የአፍሪካ መሪዎች በዩክሬን እና በሩሲያ መካከል ሰላም እንዲመጣ ያስችሉ ይሆን?

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ለአስራ ስምንት ወራት የዘለቀውን የዩክሬን እና የሩሲያን ጦርነት በንግግር እንዲቋጭ ለማድረግ ሰባት የአፍሪካ መሪዎች ወደ ሁለቱ አገራት አቅንተዋል።
በደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት የሚመራው የሰላም ተልዕካን ቡድን በአህጉሪቱ የምጣኔ ሃብት ቀውስ ያስከተለው ይህ ጦርነት እንዲያከትም የሁለቱን አገራት መሪዎችን የማግባባት ሥራን ጀምሯል።
የደቡብ አፍሪካ፣ የግብፅ፣ የሴኔጋል፣ የኮንጎ-ብራዛቪል፣ የኮሞሮስ፣ የዛምቢያ እና የኡጋንዳ ልዑካንን ያካተተው ይህ የሰላም ቡድን፣ አርብ ዕለት ከዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሌድሚር ዜሌንስኪ ጋር መክረዋል።
ዛሬ ቅዳሜ ሰኔ 10/2015 ዓ.ም ደግሞ ወደ ሩሲያ በማቅናትም ከፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር ይገናኛል።
የሰላም ልዑካኑ ቡድን ይህንን ወቅት መምረጣቸው ትንሽ ግርታን ፈጥሯል። ጉብኝቱ ዩክሬን ለረጅም ጊዜ ስትዘጋጅበት የነበረውን የመልሶ ማጥቃት ዘመቻን በጀመረችበት እና ውጊያው እየተጠናከረ መምጣቱን ተከትሎ መሆኑ ነው።
ታዲያ ይህ የመሪዎቹ ተልዕኮ ምን ሊያሳካ ይችላል?
የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ ሁለቱን አገራት ለማሸማገል እንደሚፈልጉ ከሳምንታት በፊት ሲናገሩ መደራደሪያ ነጥቦችንም ሆነ ስለ ጊዜ ገደብ አላወሩም።
ሁለቱን መሪዎች የማሸማገል ፍላጎት እንዳለ የተገለጸው ከደቡብ አፍሪካ ብቻ አይደለም፣ ከዚህ ቀደምም ከቻይና እና ቱርክ እንዲሁም ከሮማው ካቶሊክ ሊቀ ጳጳስ በኩልም ሲናገር ተደምጧል።
ሆኖም የአፍሪካ የልዑካን ቡድን ሁኔታውን ገፍቶበት ሁለቱን መሪዎች ማግኘቱ ጥያቄ ማጫሩ አልቀረም።
“ለዚህ ጣልቃ ገብነት ገፊው መንስኤ ምንድን ነው?” የፖለቲካ ተንታኙ እና የቀድሞ ዲፕሎማት ደቡብ አፍሪካዊው ኪንግስሌይ ማኩቤላ ይጠይቃሉ።
“ግልጽ አይደለም፤ የአፍሪካ መሪዎች ለይስሙላ እና ለፎቶ የሚያደርጉት ሽር ጉድ ይሆን?” ሌላው የዲፕሎማቱ ጥያቄ ነው።
የመሪዎቹ ተልዕኮ ያልተጠበቀ ነው። አፍሪካውያን ጦርነቱ ከተከሰተ ጀምሮ ገለልተኛ አቋም አለን ሲሉ በተደጋጋሚ ቢደመጡም፣ ጦርነቱን የሚያዩት በሩሲያ እና በምዕራባውያን መካከል የነበረው ፍጥጫ ቅጥያ መሆኑን ነው።

