በዋጋ መናር ምክንያት የኢትዮጵያ ፀሐፊያን ሥራዎች የሕትመት ብርሃንን ላያዩ ይሆን?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ብዕራቸው ከዓመት ዓመት የማይነጥፍ፣ የአንባቢን የአእምሮ ረሃብ ለማስታገስ የሚታትሩ፣ ጥናት እና ምርምር የሚያደርጉ ደራሲያን ፈተና ውስጥ መውደቃቸውን በተለያየ አጋጣሚ እየተናገሩ ነው።
በዕውቀቱ ስዩም በይፋዊ የፌስቡክ ሰሌዳው ላይ “በድርሰት ሥራ ከተሰማራሁ ጊዜ ጀምሮ አንባቢዎቼን ያሳውቃል፣ ያዝናናል ብዬ እማስበውን ሁሉ አጋራለሁ፤ በዋጋም በብላሽም (በነጻም)! አሁን የወረቀት ዋጋ እጅግ እጅግ ናረ! ድርሰት አሳትሞ እንጀራ መብላት ጉዳይ አደጋ ላይ ወድቋል!...” ሲል የመጽሐፍት ሕትመት ዋጋ መወደድን በተመለከተ አስፍሮ ነበር።
ለደራሲያኑ መጽሐፍትን ለማሳተም የሚወጣው ወጪ ከቀን ቀን እየጨመረ መሄዱ ራስ ምታት ሆኖባቸዋል።
በቅርቡ “ጠመንጃ እና ሙዚቃ” የተሰኘውን መጽሐፉን ለንባብ ያበቃው ይነገር ጌታቸው (ማዕረግ) የሕትመት ዋጋ የደራሲያንን እጅ እና እግር አስሮ ማስቀመጡን ይናገራል።
አስራ አራት መጽሐፍትን ለንባብ ያበቃው እንዳለጌታ ከበደም የሕትመት ዋጋ ከዕለት ዕለት እየናረ መሆኑን ሲያስረዳ “የዛሬ ዋጋ ለነገ አይሰራም” በማለት ነው።
ሰዎች እኮ የዕለት ተዕለት የኑሮ ውድነቱን በተለያየ መንገድ ተጋፍጠው ወደ መጽሐፍት ጋር ሲመጡ ይደነግጣሉ የሚለው ደግሞ ይነገር ነው።
በሕትመት ዋጋ መናር የተነሳም አንባቢያን ከተሳፈሩበት የንባብ ሰረገላ ላይ ለመውረድ ቅርብ መሆናቸውንም ይጠቁማል።
እንዳለ ጌታ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን ሲመጡ ከመጽሐፍት ሕትመት እና ዋጋ ጋር በተያያዘ ለውጦች ይኖራሉ ብሎ ተስፋ አድርጎ እንደነበር ያስታውሳል።
የእንዳለ ጌታ ከበደ ተስፋ ግን የመጻሕፍት ሕትመት እና አሳታሚነት ላይ የተሻለ ነገር ይኖራል የሚል ብቻ ሳይሆን፣ የኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ ላይ መነቃቃት ይኖራል የሚልም ነበር።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ሥልጣን ከመምጣታቸው በፊትም ሆነ ጠቅላይ ሚኒስትር ከሆኑ በኋላ በርካታ መጻሕፍትን በማሳተማቸው “የደራሲያን ምጥ እና መከራ” ይገባቸዋል ብሎ ማሰቡን ያነሳል።
ለእንዳለ ጌታ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ደራሲ መሆን ብቻ ሳይሆን፣ በደራሲያንም መከበባቸው ተስፋ የማድረጉ ሌላው ምክንያት ነው።
