በኢትዮጵያ ካሉ ትላልቅ ፕሮጀክቶች ዲዛይን ጀርባ ያለው ወጣት አርክቴክት

የፎቶው ባለመብት, Haile Tadesse
በገበታ ለሀገር ከእየተገነቡ ካሉ የተለያዩ ግዙፍ ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ የሆነው የሚገኝበት የኮንታ ዞን በተፈጥሮ ሀብቶች የታደለው ነው።
ኮንታ ግን በተፈጥሮ ሀብት ብቻ ሳይሆን በሙያቸው የተካኑ አርክቴክቶችም አግኝቷል።
በእነዚህ አርክቴክቶች ዲዛይን የተደረገው እና በቅርቡ ተመርቆ ይፋ የተደረገው የሃላላ ኬላ ሪዞርት በርካቶችን አስደምሟል።
በደቡብ ምዕራብ ክልል፣ በኮንታ ዞን የኮይሻ ፕሮጀክት ይገኛል። ታድያ ከዚህ ፕሮጀክት ጀርባ እነማን አሉ? ቢቢሲ ከእነዚህ መካከል ወጣቱን አርክቴክት ኃይሌ ታደሰን አግኝቷል።
በቅድሚያ ግን ስለ ኮይሻ ፕሮጀክት ጥቂት ነገር እንበል።

የፎቶው ባለመብት, PM Office
ይህ የመዝናኛ ስፍራ ልማት የኮይሻ ዓለም አቀፍ የቱሪስት መዳረሻ ልማት የሚባለው ትልቅ ፕሮጀክት አካል ሲሆን በክልሉ የተለያዩ ዞኖች ውስጥ የሚገኝ ነው።
አካባቢው የጨበራ ጩርጩራ ብሔራዊ ፓርክ መገኛ ሲሆን፣ የተለያዩ ማኅበረሰቦችም መኖሪያ ነው።
በሚያዝያ ወር መጀመርያ ላይም በደቡብ ምዕራብ ክልል ውስጥ የሚገኘው የገበታ ለሀገር ፕሮጀክት አካል የሆነው የሐላላ ኬላ ሪዞርት በይፋ ተመረቋል።
ገበታ ለሀገር በሚባለው ፕሮጀክት ስር የሆነው እና አዲስ በተመሠረተው ክልል ውስጥ የሚገኘው ይህ የመዝናኛ ስፍራ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ተመርቆ ተከፍቷል።
ይህ ሪዞርት ከፕሪቶሪያው ስምምነት በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና የህወሓት ተወካዮች ለመጀመሪያ ጊዜ ፊት ለፊት በመገናኘት የተነጋገሩበት ስፍራ ነው።
“ይህ ፕሮጀክት የአካባቢውን ታሪክ እና ባህል የተፈጥሮን እና የሰው ሰራሽ ሀብቶች አጣምሮ የያዘ ነው” ይላል ፕሮጀክቱን ዲዛይን ያደረገው አርክቴክት ኃይሌ።
በክልሉ እየተሰሩ ካሉ የገበታ ለሀገር ፕሮጀክቶች ውስጥ ትልቁ የጨበራ ጩርጩራ ብሔራዊ ፓርክ መሆኑን አርክቴክቱ አክሎ ይናገራል።
ከዚህም ባሻገር ረዥም እድሜ ያስቆጠረው እና ሰው ሰራሹ ልማት ሃላላ ኬላ የተባለው የድንጋይ ካብ እዚሁ ውስጥ ይገኛል።
“በዳውሮ ሕዝብ በ16ኛው ክፍለ ዘመን ውስጥ የተገነባው የድንጋይ ካብ ወይንም ኬላ በግምት 1200 ኪሎ ሜትር የሚረዝም ነው። መጠሪያውንም ከመጨረሻው ንጉሣቸው ያገኘ ነው። እነርሱ ‘ካቲ ሃላላ ኬላ’ ይሉታል።”
በተጨማሪም የግልገል ጊቤ ሦስት ግድብ፣ እንዲሁም የኮይሻ የኤሌትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ የዚሁ ትልቁ ፕሮጀክት አካል ናቸው።
በሃላላ ኬላ ፕሮጀክት ውስጥ በአምስተኛነት ደረጃ የታቀፈው ፕሮጀክት ጫራ የሚባል ማኅበረሰብን ማዕከል ያደረገ ነው።
“የጫራ ሕዝብ ከጥንት ጀምሮ ከአፈር ውስጥ ብረት የማውጣት እውቀት ያለው ሲሆን፣ እስከ ዛሬ ድረስም ይህንን ሙያ እየሰሩ ይገኛሉ። ይህ ማኅበረሰብ የራሱ የሆነ ባሕል እና ክህሎት ያለው ሕዝብ ነው።”
እነዚህ ልማቶች በአምስት ክላስተሮች በመክፈል ዲዛይኑን እንደሰሩ አክርቴክት ኃይሌ ይናገራል።
ከዚህ በተጨማሪ እነዚህን የልማት መዳረሻዎችን ደረጃ በደረጃ እስከ 25 ዓመታት በሚደርስ ጊዜ ውስጥ ሠርቶ ለማጠናቀቅ ታቅዷል።
ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ “በአጭር ጊዜው የሦስት ዓመት ፕሮጀክት ውስጥ ሃላላ ኬላ እና ጨበራ ሪዞርቶች ይገኛሉ።”

የፎቶው ባለመብት, Haile Tadesse
አርክቴክት ኃይሌ ማን ነው?
