የአፍሪካ መሪዎችን እያስተናገደች ያለችው ኪዬቭ የሚሳኤል ጥቃት ተፈጸመባት

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የአፍሪካ መሪዎች የሰላም ልዑካን ቡድንን እያስተናገደች ያለችው የዩክሬኗ መዲና ኪዬቭ የሚሳኤል ጥቃት ተፈጸመባት።
መሪዎቹ ወደ ኪዬቭ ያቀኑት ሩሲያና ዩክሬን ጦርነቱን አቁመው ውይይት እንዲጀምሩ ለማግባባት ነው ተብሏል።
የዩክሬን ጦር በዛሬው ዕለት የሚሳኤል ጥቃት እንደተፈጸመ ገልጾ በርካቶቹንም የአየር ኃይሉ ማክሸፍ እንደቻለም ተገልጿል።
ከእነዚህ ውስጥ ስድስቱ ሃይፐርሶኒክ ኪንዝሃል የተሰኙ ሚሳኤል መሆናቸውንም ጦሩ አስታውቋል።
ጥቃቱንም ተከትሎ የዩክሬን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲሚትሮ ኩሉባ መልዕክቱ ግልጽ እንደሆነ ተናግረዋል።
“የሩሲያ የሚሳኤሎች ጥቃት ለአፍሪካ መልዕክት ናቸው። ይህም ሩሲያ የበለጠ ጦርነትን እንጂ ሰላምን አትፈልግም የሚል ነው” ብለዋል።
የአፍሪካ መሪዎች ጉብኝታቸውን በጀመሩበት ወቅት የተፈጸመው ይህ የአየር ጥቃት የሩስያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን “ተጨማሪ ጦርነት” እንደሚፈልጉ አሳይ ነው ብለዋል።
የመሪዎቹ የልዑካን ቡድን በደቡብ አፍሪካው ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎሳ የሚመራ ሲሆን የሴኔጋል፣ የዛምቢያ እና የኮሞሮስ መሪዎችን ጨምሮ በአጠቃላይ የሰባት አገራት መሪዎች ተካትተውበታል።
የሰላም ልዑካኑ በ ኪዬቭ ቆይታቸው ከፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዘሌንስኪ ጋር ተገናኝተው ይመክራሉ። ቅዳሜ ሰኔ 10/2015 ዓ.ም ወደ ሩሲያ በማቅናትም ከፕሬዚዳንት ፑቲን ጋር ለመገናኘት ቀነ ቀጠሮ ይዘዋል።
መሪዎቹ ከሁለቱ አገራት መሪዎች ጋር ግጭትን በዘላቂነት የማስቆምና ልዩነቶቻቸውንም በሰላም እንዲቋጩ ለማድረግ ይወያያሉ።
በተጨማሪም ያልተገደበ እህል ከዩክሬን እና ማዳበሪያ ከሩሲያ ወደ ሌሎች አገሮች የመላክን አስፈላጊነት ላይ አጽንኦት ይሰጣሉ ተብሎ ይጠበቃል። የሰላም ልዑካኑ ተነሳሽነት የመጣው ዩክሬን በሩሲያ ወረራ ላይ የመልሶ ማጥቃት ዘመቻውን በጀመረችበትና ውጊያው እየተጠናከረ በመጣበት ወቅት ነው።
ሩሲያ ዩክሬንን ወራ በኃይል ግዛቶቿን ከተቆጣጠረች 18 ወራት ተቆጥሯል።
ዩክሬንም በምስራቅና ደቡብ በሩሲያ የተያዙባትን ግዛቶች ለማስመለስ ለረጅም ጊዜ ሲጠበቅ የነበረውን መልሶ ማጥቃት ጀምራለች።
መጀመር ብቻ ሳይሆን መልሶ ማጥቃቱ ተጠናክሮ ቀጥሏል።