የኢትዮጵያ ደራሲያን ማኅበር ፕሬዝዳንት አበረ አዳሙ “ማኅበራችን በወረቀት መወደድ ምክንያት ከፍተኛ ችግር ውስጥ ነው ያለው” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
አቶ አበረ የመጽሐፍ ሕትመት ዋጋ በዚሁ ከቀጠለ “ለወደፊቱ መጽሐፍ የሚባልስ ነገር ይኖራል ወይ? ደራሲስ ሊኖር ይችላል ወይ?” ሲሉ ማኅበሩ መልስ ያላገኘለትን ጥያቄ መልሰው ይጠይቃሉ።
ለደራሲ አበረ በመጪዎቹ ዓመታት የሕትመት ዋጋ በዚሁ ከቀጠለ “መጽሐፍ የሚባል ላይታተም ይችላል።”

የፎቶው ባለመብት, Walia publisher
“በሕትመት ዋጋ ውድነት የተነሳ የአገር ታሪክ ቆርጬ አውጥቻለሁ”
በአሁን ጊዜ 5000 ቅጂ መጽሐፍት ለማሳተም አንድ ሚሊዮን ብር ገደማ ያስፈልጋል የሚለው እንዳለ ጌታ፣ ደራሲው በሕትመት ዋጋ መናር የተነሳ በተስፋ መቁረጥ መሸበቡን ይናገራል።
ይነገር ከሁለት ዓመት በፊት “የከተማው መናኝ” የተሰኘውን እና በኤልያስ መልካ የሙዚቃ ሕይወት ዙሪያ ላይ ያተኮረውን የመጀመሪያ መጽሐፉን አንዱን በ57 ብር ነበር ያሳተመው።
በዚህም በወቅቱ 5000 ቅጂ መጽሐፍት ለማሳተም 257 ሺህ ብር ገደማ ነበር የከፈለው።
አሁን ግን ሁለተኛ መጽሐፉን አንዱን ከ210 ብር በላይ ማሳተሙን በመግለጽ፣ የሕትመት ዋጋ ውድነቱን በንጽጽር ለማሳየት ይሞክራል።
የኢትዮጵያ ሙዚቃ ታሪክ እና ፖለቲካን የሚያነሳ መጽሐፉን፣ ጠመንጃና ሙዚቃ፣ 3000 ቅጂ ለማሳተም ግን ከ600 ሺህ በላይ መክፈሉን ለቢቢሲ ገልጿል።
የመጽሐፍ የገጽ ብዛት የሕትመት ዋጋ ላይ የራሱ የሆነ ልዩነት ስለሚያመጣ “የብዙ ሰዎች ታሪክን አውጥቼ ነው ያሳተምኩት። ምክንያቱም ከምችለው በላይ ስለሆነ ነው ገጽ መቀነስ የነበረብኝ” ይላል።
መጽሐፉን ወደ 400 ገጽ ለማውረድ ሲል የበርካታ የኪነጥበብ ባለሙያዎችን ታሪክ ማውጣቱንም ሲያስረዳ “የአገር ታሪክ ቆርጬ አውጥቻለሁ” በማለት ነው።
380 ገጽ የያዘው ይህ የይነገር መጽሐፍ 450 በር እንዲሸጥ የተተመነለት ቢሆንም፣ መጽሐፉ የለፋሁበት በመሆኑ እና አንባቢ ጋር እንዲደርስ ፍላጎት ስለነበረኝ በብዙ መንገድ የእኔን ትርፍ ቀንሼ ነው ለአንባቢያን ያቀረብኩት ይላል።
“የአሳታሚ እና የአከፋፋይ ጥቅምን እነካለሁ ከተባለ የተለፋበት መጽሐፍ ከገበያ ይወጣል” ሲልም የገበያው ሰንሰለት ፈታኝ መሆኑን ያብራራል።
እንዳለጌታ ከበደ የወረቀት ዋጋ መወደድ ብዙ ደራሲዎች እንዳያሳትሙ ወደ ኋላ እንደጎተታቸው የራሱን ልምድ አንስቶ ሲናገር “ይህ አሁን ያሳተምኩት መጽሐፍ [እስረኞቹ] ባለፈው ክረምት ታትሞ ቢሆን ኖሮ መሸጫ ዋጋው 300 ብር ይሆን ነበር” ይላል።
ደራሲያን ከሚያሳትሙት መጽሐፍ የሚያገኙት ጥቅም እዚህ ግባ የሚባል እንዳልሆነ የሚናገሩት ደራሲያኑ አከፋፋዮች 40 በመቶ ድረስ ይወስዳሉ ይላሉ።