አርክቴክት ኃይሌ ታደሰ በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን በግንደ በረት ወረዳ ውስጥ በምትገኘው ካቺሲ ውስጥ ነው ተወልዶ ያደገው።
የመጀመሪያ እና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱንም ተምሮ ያጠናቀቀው በትውልድ አካባቢው ነው።
በኋላም በወለጋ ዩኒቨርስቲ በአርክቴክቸር የትምህርት ዘርፍ አምስት ዓመት ካጠና በኋላ በከፍተኛ ውጤት ተመርቋል።
ከተመረቀ በኋላም ለሁለት ዓመታት በሐዋሳ እና በደብረ ብርሃን ዩኒቨርስቲዎች በመምህርነት አገልግሏል።
ከዚያም የሁለተኛ ዲግሪውን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በአርክቴክቸራል ኢንጂነሪንግ የትምህርት ዘርፍ አጠናቅቋል።
ተመርቆ እንደጨረሰም የራሱን የግል ድርጅት ‘ሉላ ኢንጂነሪንግ’ በሚል ስያሜ በማቋቋም እየሠራ መሆኑን ከቢቢሲ ጋር በነበረው ቆይታ ተናግሯል።
“ተወልጄ ያደግኩት ገጠር ውስጥ ነው” የሚለው ኃይሌ፣ በኮንታ አካባቢ ያለው የተፈጥሮ ውበት እንደሚማርከው ይናገራል።
“የአፍሪካ ተራራዎች ተሰብስበው ዳውሮ ከትመዋል ይላሉ ሰዎች” በማለት አካባቢው በተፈጥሮ ሀብት የታደለ መሆኑን ይገልጻል።
በሌላ በኩል የዳውሮ ሕዝብ ያለው ባህል፣ ትውፊት እና ሕግጋት ከዚህም ባሻገር በአካባቢው ያለው ሰላም አስተማማኝ መሆኑንም ይጠቅሳል።
ከዚህ በተጫመሪ ሕዝቡ ለእንግዳ የሚያደርገው አቀባበል የተለየ መሆኑ አካባቢው ለጎብኚ ምቹ እና ሁሉን የያዘ እንደሆነ ይመሰክራል።
አርክቴክት ኃይሌ እንደሚለው ለእነዚህ ፕሮጀክቶች በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽህፈት ቤት አማካኝነት በቅርበት የሚደረገው ክትትል እና የአካባቢው ሰላም ሥራዎቹ በተያዘላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ አስተዋጽኦ አድርጓል።

የፎቶው ባለመብት, PM office
የአርክቴክት ኃይሌ ሚና ምን ነበር?