የፎቶው ባለመብት, South African Presidency
አፍሪካውያኑ መሪዎች ከአህጉራቸው ውጭ በዲፕሎማሲያዊ ጣልቃ ሲገቡም የመጀመሪያቸው ነው።
“አፍሪካ የተባበሩት መንግሥታትን ጨምሮ ሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማት ውስጥ ያላት ተደማጭነት እንዲጨምር እየጠየቀች ባለችበት ወቅት መሆኑ፣ ይህ ጅማሮ እንደ መልካም ነው መታየት ያለበት” ይላሉ በዓለም አቀፉ የክራይሲስ ግሩፕ የአፍሪካ ዳይሬክተር ሙሪቲ ሙቲጋ።
ለዚህ ውይይትም ሁኔታውን በማመቻቸት የአንበሳውን ድርሻ የያዙት ዢን ኢቭስ ኦሊቪየር የሚባሉ ግለሰብ ናቸው።
መቀመጫውን በዩናይትድ ኪንግደም ያደረገ ብራዛቪል ፋውንዴሽን የተሰኘ ተቋም ይመራሉ።
ተቋሙ በዋነኝነት ትኩረቱን በአፍሪካ ሰላም እና ልማት ላይ አድርጓል።
ዢን ከኮንጎ ብራዛቪል አምባገነን መሪ ጋር ረዘም ያለ ጊዜ የቆየ ግንኙትም በመመሥረታቸው አወዛጋቢ አድርጓቸዋል።
ዢን የመሪዎቹ ጉብኝት ይፋ መሆኑን ተከትሎ ስለ ጉዟቸው አስተያየት ከመስጠት ተቆጥበዋል።
ነገር ግን ቀደም ሲል ለህትመት በበቁ ቃለ ምልልሶቻቸው የመሪዎቹ ተልዕኮ ምን ሊሆን እንደሚችል አስቀምጠዋል።
ጦርነቱን በሰላም ከመቋጨት ይልቅ ሁለቱ መሪዎች ተቀራርበው ውይይት እንዲጀምሩ ማስቻል ቅድሚያ የሚሰጡት ነው ብለዋል።
ወታደራዊውን ሁኔታ በቀጥታ በማይነኩ ጉዳዮች ላይ ውይይት እንዲጀመር እና ከዚያም ማስቀጠል መቻል ነው ሲሉም ተናግረዋል።
መሪዎቹ ሊያነሷቸው ከሚችሉ ጉዳዮች አንዱ አገራቱ የጦር እስረኞችን መለዋወጥ ይሆናል።
ሌላኛው አፍሪካን በቀጥታ የሚመለከታትን እህል እና ማዳበሪያ ላይ ለተከሰተው ቀውስ መፍትሄዎችን ለማምጣት መሞከር ነው።
ጦርነቱን ተከትሎ የዩክሬን እህል እና የሩሲያ የማዳበሪያ አቅርቦት እጅጉኑ በመገደብ ዓለም አቀፍ የምግብ ዋስትናን የከፋ አድርጎታል። ከሁለቱ አገራት በምታመጣቸው ምርቶች ላይ ጥገኛ ለሆነችው አፍሪካ፣ በተለይ ጉዳቱ የከፋ ነው።
ዢን እንደሚሉት የአፍሪካ መሪዎች ዩክሬን በጥቁር ባሕር በኩል እህል እንድትልክ ደኅንነቱን የማስጠበቅ ስምምነትን ሩሲያ እንድታራዝመው ማሳመን የዚህ ተልዕኮ አንዱ ተግባር ይሆናል።
