የዩክሬንን የመልሶ ማጥቃት ዘመቻን እየመሩ ያሉት ቁልፍ ሰው

የዩክሬን ጦር ዋና አዛዥ ጄነራል ቫለሪ ዛሉዝህኒ

የፎቶው ባለመብት, Ukraine Army

የምስሉ መግለጫ, የዩክሬን ጦር ዋና አዛዥ ጄኔራል ቫለሪ ዛሉዝህኒ

ሩሲያ በዩክሬን ላይ ወረራ ከፍታ ግዛቶቿን በኃይል ከተቆጣጠረች 18 ወራት ተቆጠሩ።

ዩክሬንም በምሥራቅ እና በደቡብ በኩል በሩሲያ የተያዙባትን ግዛቶች ለማስመለስ ለረጅም ጊዜ ሲጠበቅ የነበረውን መልሶ ማጥቃት ጀምራለች።

መልሶ ማጥቃቱ መጀመር ብቻ ሳይሆን ተጠናክሮ ቀጥሏል።

ዘመቻውን በማቀድ እና በማስፈጸም ረገድ አንድ ቁልፍ ሰው ተቀምጠዋል።

የ49 ዓመቱ የዩክሬን ጦር ዋና አዛዥ ጄኔራል ቫለሪ ዛሉዝህኒ።

ጄኔራሉ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ እምብዛም አይታወቁም ነበር።

ጦርነቱን ተከትሎ ግን እውቅና እና ዝናቸው ከዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮለድሚር ዜሌንስኪ ጋር ይቀናቀናል።

ጄኔራል ዛሉዝህኒን የትምህርት ቤት ጓደኞቻቸው እና ወዳጆቻቸው “የእኛ ቫሌራ” ሲሉ ይጠሯቸዋል።

የዩክሬን ጦር ዋና አዛዥ ሆነው የተሾሙት በአውሮፓውያኑ 2021 ነው።

እሳቸውን በቅርበት የሚያውቁ ሹመታቸው ቀጥታ ከፕሬዝዳንት ዜሌንስኪ የመጣ ነው ይላሉ።

ሹመቱ ራሳቸውን ጄኔራሉን ጨምሮ በርካቶችን ያስገረመ ነበር፤ ምክንያቱም በርካታ የሥልጣን እርከኖችን በመሻገራቸው ነው።

ጄኔራል ዛሉዝህኒ ቀድሞውንም ራዕይ ያላቸው እና ዘመናዊ የጦር አዛዥ በመሆናቸው ነው የሚታወቁት።

ከበታቾቻው ጋር መቀለድ የሚወዱ እና የተግባር ሰው ናቸው።

በተሾሙ በሰባት ወራት ውስጥ ነው የዩክሬንን የመከላከል ዘመቻ መምራት የጀመሩት።

ሩሲያ ወረራዋን ስትከፍት ኪዬቭን ትቆጣጠራለች የሚል ስጋት የነበረ ቢሆንም፣ ባለፈው ዓመት የካቲት ወር ላይ ሩሲያ አቅዳው የነበረው የዩክሬን ዋና ከተማ ኪዬቭን በሦስት ቀናት ውስጥ መቆጣጠር እንደማትችል እርግጥ ሆነ።

ሁኔታዎች የጨለሙ ቢመስሉም የዩክሬን ባለሥልጣናት ሕዝቡ እንዳይደናገጥ ጥሪ እያደረጉ ነበር።

የሩሲያ ወታደሮች በሰሜን፣ በምሥራቅ እና በደቡብ በኩል በመግፋት ዋና ከተማዋ ላይ ትልቅ ስጋት ፈጠሩ።

በዩክሬን ከፍተኛ ባለሥልጣናት ዘንድም ኪዬቭ በሩሲያ እጅ እንዳትገባ ለማድረግም በአቅራቢያዋ ያሉትን ድልድዮች እናፍርስ የሚል ሃሳብ መንሸራሸር ጀመረ።

ይህንንም ዕቅዳቸውን ጄኔራል ቫለሪ ዛሉዝህኒንም ደውለው አማከሯቸው። የጄኔራሉ መልስ ግን “በፍጹም ይህንን አናደርግም” የሚል ነበር።