አብዛኛው ደራሲ ለመጽሐፉ ዋጋ ለመተመን እጅጉን እንደሚጨነቅ የሚናገረው እንዳለ አንባቢን ሳይገፉ፣ የአእምሯቸው ውጤትም ዋጋ ሳያጣ ማሳተም የገቡበት በሕትመት ዋጋ መወደድ ምክንያት የገቡበት አጣብቂኝ መሆኑን ይጠቅሳል።
የኢትዮጵያ አንባቢያን ዝቅተኛ እና መካከለኛ ገቢ ያላቸው መሆናቸውን የሚጠቅሱት ደራሲያኑ፣ በአሁኑ ወቅት 500 እና 1000 ቅጂ ማሳተም ብርቅ መሆኑን ይናገራሉ።
ደራሲያኑ አክለውም እነዚህ አንባቢያን የቤታቸውን ቀዳዳ ከደፈኑ በኋላ ወደ መጽሐፍ ገበያ ብቅ እንደሚሉ በመጥቀስ፣ መጽሐፍ ልክ እንደ ፍጆታ እቃ ሸመታ በክርክር የሚገዛበት ሥርዓት መፈጠሩ የገበያው ራስ ምታት መሆኑን ያነሳሉ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
“የሕትመት ዋጋ ውድነቱ በዚሁ ከቀጠለ ከገበያ መውጣቴ አይቀርም”
መጽሐፍ በመሸጥ እና በማሳተም በአጠቃላይ 30 ዓመታት በዘርፉ ላይ መቆየታቸውን የሚናገሩት አቶ ዓይናለም መዋ፣ በሕትመት ዋጋ መናር የተነሳ ያዘገይዋቸው መጽሐፍት መኖራቸውን ለቢቢሲ ገልጸዋል።
አቶ አይናለም ሊያሳትሟቸው የነበሩ መጽሐፍትን “ለጊዜው ገታ አድርገናቸዋል” ሲሉ የዋጋው ውድነት ያደረሳባቸውን ጫና ያስረዳሉ።
“ቢታተሙ የሕትመት ዋጋቸው ሦስት እና አራት እጥፍ ስለሆነ ገበያ ላይ የሚገዛቸው ሰው ምን ያህል ነው በሚል ስጋት ለጊዜው እንዲቆዩ አድርገናቸዋል።”
አቶ አይናለም የአሌክስ አብርሃም እና የበዕውቀቱ ስዩም መጽሐፍትን ከዚህ በፊት ማሳተማቸውን በማስታወስ፣ የታተሙት ቅጂዎች አልቀው ለዳግም ሕትመት ለማዘዝ ዋጋ በመናሩ ምክንያት ብቻ አዘግይተዋቸዋል።
የእነዚህ ደራሲያን መጽሐፍት ከዚህ ቀደም ሲታተሙ ከ105 እስከ 120 ብር ይሸጡ የነበሩ ሲሆን፣ አሁን ግን ዋጋቸው በትንሹ ወደ ሦስት መቶ ብር ሊገባ ይችላል ብለዋል።
“ስለዚህ ሦስት መቶ ብር ገዝቶ የሚያነበው ማን ነው የሚለው ያሰጋል” ይላሉ።
ከ16 ዓመት በላይ በመጽሐፍ ሽያጭ እና ማከፋፈል ላይ የቆየው ጃዕፈር ሽፋ፣ ምንም እንኳ ልክ እንደሌሎች ዋጋዎች የመጽሐፍ ዋጋም ጭማሪ እያሳየ ቢሆንም፣ በንጽጽር ባለፉት ሦስት ዓመታት ግን ዋጋው በአንዴ በእጥፍ መጨመሩን ይናገራል።
ከዚህ ቀደም የመጽሐፍት ዋጋ ከ15 ወደ 20 ብር ለማደግ ዘገምተኛ እንደነበር የሚያስታውሰው ጃዕፈር፣ የቅርብ ዓመታቱ ጭማሪ ግን “በጣም ፈጣን እና ከፍተኛ” መሆኑ ለየት አንደሚያደርገው ያስረዳል።
የሕትመት ዋጋ እየናረ መምጣት የጎዳው ደራሲያኑን ብቻ ሳይሆን ማተሚያ ቤቶችን ጭምር መሆኑን የሚያነሳው እንዳለጌታ “እኔ የማውቃቸው አርባ እና ሃምሳ ሠራተኞች የነበሯቸው ማተሚያ ቤቶች አሁን በ20 ተወስነዋል።”