አርክቴክት ኃይሌ ታደሰ ከዓመታት በፊት በመሠረተው ድርጅቱ አማካይነት በዚህ ፕሮጀክት እና በሌሎችም ትላልቅ ፕሮጀክቶች ላይ ከተሳተፉት አካላት መካከል ነው።
‘ሉላ ኢንጂነሪንግ’ የተባለው የእርሱ ድርጅት እና ሌላ ‘ስታዲያ ኢንጂነሪኒግ’ የተባለው ድርጅት በጥምረት የእነዚህን ፕሮጀክቶች ዲዛይን በመሥራት እንዲሁም ቁጥጥር በማድረግ ተሳትፈዋል።
“እነዚህን በክላስተር የተከፈሉትን ዲዛይኖች ‘ኮንሰፕት ዲዛይን’ ከማዘጋጀት ባለፈ የዲዛይን ቁጥጥር እና ክትትል እንድንሰራ ነው ኮንትራት የገባነው” ይላል።
እንደ ግሉ ደግሞ ኃይሌ የአርክቴክቸራል ቡድን መሪ በመሆን እነዚህ ፕሮጀክቶች ላይ ተሳትፎ ማድረጉን ይናገራል።
“እድሜዬ 31 ነው፤ ዛሬ ደረስኩባቸው ብዬ የማስባቸው ነገሮች፣ ፍላጎቴን እና ጥረቴን አንድ ላይ አጣምሬ ሳያቸው ትንሽ የዘገየሁ ይመስለኛል” በማለት በራስ መተማመን በዚህ ፕሮጀክት ላይ መሳተፉን ይናገራል።
“ትልቁ ነገር ጠንክሮ መሥራት ነው” የሚለው ይህ ወጣት፣ ከልጅነቱ ጀምሮ ለአርክቴክቸር ትምህርት፣ ፍቅር እና ልዩ የሆነ ፍላጎት ማሳደሩ አሁን ለደረሰበት ደረጃ ለመብቃት ረድቶታል።
አርክቴክት ኃይሌ በትምህርት እና በሥራው ላይ ከመበርታቱ ባሻገር በዚህ ዘርፍ በተቻለው መጠን ሌሎች ቦታዎች ያሉ ተሞክሮዎችን ለማግኘት ከፍተኛ ጥረት ያደርጋል።
“ይህንን ፕሮጀክት ከማግኘቴ በፊት ኬንያ እና ታንዛኒያ ሄጄ ነበር። የእኛ አገር ፓርኮች እንዴት መልማት አለባቸው የሚለውን ተሞክሮ ለመውሰድ ማሳይ ማራ እና ሰረንጌቲ ፓርኮችን ጎብኝቻለሁ።”
ከዚህ በተጨማሪም እንደሀገር ተይዞ እየተሠራ ያለውን በአማራ ክልል የሚገኘውን የጎርጎራ የቱሪዝም ልማት መዳረሻ ዲዛይንንም እንደሠራ ጠቅሷል።
አርክቴክት ኃይሌ የዚህን ፕሮጀክት ዲዛይንንም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በተገኙበት በኮይሸ ተገኝቶ ማቅረቡንም ተናግሯል።
ቀጣይነት ያለው ዲዛይን
አርክቴክት ኃይሌ ስለ ወደፊት ህልሙ እና አሁን እየሠራው ስላለ ሥራ ሲጠየቅ ቀጣይነት ስላላቸው ፕሮጀክቶች በተደጋጋሚ ይናገራል።
“አባቶቻችን ማንኛውንም ልማት ሲሰሩ ከተፈጥሮ ጋር እንዲስማማ አድርገው ነው። ተፈጥሮን የሚጎዳ ማንኛውንም ነገር አያበረታቱም” የሚለው ኃይሌ፣ ከአየር ብክለት ጋር በተያያዘ ዓለማችን ፈተና እየገጠማት እንደሆነ ያስታውሳል።
አክሎም “ቀጣይነት ባላቸው ነገሮች እሳቤ ከዚህ በፊት የተበላሸው ወደኋላ እንዲመለስ፣ እንዲሁም ዛሬ እየተገነባ ያለው ደግሞ ተሻሽሎ አንዲገነባ ይታሰባል።”
ነገር ግን እሱ እንሚታዘበው ከሆነ በአሁኑ ጊዜ እየተገነቡ ያሉ የተለያዩ አይነት ግንባታዎች የተበላሸውን ለማስተካከል፣ የወደፊተንም ለመጠበቅ መደረግ ያለበትን ማዕከል ያደረጉ አይደሉም።
“ፕሮጀክቶች ያለጥናት ይታቀዳሉ። ይገነባሉ። መጀመሪያ እና መጨረሻቸው አይታወቅም። ወደፊት ለምትሄደው ዓለምም እየሠራን አይደለም። አባቶቻችን ያወረሱንንም ያህል እየሠራን አይደለም። እንደ አገር መካከል ላይ [ተንጠልጥሎ] የቀረ ነገር አለን።”
አርክቴክት ኃይሌ ታደሰ እንደሚለው በኦሮሞ አባቶች ባሕል መሠረት “. . . አምስቱ ኦዳዎች በማለት ለእኛ እንዳወረሱን፣ እኛም ደግሞ ለመጪው ትውልድ መቆየት የሚችሉ ቀጣይነት ያላቸው ግንባታዎችን ማቆየት አለብን የሚል ፍላጎትም ተስፋም አለኝ።”