የዩክሬን ጦር ዋና አዛዥ ጄነራል ቫለሪ ዛሉዝህኒ ከፕሬዚዳንት ቮሊድሚር ዘለንስኪ ጋር

የፎቶው ባለመብት, Office of The president of Ukraine

የምስሉ መግለጫ, የዩክሬን ጦር ዋና አዛዥ ጄነራል ቫለሪ ዛሉዝህኒ ከፕሬዚዳንት ቮሊድሚር ዘለንስኪ ጋር
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

“ሕዝባችን እና ጦሩንም መክዳት ነው” በማለት ሠራዊታቸው ድልድዮቹን ፈጽሞ እንደማያፈርስ አስታወቁ።

ቢቢሲ ጄኔራሉ ይህንን ሃሳብ መቃወማቸውን በተመለከተ ከሌሎች ሁለት ምንጮች ሰምቷል።

የጄኔራሉ ሌሎች ቁልፍ ውሳኔዎችን ተከትሎም ከሚያዝያ 2022 (እአአ) በኋላ የሩሲያ ጦር ከመዲናዋ ወደ ሰሜን እና ምሥራቅ ርቆ መገፋት ተቻለ።

የጄኔራሉ ወላጆች የቀድሞዋ ሶቪዬት ኅብረት መንግሥት መሥሪያ ቤት ሠራተኞች ነበሩ።

ጄኔራል ዛሉዝህኒ በአንድ ወቅትም ከሶቭዬት ጦር ሠራዊት ጥብቅ የሥልጣን ተዋረድን ራሳቸውን ማራቅ እንደሚፈልጉ ተናግረዋል።

በአውሮፓውያኑ 1990ዎቹ አጋማሽም ጄኔራሉ ወደ ወታደራዊ ትምህርት ቤት ሲገቡ ዩክሬን ነጻ አገር ነበረች።

በወታደራዊ ኮሌጅ ውስጥ እያሉም የመማሪያ መጻህፍቶቻቸው በሶቪዬት ዘመን የተጻፉ ቢሆኑም፣ ጦርነትን ያውቁታል።

በአውሮፓውያኑ 2014 በዩክሬን ምሥራቃዊ ግዛት በሚንቀሳቀሱ እና በሩሲያ ከሚደገፉ ተገንጣዮች ጋር እየተካሄደ በነበረውም ጦርነት ምክትል አዛዥ ሆነው ተሾሙ።

ቢቢሲ ያናገራቸው የሥራ ባልደረቦቻቸውም በአመራርነት ከመጡበት ወቅት ጀምሮ ከበታቾቻቸው ጋር የመተማመን ግንኙነትን መመሥረት እንዲሁም ትዕዛዞችን እንዲያስተላልፉም ሥራ የመስጠት ልምድም እንደነበራቸው ይገልጻሉ።

ሩሲያ ወረራ በፈጸመችበት ወቅት በመጀመሪያዎቹ ቀናት ከጎናቸው የነበረችው የጄኔራል ዛሉዝህኒ የቀድሞ ረዳት ሉድሚላ ዶልሆኖቭስካ እንቅልፍ ያጡበት ወቅት ነው ትላለች። በጦሩ ግንባር ካሉ ወታደሮችም የማያቋርጥ ግንኙነትም ማድረግ ዋነኛ ሥራቸው እንደነበር ታስታውሳለች።

“ከጄኔራሎቻቸው ጋር ተደጋጋሚ ስልክ ቢያወሩም ንግግሮቻቸው ሁልጊዜ የተመጠነ እና እርጋታ የተሞላበት ነበረ” ትላለች።

ተንታኞች እንደሚናገሩት በጦር ሜዳ ላይ የጦር መኮንኖች ውሳኔን ማስተላለፍ መቻላቸው እና ሁኔታውንም እያዩ መቀያየራቸው ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ነው። የሩሲያ ጦር በበኩሉ ውሳኔዎችን የሚጠብቀው ከከፍተኛ የጦር ኃላፊዎች ብቻ መሆኑ ጎድቶታል ይላሉ።

አንዳንድ የዩክሬን ጦር ሠራዊት ምንጮች እንደሚሉት ለዩክሬን ስኬት ዋነኞቹ በጦር ግንባር ላይ ያሉት አዛዦች ናቸው እስከማለት ይደርሳሉ። ጄኔራል ዛሉዝህኒ በበኩላቸው እነዚህ መኮንኖች ውሳኔ እንዲያስተላልፉ ነጻነትን ሙሉ በሙሉ በመስጠት ሊመሰገኑ ይገባቸዋል ይላሉ።

