ሱዳናዊቷ ታዋቂ ሙዚቀኛ ሻዲን ጋርዱድ በተባራሪ ጥይት ተገደለች

ሻዲን ጋርዱድ

የፎቶው ባለመብት, SHADEN GARDOOD/FACEBOOK

የምስሉ መግለጫ, ሻዲን ጋርዱድ

ከሱዳን ከታዋቂ ዘፋኞች አንዷ የሆነችው ሻዲን ጋርዱድ በኦምዱርማን ከተማ በተባራሪ ጥይት መገደሏ ተገለጸ።

ጋርዱድ አርብ ዕለት በሱዳን ጦር ሠራዊት እና በአገሪቱ ልዩ ፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች መካከል በተነሳ ግጭት ነው ሕይወቷ ያለፈው።

የ37 ዓመቷ ሙዚቀኛ የተገደለችው ተፋላሚዎቹ ኃይሎች የሠላማዊ ዜጎችን ስቃይ ለማቃለል ስምምነት ከተፈራረሙ ከአንድ ቀን በኋላ ነው።

በሱዳን ግጭት የተቀሰቀሰው በአገሪቱ ወታደራዊ ጄኔራሎች መካከል በተፈጠረው የሥልጣን ሽኩቻ ምክንያት ነው።

ጋርዱድ የምትኖርበት በአል-ሃሽማብ በሚባለው ሰፍር አካባቢው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የልዩ ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ በስፋት የሚንቀሳቀስበት አካባቢ ሆኗል።

የእህቷ ልጅ ሄራ ሐሰን መሐመድ ሙዚቀኛዋ መሞቷን በፌስቡክ ካረጋገጠች በኋላ “ተወዳጅ እና እንደ እናት ነበረች። እያወራን ነበር። ፈጣሪ ነፍሷን ይማር” ብላለች።

በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በተሰራጨው ቪዲዮ ላይ ጋርዱድ ከጥቃቱ ለመደበቅ እየሞከረች እንደሆነ ተናግራ ልጇ መስኮቶቹን እንዲዘጋ ስትጠይቅ ተሰምታለች።

“ከበሩ እና ከመስኮቱ ራቁ … በአላህ ስም፤ በደንብ ለብሰን ነው የምንሞተው… ይህን ልበሱ፣ በደንብ ለብሰን እንሞታለን” ስትል ተሰምታለች።

ጋርዱድ በሰፈሯ ስላለው ግጭት እና ተኩስ ፌስቡክ ላይ የቀጥታ ቪዲዮዎችን የምታሰራጭ የነበረ ሲሆን፣ ጦርነቱን በመቃወምም በትኩረት ጽፋለች።

ፌስቡክ ላይ ለመጨረሻ ጊዜ በካሰፈረቻቸው ጽሑፎች በአንዱ “ለ25 ቀናት በቤታችን ተገድበን ቆይተናል… ተርበን እና በከፍተኛ ፍርሃት ውስጥ እየኖርን ቢሆንም በሥነ-ምግባር እና በእሴቶችን ግን ሙሉ ነን” ስትል በመዲናዋ ካርቱም ካለውን ዘረፋ አንጻር ጽፋለች።

ጋርዱድ ከጦርነቱ የመጀመሪያ ቀን ጀምሮ የጦር አውድማ በሆነው በአገሪቱ ብሔራዊ ቴሌቪዥን እና ሬዲዮ ሕንጻ አጠገብ ትኖር ነበር።

ልዩ ኃይሉ ህንጻውን ቢጠብቅም በጦር ጄቶች ከሚደርሰው የማያቋርጥ ጥቃት በተጨማሪ በመሬት ላይ በሁለቱ ኃይሎች መካከል ግጭት ተደጋግሞ ተፈጥሯል።

ከጋርዱድ ጋር በተመሳሳይ ሰፈር የሚኖሩ አንድ ነዋሪ “ትናንት ሌሊቱን ሙሉ የዘለቀው ግጭት ኃይለኛ ነበር። ሌሊቱን ሙሉ ተዋጊ ጄቶችም ሲያንዣብቡ ቆይተዋል” ብለዋል።

“የታዘብኩት ነገር ሻዲን ጉዳት ከደረሰባት በኋላ ግጭቱ ትንሽ የቀነሰ ቢሆንም፣ በኋላ ላይ ከሩቅ ድምጽ መስማት ቀጠልን” ሲሉ ገልጸዋል።

ጋርዱድ በኋላ ላይ በደረሰባት ጉዳት ምክንያት ሕይወቷ ማለፉን ነዋሪው ተናግሯል።

ጋርዱድ የ15 ዓመት ወንድ ልጇ ሃሙዲ እና እናቷ እና እህቷ ባሉበት ነው ሕይወቷ ያለፈው።

በሱዳን ጦር ኃይሎች እና በአገሪቱ ልዩ ፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች መካከል ያለው ጦርነት በካርቱም ለአራት ሳምንታት ያህል ሲካሄድ ቆይቷል።

ሻደን ጋርዱድ በሱዳን ታዋቂ ዘፋኝ ነች

የፎቶው ባለመብት, SHADEN GARDOOD/FACEBOOK

በጦርነቱ ምከንያት ከ600 በላይ ንፁሃን ዜጎች ሲሞቱ ከ4,000 በላይ ደግሞ ቆስለዋል። 80 በመቶ ያህሉ ሆስፒታሎች ሲዘጉ የከፋ የምግብ፣ የውሃ እና የመብራት እጦትም ተከስቷል።

ጋርዱድ ከ2011 ጀምሮ የጦርነት ቀጠና ከሆነው ከደቡብ ኮርዶፋን ግዛት የተገኘች ሲሆን፣ በኋላ ላይ ከቤተሰቦቿ ጋር በካርቱም መኖር ጀምራ ነበር።

ለክልሏ ሠላም እና ደኅንነት የዘፈነች ሲሆን፣ አል-ባጋራ የሚባሉትን እና የተገለውን ማኅበረሰቧን ባህል በማስተዋወቅ ሠርታለች።

ጋርዶድ ዘፋኝ ከመሆኗም በላይ የአል-ባጋራ ዜማዎች ተመራማሪ ነበረች። ጥናታዊ ጽሑፎችንም አቅርባለች።

ባለፉት ጥቂት ሳምንታት በካርቱም በርካታ ታዋቂ ሰዎች ተገድለዋል። ከእነዚህም መካከል በ80 ዓመታቸው በተባራሪ ጥይት ሕይወታቸው ያለፈው የሱዳን የመጀመሪያዋ ፕሮፌሽናል ተዋናይት አሲያ አብደልማጂድ ይገኙበታል።

የ72 ዓመቱ የቀድሞ እግር ኳስ ተጫዋች ፎዚ ኤል-ማርዲም ሕይወቱ ያለፈው ሴት ልጁ በኦምዱርማን በተነሳ ግጭት ከተገደለች ከጥቂት ቀናት በኋላ ነው።

ጦርነቱ ከተጀመረ ከአራት ቀናት በኋላ ተደጋጋሚ የተኩስ አቁም ቢታወጅም ተግባራዊ ሊሆን ግን አልቻለም።

ግጭቱ ከመቀጡለም በላይ ተዋጊ ጄቶቹ በከተማው እያንዣበቡ ይገኛሉ።