ደቡብ አፍሪካ እና ሩሲያ ወታደራዊ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር ተስማሙ

የደቡብ አፍሪካ ወታደር

የፎቶው ባለመብት, Gallo Images

ሩሲያና ደቡብ አፍሪካ ወታደራዊ ትብብራቸውን ለማጠናከር ስምምነት ላይ መድረሳቸውን የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር አስታወቀ።

ከደቡብ አፍሪካ እና ከሩሲያ የተውጣጡ ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖች ከሰሞኑ በሞስኮ ተገኝተው በተጨማሪም የሰራዊቶታቸውን የውጊያ ዝግጁነት ለማሳደግ መስማማታቸውንም የሩሲያ መንግሥት ሚዲያ የሆነው ታስ የዜና ወኪል ዘግቧል።

ይህ በከፍተኛ የወታደራዊ መኮንንኖች ደረጃ የተደረሰው ስምምነት ከሰሞኑ በፕሪቶሪያ ተቀማጭነታቸውን ያደረጉት የአሜሪካ አምባሳደር ሩበን ብሪጌቲ ደቡብ አፍሪካ ለሩሲያ የጦር መሳሪያዎችን ታቀርባለች በማለት ከከሰሱ ከቀናት በኋላ ነው።

ደቡብ አፍሪካ ከዚህ ቀደም በዩክሬን እየተደረገ ባለው ጦርነት ገለልተኛነቷን ስትገልጽ ቆይታለች።

የደቡብ አፍሪካ የምድር ጦር አዛዥ ሌተናንት ጄነራል ላውረንስ ምባታ ከሩሲያ አቻቻው ኦሌግ ሳሊዩኮቭ ጋር በሞስኮ ያደረጉትን ውይይት መምራታቸውን ታስ የሩሲያን መከላከያ ሚኒስቴር ዋቢ አድርጎ ዘግቧል።

“ሁለቱ አገራት በወታደራዊ ትብብር እንዲሁም አገራቱ በውጊያ ወቅት ዝግጁነትን ለማሳደግ ተስማምተዋል”

“በወታደራዊ አዛዦቹ መካከል የተደረገው ውይይት በምድር ጦራቸው መካከል ያለውን ትብብር በተለያዩ አካባቢዎች በበለጠ ሁኔታ ለማስፋፋት ስምምነት ላይ ደርሰዋል” ሲል መከላከያ ሚኒስቴር መግለጫ አውጥቷል።

ባለፈው ሳምንት የአሜሪካው አምባሳደር ብሪጌቲ ከወራት በፊት የሩሲያ መርከብ በኬፕታውን ከሚገኘው የባህር ኃይል ጦር ሰፈር መሳሪያዎችን ጭና መውጣቷን እርግጠኛ ነኝ ማለታቸውን ተከትሎ ደቡብ አፍሪካ የዲፕሎማሲያዊ ውዝግብ ውስጥ ገብታ ነበር።

ደቡብ አፍሪካ ለሩሲያ የጦር መሳሪያ ሽያጭ ሬከርድ እንደሌላት ገልጻ ነገር ግን ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎሳ አሜሪካ ያቀረበችው ውንጀላ እንዲጣራ ምርመራ እንዲደረግ ትዕዛዝ አስተላልፈው ነበር።

“ደቡብ አፍሪካ በዩክሬን ጦርነት እንድትሳተፍ ከፍተኛ ጫና እያስተናገደች ነው” በማለት ፕሬዚዳንት ራማፎሳ በአንድ ጋዜጣ ላይ ጽሁፋቸውን አስፍረዋል።

አክለውም “ይህ በሩሲያ እና በምዕራቡ ዓለም መካከል የሚደረግ ፉክክር ነው። በዚህ ተሳታፊ አንሆንም” ብለዋል።

የደቡብ አፍሪካ መከላከያ ከፍተኛ የጦር መኮንኖቹ በሞስኮ እንደሚገኙ አረጋግጧል።

“ደቡብ አፍሪካ በአህጉሪቱ ካሉና ከተለያዩ አገራት ጋር ወታደራዊ የሁለትዮሽ ግንኙነት እንዳላት መታወቅ አለበት” ሲል የደቡብ አፍሪካ መከላከያ በመግለጫው ጠቅሶ ወደ ሩሲያ የተደረገው ጉዞ አስቀድሞ የታቀደ መሆኑንም አስታውቋል።

ዋናው ተቃዋሚ ዴሞክራቲክ አሊያንስ ጉብኝቱን የደቡብ አፍሪካ መንግሥት ለሩሲያ ያለውን ድጋፍ “ሳይሸማቀቅ” ያሳየበት የቅርብ ጊዜ ምሳሌ ነው ብሏል።