ጦርነቱ በተጀመረበት ወቅት ፕሬዝዳንት ዜሌንስኪ በምሽት በሚያሰጧቸው መግለጫዎች የሕዝቡን ሞራል ከፍ በማድረግ ቁልፍ ሚና ተጫውተዋል።

ፕሬዝዳንቱ በጠንካራ አስተዳደራቸው የውጭ አጋሮች ገንዘብ እና ወታደራዊ ድጋፍ እንዲያደርጉላቸው ከፍተኛ ጫና አሳድረዋል።

የጄኔራል ዛሉዝህኒ ዋነኛ ትኩረት በወታደራዊ ስትራቴጂ የበላይነትን መጎናጸፍ ነበር።

የዩክሬን ወታደሮች በምሥራቅ እና በደቡብ የሚገኙትን ሰፊ ግዛቶች ነጻ አውጥተዋል።

ይህንንም ተከትሎ የጦር አዛዡ በአደባባይ ልታይ ልታይ ባይሉም አልፎ ተርፎም ለቃለ መጠይቅ ባይስማሙም ብሔራዊ ጀግና ተብለዋል።

ስማቸው የጀግንነት እና ቆራጥነት ተምሳሌት ሆኗል። የዩክሬን ተረቶች እና ምሳሌያዊ አነጋገሮችም ማጣፈጫ ሆነዋል።

ከእነዚህም መካከል “ጄኔራል ዛሉዝህኒ አንድ መብራት ያልበራ ክፍል ውስጥ ሲገቡ መብራቱን አያበሩም ሆኖም ጨለማውን ያጠፋሉ” ተብሎላቸዋል።

ተወዳጅነታቸውም ከፕሬዝዳንት ዜሌንስኪ ጋር ፍጹም አንድ ሆኗል።

የሴራ ተንታኞችም ይህንን በማየት በጄኔራሉ እና በፕሬዝዳንቱ መካከል ጠብ ተፈጥሮ ሊሆን ይችላል የሚል ግምት ይሰጣሉ።

ፕሬዝዳንት ዜሌንስኪ ጄኔራሉን ሊተኳቸው ይችላሉ የሚሉ፣ እንዲሁም ጄኔራል ዛሉዝህኒ የፕሬዝዳንቱን የፖለቲካ አመራር እየተገዳደሩ ነው የሚሉ ወሬዎችም ይነዛሉ።

ነገር ግን እስካሁን ድረስ ሁለቱም አልተከሰቱም።

የፕሬዝዳንቱ ቅርብ ሰው ለቢቢሲ እንደተናገሩት “ፕሬዚዳንት ዜሌንስኪ በአሁኑ ወቅት ለአገራቸው ከአጋሮቻቸው ወታደራዊ ድጋፍ ለማግኘት ሙሉ በሙሉ የተጠመዱ ሲሆን፣ ለእንዲህ አይነት ቅናት ጊዜ የላቸውም” ብለዋል።

ጄኔራሉ እና ፕሬዝዳንቱ በየፊናቸው እያከናወኑት ባለው ተግባር በጣም የተደሰቱ ይመስላል።

ጄኔራሉ ከታይም መጽሄት ጋር ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር ላይ ባደረጉት ቆይታ፣ ወታደራዊ ስትራቴጂን በተመለከተ ጥቃቅን ዝርዝሮች ለፕሬዝዳንቱ መንገር እንደማይጠበቅባቸው ተናግረዋል።

"ስለ መድኃኒት ወይም ስለ ድልድይ ግንባታ ማወቅ ከሚያስፈልገው በላይ ወታደራዊ ጉዳዮችን መረዳት አያስፈልገውም" ብለዋል።

የፖለቲካ ተንታኞች እና የማኅበራዊ ሳይንስ አጥኚዎች የጄኔራሉ ተወዳጅነት የሚያስገርም አይደለም ይላሉ። በአንድ በኩል አሁን ባለው ሁኔታ ዩክሬናውያን ሞራላቸውን ከፍ የሚያደርጉበት መንገድ መፈለጋቸው ነው። በሌላ በኩል ደግሞ ጄኔራሉ ከማኅበረሰቡ ጋር ያላቸው ጥብቅ ቀረቤታ ነው።

