የዩክሬን መልሶ የማጥቃት ዘመቻ ደም አፋሳሽ እንደሚሆን አሜሪካዊው ጄኔራል ተናገሩ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ዩክሬን በሩሲያ ኃይሎች ላይ እያካሄደችው ያለው መልሶ ማጥቃት አስቸጋሪ እና “ደም አፋሳሽ” ሊሆን እንደሚችል አንድ የአሜሪካ ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንን ተናገሩ።
ጄኔራል ማይክ ሚሊ ዩክሬን እያካሄደችው ያለው የመለሶ ማጥቃት ሂደት ከተገመተው በተለየ አዝጋሚ መሆኑን አመልክተው፣ ነገር ግን የዩክሬን ኃይሎች “በዝግታ ወደፊት እየገፉ” መሆናቸውን ጨምረው ገልጸዋል።
“መልሶ ማጥቃቱ ዝግ ባለ ሁኔታ እየሄደ ነው፤ነገር ግን ይህ የጦርነት ባህርይ ነው” ብለዋል ጄኔራል ማይክ ሚሊ።
ባለፈው ሳምንት የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ ሠራዊታቸው የሚያካሂደው መልሶ ማጥቃት ዝግ ያለ መሆኑን ማመናቸው ይታወሳል።
የአሜሪካ ጦር የጋራ ኤታማዦር ሹም የሆኑት ጄኔራል ማይክ ሚሊ አርብ ዕለት ዋሽንግተን ውስጥ በሚገኘው ናሽናል ፕሬስ ክለብ ለተሰበሰቡ ታዳሚዎች እንደተናገሩት የዩክሬን መልሶ ማጥቃት “አስቸጋሪ በመሆኑ ፈንጂ በተቀበረባቸው አካባቢዎች ሆን ተብሎ በዝግታ እየተካሄደ ነው።”
የመልሶ ማጥቃቱ ፍጥነት ከሚጠበቀው በላይ አዝጋሚ መሆኑ እምብዛም እንዳላስደነቃቸውም ጄኔራሉ አመልክተዋል።
“በወረቀት ላይ የሚታቀደው ጦርነት እና በተግባር የሚካሄደው ጦርነት ልዩነት አላቸው።በእውነተኛው ጦርነት ሰዎች ይሞታሉ” ብለዋል።
“ሰዎች በአካል በጦር ግንባሮች ላይ ተሰልፈው እየተዋጉ ነው። በዚህም በከፍተኛ ፈንጂዎች የሚቆራረጡት የሰዎች አካል ክፍሎች ናቸው። ይህንን ስል ጦርነቱ አስቸጋሪ ሊሆን እና ሳምንታት ወይም ወራትን ሊወስድ ይችላል። ስለዚህም ረጅም ጊዜ የሚወስድ እና በጣም በጣም ደም አፋሳሽ ይሆናል። ይህንን በተመለከተ ማናችንም ብዥታ ሊኖረን አይገባም።” ብለዋል ጄኔራል ማይክ።
የዩክሬን ወታደሮች ጥቃት እያካሄዱ ያሉት “ፈንጂ በተቀበረባቸው መስኮች በኩል ወደ ምሽጎች ነው” በማለት “ይህ ማለት ደግሞ ወታደሮቹ የሚፋለሙት ነፍሳቸውን ለማትረፍ ነው” ብለዋል ጄኔራሉ።
ጨምረውም አሜሪካ ለዩክሬን ማድረግ የምትችለውን ሁሉ እየሰጠች መሆኑን ገልጸዋል።
ጄኔራል ማይክ ሚሊ ከፍተኛው የአሜሪካ ጦር ሠራዊት ጄኔራል ሲሆኑ የፕሬዝዳንት ባይደን ወታደራዊ አማካሪ፣ የአሜሪካ መከላከያ እና የብሔራዊ የደኅንነት ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ ናቸው።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የዩክሬን ወታደራዊ ጠቅላይ አዛዥ የሆኑት ቫለሪ ዛሉዢኒ፣ የአገራቸው የመልሶ ማጥቃት ዘመቻ የተስተጓጎለው ባለባቸው ዝቅተኛ የከባድ መሳሪያ የተኩስ አቅም ነው ሲሉ ተናግረዋል።
አርብ ዕለት ከታተመው ዋሽንግተን ፖስት ጋር አዛዡ ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ ከዘመናዊ ተዋጊ ጄቶች አንስቶ እስከ መድፍ ጥይቶች ድረስ ምዕራባውያን ሊሰጧቸው ቃል የገቡት የጦር መሳሪያዎች አቅርቦት አዝጋሚ መሆን ተስፋ እንዳስቆረጣቸው ገልጸዋል።
“ፍላጎታችን ዓለምን ስጋት ላይ መጣል ስላልሆነ 120 የጦር ጄቶች አያስፈልጉንም። በጣም የተወሰኑ ጄቶች ብቻ ይበቁናል” ብለዋል አዛዡ።
በሌላ በኩል ደግሞ የአሜሪካ የስለላ ድርጅት ሲአይኤ ኃላፊ ዊሊያም በርንስ በቅርቡ ይፋ ባልተደረገ ጉብኝት ወደ ዩክሬን አምርተው ከፕሬዝዳንት ዜሌንስኪ እና ከዩክሬን የደኅንነት ባለሥልጣናት ጋር ተወያይተዋል።
የሲአይኤው ኃላፊ በቆይታቸው ዩክሬን በሩሲያ ኃይሎች ላይ እያካሄደች ስላለችው የመልሶ ማጥቃት ዘመቻ የተወያዩ ሲሆን፣ አሜሪካ ለዩክሬን የደኅንነት መረጃዎችን ማጋራቷን እንደምትቀጥል አረጋግጠዋል።