እንዲሁም በዩክሬን ወደቦች ላይ ለሚያልፈው የሩሲያ ማዳበሪያ ላይ ያሉ የውጭ ንግድ ገደቦች እንዲቃለሉም መንገድ ለመፈለግ ከዩክሬን ባለሥልጣናት ጋር እንደሚነጋገሩ ዢን ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅት የአፍሪካ መሪዎች “ሁለቱ ተፋላሚ ወገኖች ስምምነት ላይ እንዲደደርሱ ተጨባጭ የሆኑ የድርድር ሃሳቦችን ለማቅረብ እንደሚፈልጉ ጠቋሚ መረጃዎች አሉ” ይላሉ ሙቲጋ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አሜሪካ በደቡብ አፍሪካ ላይ እያሳደረችው ያለው ጫና
የሰላም ተልዕኮውን እየመሩ ያሉት ሰባቱ አፍሪካውያን መሪዎች ሲመረጡ በዘፈቀደ አይደለም። በዩክሬን እና በሩሲያ መካከል እየተደረገ ያለውን ጦርነት በተለያየ መንገድ የሚመለከቱ እና ሚዛናዊም ለማድረግ ተሞክሯል።
ልዑካን ቡድኑ አራት ፕሬዝዳንቶች፣ የግብፅ ጠቅላይ ሚኒስትር እና የኡጋንዳ እና የኮንጎ ብራዛቪል ተወካዮችን ያካተተ ነው።
ደቡብ አፍሪካ እና ኡጋንዳ ድጋፋቸው ለሩሲያ አዘንብሏል የተባሉ ሲሆን፣ ዛምቢያ እና ኮሞሮስ ውግንናቸው ከምዕራቡ ዓለም ጋር ነው።
ግብፅ፣ ሴኔጋል እና ኮንጎ ብራዛቪል ደግሞ ገለልተኛ አቋም እንዳላቸው ነው የሚታሰበው።
ነገር ግን በቅርብ ጊዜ በደቡብ አፍሪካ የተከሰቱ ጉዳዮች፣ ሁኔታዎች መልካቸውን እንዲቀይሩ እያደረጉ ነው ተብሏል። ደቡብ አፍሪካ ለሩሲያ የጦር መሳሪያ ድጋፍ እያደረገች ነው በሚልም አሜሪካ ውግዘቷን አቅርባለች።
ከሳምንታት በፊት ከደቡብ አፍሪካዋ ከተማ ኬፕታውን የጦር መሳሪያ የጫነች መርከብ ወደ ሩሲያ አቅንታለች የተባለ ሲሆን፣ ሆኖም ፕሬዝዳንት ራማፎሳ በአገራቸው ላይ የቀረበውን ክስ ውድቅ አድርገውታል።
የባይደን አስተዳደር የደቡብ አፍሪካን መንግሥት ምርመራ ውጤት እየጠበቀ ይገኛል። ነገር ግን ከሁለቱም ፓርቲዎች የተውጣጡ የአሜሪካ የምክር ቤት አባላት ቡድን ደቡብ አፍሪካን ከአንዳንድ ጥቅሞች በማገድ አሜሪካ ልትቀጣት ይገባል ይላሉ።
“ተልዕኮው ደቡብ አፍሪካ ያላትን አቋም እንድታሳይ ከመፈለግ ጋር የተያያዘ ይመስለኛል” ሲሉ በለንደን የቻተም ሐውስ የአፍሪካ ፕሮግራም ዳይሬክተር የሆኑት ዶክተር አሌክስ ቫይንስ ይናገራሉ።
አሜሪካውያን ሩሲያ በዩክሬን ላይ ወረራ በፈጸመችበት ወቅት አፍሪካ ለዩክሬን ወገንተኝነትን እንድታሳይ ያደርጉት የነበረውን ጫና አቁመውታል ይላሉ።
በርካታ የአፍሪካ መንግሥታት የገለልተኝነት አቋምን የመረጡ ሲሆን፣ ይህም ከቀዝቃዛው ጦርነት ታሪክ ጋር እንደሚገናኝ እና ሩሲያን መደገፍ ማለት እንዳልሆነ አሜሪካ ትረዳለች በማለትም ይገልጻሉ።
በአሁኑ ወቅት የአሜሪካ መንግሥት ያለው አቋም “እውነተኛ የሆነ ገለልተኛነት” አገራት እንዲኖራቸው ይፈልጋል ይላሉ።
እናም “በአሁኑ ወቅት በደቡብ አፍሪካ ላይ ያለው ጫና እውነተኛ ገለልተኛ መሆኗን ማሳየት ነው” በማለትም ያስረዳሉ።