በአንድ ወቅት ወደ ባኽሙት የጦር ግንባር በመላኩ ምክንያት ሠርጉን ለማዘግየት የተገደደ ወታደር ሠርግ ላይ መገኘታቸው ሰውን አስደምሟል።

የዩክሬን ጥቃቶች እየተጠናከሩ ሲሄዱም የሩሲያ ወታደራዊ ጦማሪዎች ጄኔራሉ ቆስለዋል አልፎ ተርፎም ተገድለዋል የሚሉ ወሬዎችን ያሰራጩ ነበር።

ይህንንም ጉዳይ የሩሲያ የውጭ የደኅንነት እና ስለላ ኃላፊ ሰርጌይ ናሪሽኪን የተቀበሉት ይመስል ነበር። “የዩክሬን የጦር አዛዥ የጤና ሁኔታን በተመለከተ እያንዳንዷ መረጃ አለችን፣ ነገር ግን ይፋ አናደርግም” ብለው ነበር።

የጄኔራሉ ቅርብ ሰው የሆኑት ኮሎኔል አናቶሊ ሽቴፋን ይህንን ወሬ “የሩሲያ ፕሮፓጋንዳ እብደት” ብለውታል።

ሆኖም ይህ ወሬ ዩክሬናውያንን ማስጨነቁ አልቀረም።

በቅርቡም የዩክሬን መከላከያ ሚኒስቴር ጄኔራል ዛሉዝህኒ በኪዬቭ ወታደራዊ ሥነ ሥርዓት ላይ ሲሳተፉ የሚያሳዩ በርካታ ፎቶዎችን አውጥቷል።

የዩክሬን ጦር ዋና አዛዥ ጄነራል ቫለሪ ዛሉዝህኒ ከኮሎኔል አናቶሊ ሽቴፋን ጋር

የፎቶው ባለመብት, Col Anatoly Shtefan

የምስሉ መግለጫ, የዩክሬን ጦር ዋና አዛዥ ጄኔራል ቫለሪ ዛሉዝህኒ ከኮሎኔል አናቶሊ ሽቴፋን ጋር

በአሁኑ ወቅት ጄኔራሉ በዩክሬን ሕዝብ ዘንድ ያላቸው የጀግንነት ቦታ አስተማማኝ ነው።

ነገር ግን የዩክሬንን ዕጣ ፈንታን በርካቶች ለጄኔራሉ ማሸከማቸውን ተከትሎ መጪው ጊዜ የተወሳሳበ ሊሆን ይችላል።

ዩክሬን ያደረገችው መከላከል በመጨረሻ ቢሳካ፣ የአገሪቱ መጻኢ ዕጣ ፈንታ ፈታኝ ሊሆን እንደሚችል የማኅበረሰብ አጥኝኚው ኦሌክሲ አንቲፖቪች ያስጠነቅቃሉ። እናም በባለሙያው ግምት ጄኔራሉ ከፖለቲካው መራቅን ይመርጡ ይሆናል ይላሉ።

“ከጦርነቱ በኋላ ዩክሬን ሙሉ በሙሉ ምጣኔ ሃብቷ መንኮታኮት ወይንም ከፍተኛ ቀውስ ሊገጥማት ይችላል። ይህ ደግሞ የጦርነቱ ጠባሳ ነው” ይላሉ።

የፖለቲካ ተንታኙ ሚኮላ ዳቪዲዩክ በበኩላቸው የጦር አዛዡ ጄኔራል ወደ ፖለቲካ ቢገቡ ሊሳካላቸው እንደሚችሉ ያምናሉ።

“ፕሬዝዳንት ዜሌንስኪ ሕዝባቸውን ያልተዉ መሪ ቢሆኑም፣ ጄኔራል ዛሉዝህኒ የተከላከሉላቸው እና የታገሉላቸው መሪ ናቸው። ይህ ሁኔታ በሕብረተሰባቸው ዘንድ ሌላ ስፍራ አስገኝቶላቸዋል” ይላሉ።

ቢቢሲ ጄኔራል ዛሉዝህኒን ለቃለ ምልልስ ቢጠይቃቸውም ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል።