በአመፅ እየታመሰች ያለችው የፈረንሳይዋ ከተማ ማርሴ በአስለቃሽ ጭስ ታፍናለች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አውሮፓዊቷ ሃገር ፈረንሳይ አንድ ታዳጊ የፖሊስ ጥይት ሰለባ መሆኑን ተከትሎ ከባለፈው ሳምንት ጀምሮ በአመፅ እየታመሰች ነው።
በማርሴ ፖሊስና አመፀኞች ተጋጭተው ከተማዋ በአስለቃሽ ጭስ ታፍና ውላለች።
በደቡባዊቷ ከተማ በተነሳው አመፅ ምክንያት እስካሁን በትንሹ 54 ሰዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ፖሊስ ገልጧል።
ነገር ግን በዋና ከተማዋ ፓሪስ በርካታ ፖሊስ ተደርድሮ አመፀኞችን መመከት ችሏል።
የትራፊክ ፖሊስ ጥሶ ሲያሽከርክር በፖሊስ ጥይት የተገደለው የ17 ዓመቱ ናሄል የቀብር ስነ-ስርዓት ላይ በርካታ ሰዎች ተገኝተዋል።
ማክሰኞ ዕለት ታዳጊው በፓሪሷ ናንቴር ክፍለ ከተማ ከተገደለ በኋላ ሺህዎች ለአመፅ ወጥተዋል።
የሃገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዤራልድ ዳርማኒን የፀጥታ ሰዎች በወሰዱት እርምጃ “ምሽቱ ተራጋግቷል” ሲሉ በትዊተር ገፃቸው ፅፈዋል።
ከቅዳሜ ጀምሮ 45 ሺህ ያክል ፖሊስ አመፅ በተነሳባቸው የሃገሪቱ ከተሞች ተሰማርተዋል።
አርብ ዕለት 1300 ሰዎች መታሰራቸው ሲገለጥ፤ ሐሙስ ደግሞ 900 ያክል አመፀኞች በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ተነግሮ ነበር።
ቅዳሜ አመሻሹን በማርሴ ከተማ ፖሊስና አመፀኞች ከባድ ግጭት ውስጥ ገብተዋል።
የፈረንሳይ መገናኛ ብዙሃን እንደዘገቡት በርካታ ቁጥር ያላቸው አመፀኞችና የፖሊስ ኃይል ለአንድ ሰዓት ያክል ሲጋጩ አምሽተዋል።
በዋና ከተማዋ ፖሊስ በለተይ የቱሪስት መስሕብ በሆነው ሻም ዜሊዚ በርካታ ፖሊስ ተሰድሮ ታይቷል።
በርካቶች በማሕበራዊ ሚድያ በሥፍራው እንገናኝ የሚል መልዕክት ቢለዋወጡም ፖሊስ በአካባቢው መስፈሩ ይህ እንዳይሆን ምክንያት ሆኗል።
በመዲናዋ ፓሪስ ለሁለተኛ ምሽት ባቡርና አውቶቡስ ከምሽቱ 3 ሰዓት በኋላ አገልግሎት እንዳይሰጡ ታግደዋል።
የፈረንሳይ ጠቅላይ ሚኒስትር ኤሊዛቤት ቦርን ፖሊስ እንዴት አመፁን እየተቆጣጠረ እንዳለ ለመታዘብ ፖሊስ ቢሮ በአካል ተገኝተው እንደነበር ተሰምቷል።
በሰሜናዊቷ የሊል ከተማ የፖሊስ ልዩ ኃይል መንገዶችን መቆጣጠር ጀምሯል።
የእሣት አደጋ ሠራተኞች በከተማዋ በተነሳው አመፅ ምክንያት በእሣት የተቃጠሉ ተሽከርካሪዎችን እሣት ሲያጠፉ አምሽተዋል።
የ17 ዓመቱ ናሄል ቀብር ቅዳሜ ዕለት በናንቴር ከተማ በሚገኝ መስጅድ ተፈፅሟል።
የቀብር አስፈፃሚዎችና ቤተሰብ መገናኝ ብዙሃንም ሆኑ ማንኛውም ሰው ካሜራ እንዳይጠቀም ከልክለዋል።
ታዳጊው የተገደለው የፖሊስ ቁም ትዕዛዝን ጥሶ ለማለፍ ሲንደረደር ነበር።
ከግድያው በኋላ ማሕበራዊ ሚድያ ላይ የለተጠፉ ምስሎች እንደሚያሳዩት ሁለት ፖሊሶች መኪናዋን ለማስቆም ሲጥሩ አንደኛው ፖሊስ ጥይቱን ደግኖበር ነበር።
ታዳጊውን በጥይት የመታው ፖሊስ በግድያ ወንጀል ክስ የተመሰረተበት ሲሆን ለቤተሰቡ ይቅርታ ጠይቋል።
የታዳጊው ግድያ፤ ፖሊስ አሽከርካሪዎች አናቆምም ሲሉ መተኮስ ይችላል የሚለው አወዛጋቢ የ2017 ሕግ ድጋሚ የክርክር ምክንያት እንዲሆን አድርጓል።
አልፎም በፈረንሳይ የፀጥታ ኃይል ውስጥ ያለው ዘረኝነት ጥያቄ ላይ እንዲወድቅም ሆኗል።
የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብት ቢሮ ይህ ፈረንሳይ “በሕግ አስከባሪው አካል ውስጣ ያለውን ዘረኝነት እንድታጤንበት መልካም አጋጣሚ ነው” ብሏል።
የፈረንሳዩ ፕሬዝደንት ኢማኑዔል ማኽሮ ሰልፍ የወጡ ሰዎች የናሄል ሞት ምክንያት አድርገው ሕገ-ወጥ ድርጊት ፈፅመዋል ሲሉ ኮንነዋል።












