ጄኔራል አል ቡርሐን የተቀናቃኛቸውን የጄኔራል ዳጋሎ ኃይልን የባንክ አካውንቶች አገዱ

ጄኔራል አብደል ፋታህ አል-ቡርሐን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ጄኔራል አብደል ፋታህ አል-ቡርሐን

የሱዳን ጦር ሠራዊት አዛዥ የሆኑት ጄኔራል አብደል ፋታህ አል-ቡርሐን የተቀናቃኛቸውን የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ እና በቡድኑ ስር ያሉ ተቋማት የባንክ አካውንቶች እንዳይንቀሳቀሱ አዘዙ።

ጄኔራል ቡርሐን እሁድ ዕለት ይፋ ካደረጓቸው በርካታ ትዕዛዞች መካከል፣ ከፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ጋር ግንኙነት አሏቸው የሚባሉ አራት የጦር ጄኔራሎችን በጡረታ አሰናብተዋል።

ከእነዚህ የጦር መኮንኖች መካከልም የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ (አርኤስኤፍ) አዛዥ የጄኔራል መሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ ዘመድ የሆኑት ብርጋዴር ጄኔራል ኦማር ሐምዳን አሕመድ ይገኙበታል ተብሏል።

በጄኔራል አል ቡርሐን በጡረታ የተሰናበቱት የጦር መኮንን በአሁኑ ወቅት በሱዳን ውስጥ የተከሰተውን ጦርነት ለማስቆም በሁለቱ ጄኔራሎች መካከል እየተካሄደ ባለው ድርድር ላይ የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉን ተደራዳሪዎች በመምራት እየተሳተፉ ነው።

ድርድሩ በአሜሪካ እና በሳዑዲ አረቢያ አሸማጋይነት በወደብ ከተመዋ ጄዳ ውስጥ እየተካሄደ ሲሆን፣ ባለፈው ሳምንት ሁለቱ ወገኖች ሰላማዊ ሰዎችን እና የእርዳታ አቅርቦቶችን ከጥቃት ለመጠበቅ ተስማምተዋል።

ጄኔራል አል ቡርሐን በተጨማሪም የሱዳን ብሔራዊ ባንክ ገዢ የሆኑትን ሁሴን ያሂያ ጃንኮልን አንስተው ቦራይ ኤል-ሲዲቅን በቦታቸው ተክተዋል።

ነገር ግን የሱዳን ጦር ሠራዊት አዛዥ አል ቡርሐን የብሔራዊ ብንኩ ገዢን ከኃላፊነታቸው ለምን እንዳነሱ ምክንያት አልሰጡም።

የሱዳን የሽግግር ሉዓላዊ ምክር ቤትን በሊቀ መንበርንት እና በምክትልነት ሲመሩ የነበሩት ጄኔራል አል ቡርሐን እና ጄኔራል ዳጋሎ የአገሪቱን የመሪነት መንበር በበላይነት ለመቆጣጠር በፈጠሩት ሽኩቻ ነበር ወታደራዊ ግጭት ውስጥ የገቡት።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ከተጀመረ አንድ ወር የሆነውን የሱዳን ጦርነትን ለማስቆም በሱዳን ሠራዊት እና በፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች መሪዎች መካከል ከሳምንት በፊት ሳዑዲ አረቢያ ውስጥ መካሄድ የጀመረው ድርድር የሚፈለገውን ውጤት አስካሁን አላስገኘም።

አንድ አሜሪካዊ ዲፕሎማት ድርድሩ እጅግ አስቸጋሪ እንደሆነ እና ሁለቱ ወገኖች ከስምምነት ላይ ለመድረስ ከሚያስችል መቀራረብ ላይ አለመድረሳቸውን አሁንም “ተራርቀው ነው ያሉት” ሲሉ ገልጸውታል።

ሁለቱ ኃይሎች ባለፈው ሳምንት በደረሱት ስምምነት መሠረት የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት በችግር ላይ ላሉ ሰዎች እንዲደርስ እና ውጊያን በመሸሽ ከአካባቢያቸው ለቀው ለመውጣት የሚፈልጉ ሰዎች እንዲንቀሳቀሱ ፈቅደዋል።

የአገሪቱ ጦር ሠራዊት አዛዥ የጄኔራል አብደፍ ፋታህ አል ቡርሐን እና የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ አዛዥ የጄኔራል መሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ ተወካዮች አሁንም ድርድራቸውን መቀጠላቸው ተነግሯል።

ሁለቱ ወገኖች በዋናነት ለ10 ቀናት የሚቆይ ተኩስ አቁም ለማድረግ እና ተፈጸሚነቱን የመቆጣጠሪ ዘዴ ላይ እንዲስማሙ አደራዳሪዎቹ ግፊት እያደረጉ ነው።

አሁን የአገሪቱ ጦር አዛዥ የወሰዱት የባንክ አካውንቶችን የማገድ እና ከጄኔራል ዳጋሎ ጋር ቅርበት አላቸው የተባሉ የጦት መኮንኖችን ጡረታ ማስወጣት በሁለቱ ወገኖች መካከል በሚደረገው ድርድር ላይ እንቅፋት እንዳይፈጥር ተሰግቷል።

ተፋላሚዎቹ ወገኖች ውጊያው ከተጀመረ በኋላ በነበሩት ሳምንታት ለሦስት ጊዜ ያህል ለተለያዩ ቀናት ተኩስ ለማቆም ስምምነት ላይ ደርሰው የነበረ ቢሆንም ሳይከበር ውጊያው ቀጥሏል።

አሁን ውጊያውን ለመግታት ለአጭር ጊዜ የተኩስ አቁም እንዲደረስ እየተደረገ ያለው ግፊት ከተሳካ፣ በዘላቂነት ግጭቱን በማስቆም በአገሪቱ ውስጥ ለተፈጠረው ቀውስ መፍትሄ ለመፈለግ የሚያስችል ድርድር ለመጀመር በር ይከፍታል ተብሎ ተስፋ ተደርጓል።

በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ውስጥ አሁንም ግጭቶች እየተካሄዱ ሲሆን፣ ባለፉት ቀናት በዋና ከተማዋ ካርቱም ውስጥ ግጭቶች እየተካሄዱ መሆናቸው ተዘግቧል።

በሱዳን የተካሄደውን መፈንቅለ መንግሥትን ተከትሎ በኃያላኑ ወታደራዊ ጄኔራሎች መካከል ሲካሄድ የቆየው የሥልጣን ሽኩቻ ወደ ግጭት አምርቶ ሱዳን ቀውስ ውስጥ የገባችው ሚያዝያ 07/2015 ዓ.ም. ነበር።