ሚናን ተጫውታለች።

የባሪያ ንግድ እአአ 1863 ላይ እንዲቆም ከመደረጉ በፊት በሺዎች የሚቆጠሩ አፍሪካውያን ከአፍሪካ አህጉር በኔዘርላንድስ ቅኝ ይገዙ ወደነበሩ ካረቢያን እና ደቡብ አሜሪካ አገሮች ተግዘዋል።

ኔዘርላንድስ እንደ ሃገር ከባሪያ ንግድ ከፍተኛ ሃብት አፍርታለች። እአአ 1738 እና 1780 መካከል በአገሪቱ ለተገኘው የምጣኔ ሃብት 40 በመቶ ድርሻውን የሚይዘው የባሪያ ንግድ ነው።

ከንጉሡ በተጨማሪ ከአንድ ዓመት በፊት የደች ጠቅላይ ሚንስትር ማርክ ሩት አገራቸው በባሪያ ንግድ ላይ ለነበራት ተሳትፎ ይቅርታቸውን አቅርበዋል።

እንደ አምስተርዳም እና ሮተርዳም ያሉ ከተሞችም በባሪያ ንግድ ላይ ለነበራቸው ተሳትፎ ይቅርታቸውን አቅርበዋል።

ሆላንድ በባሪያ ንግድ ላይ ለነበራት ተሳትፎ ይቅርታዋን ትለግስ እንጂ አገሪቱ በባሪያ ንግድ ላይ ስለነበራት ተሳትፎ ታዳጊ ዜጎቿ የሚማሩባቸው የታሪክ መጽሐፍት ላይ ለማካተት እስከ 2006 ቆይታ ነበር።