ከባድ ውጊያ ላይ ያሉት የሱዳን ተፋላሚዎች የተኩስ አቁም ድርድር ዛሬ ሊጀምሩ ነው

የፎቶው ባለመብት, EPA
ዛሬ እሁድ መልሶ ይጀመራል ተብሎ ከሚጠበቀው የሱዳን ተፋላሚ ኃይሎቹ የተኩስ አቁም ንግግር ቀደም ብሎ በዋና ከተማዋ ካርቱም እና በሌሎች ከተሞች ከባድ ውጊያዎች መካሄዳቸው ቀጥሏል።
ነዋሪዎች እንዳሉት የፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች የሰላማዊ ዜጎችን ይዞታዎች እየወረሩ ሲሆን፣ የሱዳን ጦር ሠራዊት ደግሞ ሰላማዊ ሰዎች የሚኖሩባቸውን አካባቢዎችን በከባድ መሳሪያ እያደበደበ ነው።
በሁለቱ ኃይሎች መካከል በካርቱም፣ በኦምዱርማን እና በዳርፉር ክልሏ ጄኔይና ውስጥ ግጭቶች ማካሄዳቸው ተዘግቧል።
ይህ በሱዳን ሠራዊት እና በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ መካከል እየተካሄደ ያለው ውጊያ አንድ ወር ሊሆነው ተቃርቧል።
የሱዳን ተፋላሚዎቹ ኃይሎች በሳዑዲ አረቢያ እና በአሜሪካ አደራዳሪነት ለቀናት ድርድር ካደረጉ በኋላ ባለፈው ሐሙስ “ለድርድሩ ተገዢ ለመሆን” ስምምነት ፈርመዋል።
ዛሬ እሁድ ደግሞ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ለመድረስ በሳዑዲዋ የወደብ ከተማ ጄዳ ውስጥ ንግግራቸውን መልሰው ይጀምራሉ ተብሏል።
ባለፈው ሳምንት በተካሄደው ድርድር ሁለቱ ተቀናቃኝ ኃይሎች ሰላማዊ ሰዎች እና የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦቶች ጥቃት እንዳይፈጸምባቸው ጥበቃ ለማድረግ ቢስማሙም ተኩስ አቁም ላይ ግን መድረስ ሳይችሉ ቀርተዋል።
አንድ አሜሪካዊ ዲፕሎማት ድርድሩ እጅግ አስቸጋሪ እና ሁለቱ ወገኖች ለመስማማት ከሚያስችል መቀራረብ ላይ አለመድረሳቸውን እና የተራራቀ አቋም መያዛቸውን ገልጸዋል።
ነገር ግን ሁለቱ ተፋላሚ ኃይሎች ለሰላማዊ ዜጎች እና ለሰብአዊ እርዳታ አስፈላጊውን ጥበቃ ለማድረግ ስምምነት ፈርመዋል።
ዛሬ በሚጀመረው ድርድር ደግሞ ዋነኛው አጀንዳ ተፋላሚዎቹ ተኩስ አቁመው ለዘላቂ ሰላም የሚሆን ንግግር እንዲደረግ መንገድ መክፈት ነው ተብሏል።
ባለፉት ቀናት በተለያዩ የሱዳን አካባቢዎች በጄኔራል አል ቡርሐን እና በተቀናቃኛቸው ጄኔራል ዳጋሎ ኃይሎች መካከል ውጊያ እና የአየር ጥቃቶች እየተካሄዱ መሆኑ ተዘግቧል።
ሃኒ አህመድ የተባለች የ28 ዓመት የካርቱም ነዋሪ እንዳላቸው የቅዳሜ ጠዋቱ ውጊያ ካለፉት ሁለት ቀናት የከፋ ነበር፤ ታንኮች እና የፈጥኖ ደራሹ ኃይል አባልት ከተለመደው በተለየ ሁኔታ ጎዳናዎችን በመቃኘት ሲንቀሳቀሱ ነበር።
“የሠራዊቱን አውሮፕላኖች እንጂ ፊት ለፊት የምናያቸው የፈጥኖ ደራሹን ኃይል አባላት ብቻ ነው። ከተማዋ ውጥ ያሉት እነሱ ናቸው” ብላለች ሃኒ አህመድ።
በዳርፉር ያለ አንድ የመብት ተቆርቋሪ ቡድን እንዳመለተው፣ ለሁለት ሳምንት ተረጋግቶ በነበረው ጄኔይና ውስጥ ባለፈው አርብ በተቀሰቀሰው ውጊያ ቢያንስ 77 ሰዎች ተገድለዋል።
ቡድኑ ጨምሮም በሞተር ሳይክሎች እና በፈጥኖ ደራሹ ኃይል ተሽከርካሪዎች የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች የግድያ፣ የዝርፊያ፣ ንብረት የማቃጠል እና የሽብር ድርጊቶችን እየፈጸሙ ነው ብሏል።
በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ቀጥጥር ስር በነበረ የካርቱም ክፍል ውስጥ ነዋሪ የሆነው ዲዋ ታሪቅ “ታጣቂዎቹ እየተዘዋወሩ በሰዎች ላይ ዝርፊያ እና ጥቃት ይፈጽማሉ፣ በፈለጉት ቤት ውስጥም ገብተው እዚያው ይቆያሉ” ብሏል።
አራት ሳምንታትን ባስቆጠረው በዚህ ጦርነት በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የተገደሉ ሲሆን፣ 200 ሺህ የሚጠጉ ደግሞ አገራቸውን ለቀው ወደ ጎረቤት አገራት ተሰደዋል። በተጨማሪም 700 ሺህ የሚገመቱ ሱዳናውያን ተፈናቅለው እዚያው አገራቸው ውስጥ ይገኛሉ።
የተስፋፋው ዘረፋ እና የዓለም አቀፍ እርዳታ ድርጅቶች ሱዳንን ለቀው መውጣት ከፍተኛ የምግብ እና የመድኃኒት እጥረት እንዲከሰት አድርጓል።
በሰሜናዊ ዳርፉር ውስጥ በሚገኘው ትልቁ የተፈናቃዮች መጠለያ ካምፕ ውስጥ ያሉ ሰዎች በምግብ እጥረት የተነሳ በቀን አንድ ጊዜ ብቻ ነው ምግብ የሚቀርብላቸው።
የህክምና በጎ አድርጎት ድርጅቱ ሜዲዲን ሳን ፍሮንቴርስ እንዳስጠነቀቀው ህጻናት ያሉበት ሁኔታ ወደ አደገኛ ደረጃ እያሽቆቀለ መሄዱ የማይቀር ነው።
የሱዳን ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን አሁንም የሱዳን የአየር ክልል እስከ ግንቦት ማብቂያ ድረስ ዝግ ሆኖ እንደሚቆይ ገልጿል። ነገር ግን “ሰዎችን ከሱዳን የማስወጣት እና የሰብአዊ እርዳታ በረራዎች” መካሄዳቸውን ይቀጥላሉ።