አቶ ዓይናለምም ተመሳሳይ ነገር ነው የገጠማቸው። እሳቸው ከዚህ ቀደም 45 ሠራተኛ ቀጥረው ያሰሩ የነበረ ሲሆን፣ የሕትመት ዋጋ በመናሩ እና ገበያ በመቀነሱ ብቻ አሁን 28 ሠራተኞች ብቻ ነው ያሏቸው።
በአገሪቱ የሚታተሙት መጽሐፍት ብቻ አይደኩም የሚለው ጃዕፈር የሕትመት ዋጋ መናር “እየፈተነ ያለው ሁሉንም ነው” በማለት፣ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች፣ ባንክ ቤቶች እና ሌሎችም ተቋማት ላይ ጫና እየጠረ መሆኑን ያስረዳል።
በመጽሐፍት ሕትመቱ ዘርፍ ደግሞ በርካታ ተዋንያን ስላሉ ደራሲያንን፣ አሳታሚዎችን፣ አከፋፋዮችን፣ መደብሮችን እና አዟሪዎችን በመጉዳት አንባቢያንን በተለያየ መልኩ ተጎጂ እና ጫናውን ተጋሪ ያደርጋቸዋል።
በዚህ የተነሳም በማቃሰት እና ተስፋ በመቁረጥ የተሞላው የወጣት እና የአንጋፋ ደራሲያን ሕይወት ወደ ሌሎችም መጋባቱን እንዳለጌታ መሸሸግ አልፈለገም።
አቶ አይናለም መጽሐፎችን የሚያሳትሙት በራሳቸው ማተሚያ ቤት መሆኑን በማስታወስ፣ የሕትመት ዋጋ በዚሁ ከቀጠለ ለሚመለከተው የመንግሥት አካል ኪሳራ እያሳዩ መቆየት የሚችሉት ሁለት እና ሦስት ዓመት ብቻ መሆኑን በማንሳት “ከዚያ በኋላ ግን ማሽኖቹን ሸጠን ወደሌላ ዘርፍ እንገባለን ማለት ነው” ሲሉ የተጋረጠባቸውን አደጋ ያስረዳሉ።
የኢትዮጵያ አሳታሚዎች እና አታሚዎች ማኅበር ምክትል ፕሬዝዳንት የሆኑት አቶ በፍቃዱ ደምሴ፣ ከሁለት ዓመት በፊት አንዱ 32 ገጽ የሚሰጥ 60 ግራም (61*86) ወረቀት አንድ ሺህ ብር ሲሸጥ እንደነበር አስታውሰው አሁን ግን 4300 ብር መግባቱን በመጥቀስ የሌሎቹም ዋጋ መናሩን ይናገራሉ።
ለመጽሐፍ ሕትመት ግብዓት መወደድ ዓለም አቀፍ ምክንያቶች እንዳሉ ቢጠቀስም “የእኛ ግን ኢፍትሐዊ መሰለኝ” ሲሉም አስተያየታቸውን ያክላሉ።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው አሳታሚዎች እና አከፋፋዮች በአንድ ድምጽ የሚስማሙበት ለሕትመት ዋጋ መናር ዋናው ምክንያት የወረቀት ዋጋ መናር ነው።
ከዚህ በተጨማሪም የሕትመት ግብዓት አስመጪዎቹ በቁጥር አነስተኛ መሆናቸው እና በዚህም የተነሳ ውድድር መጥፋቱ ለዋጋው መናር አስተዋጽኦ ማድረጉን ያለልዩነት ይናገራሉ።
አክለውም እንደ ሌሎች ምርቶች ሁሉ በአገሪቱ ያለው የውጭ ምንዛሪ እጥረት አስተዋጽኦ ማድረጉን አንስተዋል።
አቶ ዓይናለም አስመጪዎቹ በዚህ ሁሉ ውስጥ የሕትመት ግብዓቶችን ሲያስመጡም “ጠብቀው በውድ ዋጋ ነው የሚሸጡት” ሲሉ ያስረዳሉ።
አቶ በፍቃዱ ያለውን የዋጋ ንረት መቋቋም ያቃታቸው ማተሚያ ቤቶች ከገበያ እየወጡ መሆኑን አልሸሸጉም።

የፎቶው ባለመብት, Walia publisher
ምን መፍትሔ አለ?
