አሜሪካዊው ከ65 ዓመታት በፊት ከቤተ መጻህፍት የተዋሱትን የጆርጅ ኦርዌልን መጽሃፍ መለሱ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ለታዋቂው ደራሲ ጆርጅ ኦርዌል ትልቅ ክብር ያላቸው አሜሪካዊ ግለሰብ ከ65 ዓመታት በፊት ከቤተ መጻህፍት የተዋሱትን መጽሃፍ በቅርብ መልሰዋል።
1984 የተሰኘውን መጽሃፍም ነበር ከፖርትላንድ የህዝብ ቤተ መጻህፍት ተውሰው የነበረው።
ከስድስት አስርት ዓመታት በላይ ያስቀመጡትንም መጽሃፍ ኦሪገን ግዛት ለሚገኘው ቤተ መጻህፍት ቤት ከማስታወሻ ጋር አስረክበዋል።
ከመጽሃፉ ጋር በተያያዘ ማስታወሻ ላይ ስማቸውንም ደብልዩ ፒ በሚል ምህጻረ ቃል አስፍረዋል።
በአሁኑ ወቅት የ86 ዓመት አዛውንት የሆኑት እኚህ ግለሰብ መልቲኖማህ ለተሰኘው የፖርትላንድ ግዛት ቤተ መጻህፍት ለመመለስ የወሰኑትም መጽሃፉ ለዚህ ትውልድ ከፍተኛ ጥቅም እንደሚሰጥ በማሰብ ነው።
“መጽሃፉን እንደገና እየደገምኩና እየከለስኩ ካነበብኩ በኋላ ከመቼውም ጊዜ በላይ ይህ መጽሃፍ መነበብ እንዳለበት ተገነዘብኩ” በማለት በማስታወሻቸው ላይ አስፍረዋል።
ሳይንሳዊ ልብወለድ ተብሎ ሊፈረጅ የሚችለው 1985 ፍጹም ጭቆና እና እውነትን ጭብጦች ይዳስሳል።
“ከፖርትላንድ ስቴት ዩኒቨርስቲ ልመረቅ በነበረበት ወቅት ይህንን መጽሃፍ በ1958 [እአአ] ለመመለስ አስቤ ነበር፤ ነገር ግን ማሳካት አልቻልኩም” ሲሉም በዚሁ ማስታወሻ ላይ አስፍረዋል።
“ዘግይቼ በመመለሴ በጣም ይቅርታ። በ86 ዓመቴም ቢሆን በመጨረሻ ከህሊናዬ ጥያቄ ነጻ መሆን ፈለግኩ” ብለዋል።
የተወሰኑ የመጽሃፉ ክፍሎችን እንደገና ማንበባቸውም ለመመለስ እንዳነሳሳቸው ተናግረዋል።
“አንዳንድ ሃሳቦች ምንም ሳይቀየሩ ልክ ከ65 ዓመት በፊት እንደነበረው ሁሉ በጣም ጠቃሚ ናቸው” ያሉት ግለሰቡ ለምሳሌ ገጽ 107 ላይ የተጠቀሰውን ሃሳብ ነቅሰው አውጥተዋል።
“ኢንተርኔት እና ማህበራዊ ሚዲያ የሚሉ ቃላቶችን ብትጨምሩበት ስለ 2023 እያነበባችሁ እንደሆነ ይሰማችኋል” ብለዋል።
በአውሮፓውያኑ 1949 ለህትመት የበቃው ይህ መጽሃፍ ማንኛውም ነጻ ሃሳቦችና ሂሶች በፈላጭና ቆራጭ ስርዓት የሚታፈንበት ዓለምን ያስቃኛል።
የትራምፕ ከፍተኛ አማካሪ የቀድሞው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የ2017 ሲመተ በዓልን ለመታደም የመጣው የህዝብ ቁጥር ጋር ተያይዞ ውዝግብ ተገብቶ በነበረበት ወቅት ዋይት ሃውስ “አማራጭ እውነታዎችን” እየሰጠ ነው ሲሉ መተቸታቸውን ተከትሎ የ1984 መጽሃፍ ሽያጭ በከፍተኛ ሁኔታ አሻቅቦ ነበር።
የመልትኖማህ የህዝብ ቤተ መጽሃፍ መጽሃፉ እንዲህ ዘግይቶ ቢመለስም ቅጣት አይኖርም ብሏል።












