የሱዳን ተቀናቃኝ ኃይሎች የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ መድረስ እንዳልቻሉ ተነገረ

ጄኔራል መሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ እና ጄኔራል አብደፍ ፋታህ አል ቡርሐን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ጄኔራል መሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ እና ጄኔራል አብደፍ ፋታህ አል ቡርሐን

በጦርነት ውስጥ የሚገኙት ሁለቱ የሱዳን ተቀናቃኝ ኃይሎች ሰላማዊ ሰዎች እና የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦቶች ጥቃት እንዳይፈጸምባቸው ጥበቃ ለማድረግ ቢስማሙም ተኩስ አቁም ላይ ግን መድረስ አልቻሉም።

ከተጀመረ አራተኛ ሳምነቱ ላይ የደረሰው የሱዳን ጦርነትን ለማስቆም በሱዳን ሠራዊት እና በፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች መሪዎች መካከል ሳዑዲ አረቢያ ውስጥ እየተካሄደ ያለው ድርድር የሚፈለገውን ውጤት አስካሁን አላስገኘም።

ከሱዳን ባሻገር ቀይ ባሕርን ተሻግራ በምትገኘው በሳዑዲዋ የወደብ ከተማ ጄዳ ውስጥ በተቀናቃኞቹ አንጃዎች መካከል እየተካሄደ ያለውን ንግግር ሳዑዲ አረቢያ እና አሜሪካ ናቸው ያዘጋጁት።

አንድ አሜሪካዊ ዲፕሎማት ድርድሩ እጅግ አስቸጋሪ እንደሆነ እና ሁለቱ ወገኖች ከስምምነት ላይ ለመድረስ ከሚያስችል መቀራረብ ላይ አለመድረሳቸውን አሁንም “ተራርቀው ነው ያሉት” ሲሉ ገልጸውታል።

ነገር ግን ሁለቱ ተፋላሚ ኃይሎች ለሰላማዊ ዜጎች እና ለሰብአዊ እርዳታ አስፈላጊውን ጥበቃ ለማድረግ ስምምነት ፈርመዋል።

ተኩስ የማቆሙ ነገር ግን አሁንም እልባት ያላገኘ ሲሆን፣ ንግግሩ እየተደረገ በተለያዩ የሱዳን ክፍሎች ውስጥ ውጊያዎች አየተካሄዱ ነው።

ሁለቱ ኃይሎች አሁን በደረሱት ስምምነት መሠረት የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት በችግር ላይ ላሉ ሰዎች እንዲደርስ እና ውጊያን በመሸሽ ከአካባቢያቸው ለቀው ለመውጣት የሚፈልጉ ሰዎች እንዲንቀሳቀሱ ፈቅደዋል።

የአገሪቱ ጦር ሠራዊት አዛዥ የጄኔራል አብደፍ ፋታህ አል ቡርሐን እና የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ አዛዥ የጄኔራል መሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ ተወካዮች አሁንም ድርድራቸውን መቀጠላቸው ተነግሯል።

ሁለቱ ወገኖች በዋናነት ለ10 ቀናት የሚቆይ ተኩስ አቁም ለማድረግ እና ተፈጸሚነቱን የመቆጣጠሪ ዘዴ ላይ እንዲስማሙ አደራዳሪዎቹ ግፊት እያደረጉ ነው።

ተፋላሚዎቹ ወገኖች ውጊያው ከተጀመረ በኋላ በነበሩት ሳምንታት ለሦስት ጊዜ ያህል ለተለያዩ ቀናት ተኩስ ለማቆም ስምምነት ላይ ደርሰው የነበረ ቢሆንም ሳይከበር ውጊያው ቀጥሏል።

አሁን ውጊያውን ለመግታት ለአጭር ጊዜ የተኩስ አቁም እንዲደረስ እየተደረገ ያለው ግፊት ከተሳካ፣ በዘላቂነት ግጭቱን በማስቆም በአገሪቱ ውስጥ ለተፈጠረው ቀውስ መፍትሄ ለመፈለግ የሚያስችል ድርድር ለመጀመር በር ይከፍታል ተብሎ ተስፋ ተደርጓል።

በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ውስጥ አሁንም ግጭቶች እየተካሄዱ ሲሆን፣ ትናንት ሐሙስ በዋና ከተማዋ ካርቱም ውስጥ ግጭቶች መካሄዳቸው የተዘገበ ሲሆን፣ ነገር ግን ቀደም ካሉት ቀናት ከነበረው ሁኔታ ግን ተሻለ መሆኑ ተገልጿል።

በሱዳን የተካሄደውን መፈንቅለ መንግሥትን ተከትሎ በኃያላኑ ወታደራዊ ጄኔራሎች መካከል ሲካሄድ የቆየው የሥልጣን ሽኩቻ ወደ ግጭት አምርቶ ሱዳን ቀውስ ውስጥ የገባችው ሚያዝያ 07/2015 ዓ.ም. ነበር።

በዚህም ሳቢያ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች እየተካሄደ ባለው ውጊያ ሳቢያ ለህልፈት የተዳረጉ ሲሆን፣ በርካታ ሺዎች ደግሞ ጉዳት እንደደረሰባቸው የሆስፒታል ምንጮች እና የእርዳታ ድርጅቶች ገልጸዋል።

በተጨማሪም ከ800 ሺህ የሚበልጡ ሱዳናውያን ግጭቱን በመሸሽ ቤት ንብረታቸውን ትተው በመፈናቀል እዚያው አገራቸው ውስጥ እና ወደ ጎረቤት አገራት ሳይሰደዱ እንዳልቀረ ተነግሯል።