የአፍሪካ አገራት መሪዎችን ተልዕኮ እና ጉብኝት ቅርጽ በማስያዝ ረገድ ፕሬዝዳንት ራማፎሳ ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል።
ከጉዞውም በፊት ራማፎሳ ከፕሬዝዳንት ፑቲን እና ከፕሬዝዳንት ዜሌንስኪ ጋር እንዲሁም ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ ጋር በስልክ ተወያይተዋል።
ምንም እንኳን ሩሲያም ሆነ ዩክሬን ለሰላም ድርድር ምንም ፍላጎት ባያሳዩም፣ ሁለቱም ወገኖች የአፍሪካ ልዑካን ቡድን ጉብኝትን ይፈልጉታል።
ሩሲያ በምዕራባውያኑ የሚደርስባትን ጫና ለመቋቋም አጋር ፍለጋ አፍሪካን መርጣለች። ሩሲያ ከአህጉሪቱ ጋር ያላትን መልካም ግንኙት ማሳያ ነው የተባለው በሚቀጥለው ወር በሴንት ፒተርስበርግ የሚካሄደው የሩሲያ - አፍሪካ የመሪዎች ጉባዔ ነው።
ዩክሬን በበኩሏ እንደተቀደመች በምታውቀው አፍሪካን በዲፕሎማሲ መወዳጀት ረገድ እየጣረች ትገኛለች።
በቅርቡም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯን ወደ አህጉሪቱ በመላክ ድጋፍ እንዲሰጧት ጠይቃለች።
“ምናልባትም የአፍሪካ አሸማጋዮች በሩስያ - አፍሪካ ጉባዔ ላይ እንዳይገኙ ለማሳመን ዩክሬናውያን ይሞክሩ ይሆናል” ይላሉ ዶክተር ማክሁቤላ።
“ሩሲያ ከዓለም የተገለለች እንዳልሆነች ማሳየት ትፈልጋለች። ሁለቱም አገራት ጥቅሞቻቸውን በማስላት አጋሮችን ይፈልጋሉ። ለዚያም ነው የአፍሪካ መሪዎች ወደ ሴንት ፒተርስበርግ ሄደው ጉባኤውን መካፈላቸው አጣብቂኝ ውስጥ የሚከታቸው” በማለት ያክላሉ።
ተንታኞች ጉባዔውን የአፍሪካ መሪዎች ከሩሲያ ጋር ያላቸውን ግንኙነት የሚያሳይ ወሳኝ ምዕራፍ አድርገው ይመለከቱታል። ነገር ግን ግንኙነቱ የርዕዮተ ዓለምም እንዳልሆነም ይናገራሉ።
“አፍሪካውያንም የራሳቸውን ጥቅም ያሰላሉ” የሚሉት ዶክተር አሌክስ በቅርቡ ያናገሯቸው የሞዛምቢክ የቀድሞ የሽምቅ ተዋጊዎች ከፍተኛ ስጋት “በዚህ ሩቅ የአውሮፓ ጦርነት” ምክንያት የተከሰተው የኑሮ ውድነት እና የዋጋ ግሽበት” እንደሆነ ያስረዳሉ።
“የአፍሪካውያን ጦርነት አይደለም” ይላሉ ዶክተር አሌክስ።
የአፍሪካ አሸማጋዮች ሁለቱን ተፋላሚ ወገኖች ወደ ሰላም ጠረጴዛ ማምጣት ከቻሉ ሊያነሷቸው ከሚችሏቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ በጦርነቱ ምክንያት የተከሰተው የምጣኔ ሃብት ቀውስ ሊሆን እንደሚችልም ሙቲጋ ያስረዳሉ።