እንዳለጌታ ከበደ ጠቅላይ ሚኒስትሩን የከበቧቸው ደራሲያን ስለ ሕትመት ዋጋ መናር አንስተው ከእርሳቸው ጋር ተወያይተው ከሆነ “ወይ አልነገሩንም እኛም መፍትሔውን አላየንም” ሲል ችግሩ የመንግሥት ቀጥተኛ ተሳትፎ እንደሚፈልግ ይጠቁማል።
ይነገር ጌታቸው በበኩሉ “ሐሳብ ያለው ትውልድ ያስፈልጋል እየተባለ ያለ መጽሐፍ ሐሳብ ከየት ይመጣል?” በማለት መንግሥት እንዲያስብበት ይወተውታል።
በዕውቀቱ ስዩም በፌስቡክ ልጥፉ ላይ “...መንግሥት የወረቀት ዋጋን ለመደጎም አልፈቀደም፤ ወይ አልቻለም!...” ሲል ሐሳቡን አስፍሯል።
የመንግሥት አካላትን ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ እንደሚወተውቱ፣ ነገር ግን መፍትሔ እንደሌለ ለቢቢሲ የተናገሩት ደግሞ የደራሲያን ማኅበር ፕሬዝዳንቱ አቶ አበረ ናቸው።
የአእምሮ ረሃባችንን ለማስታገስ እንዲረዳ መንግሥት የተለያዩ እርምጃዎችን መውሰድ እንደሚገባው አቶ አበረ ያስረዳሉ።
እንዳለጌታ መንግሥት ድጋፍ ካላደረገ አንባቢ እና ደራሲያን ላይገናኙ የሚሰነባበቱበት ጊዜ ሩቅ አለመሆኑን ይጠቁማል።
አክሎም ከዚህ በፊት የነበሩ መንግሥታትን ልምድ መመልከት ጠቃሚ መሆኑን ያነሳል። ይህ ደግሞ አንባቢንንም ደራሲያኑንም ይጠቅማል ሲል ይናገራል።
በአጼ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት መጻሕፍት ተመርጠው ማስተማርያ እንዲሆኑ በመወሰን በየቤተ መጻሕፍቱ እንዲገቡ ይደረግ እንደነበር በማንሳት ይህ ተሞክሮ አሁንም ሊሠራ እንደሚችል ይጠቁማል።
በዚህም የአንባቢን ቁጥር ማሳደግ፣ የሚታተሙ መጻሕፍትን ቁጥር በማብዛት የሕትመት ዋጋን መቀነስ እንደሚቻል ተስፋ አለው።
በደርግ የሥልጣን ዘመን ደግሞ መጽሐፍ ሲታተም ወታደሩ ማንበብ አለበት ተብሎ ስለሚታመን ይወሰድለት አንደነበር በማስታወስ፣ ይህም የሚታተሙ የመጽሐፍት ብዛትን ሰማንያ ሺህ እና ዘጠና ሺህ ያደርሰዋል።
በጣም አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ወረቀት አስመጪዎች መኖር ቢቢሲ ያነጋገራቸው በሕትመቱ ዘርፍ የተሰማሩ አካላት በሙሉ የሚያነሱት ጉዳይ ነው።
አቶ ፍቃዱም ሆኑ እንዳለጌታ ከሕትመት ጋር ተያያዥ የሆኑ ግብዓቶችን የሚያስመጡ ድርጅቶችን ቁጥር ማብዛት፣ ማተሚያ ቤቶችንም ቢሆኑ መደጎም አስፈላጊ መሆኑን ያነሳሉ።
አቶ ፍቃዱ አክለው ምንም እንኳ መንግሥት መጽሐፍ ላይ የተጨማሪ ዕሴት ታክስን (ቫት) ቢያነሳም ወረቀት ግን ታክሱ ታሳቢ ሆኖ አንደሚሸጥ ይናገራሉ።
ስለዚህ ሕትመት ወረቀት ላይ የተጣለውን ቫት መንግሥት ቢቀንስ የሕትመት ዋጋ ላይ ለውጥ ይኖረዋል ሲሉ ይናገራሉ።












