የአፋሩ ዳሎል እና የሐዋሳው ኢንዱስትሪ ፓርክ በታዋቂው ፎቶግራፈር ሥራዎች ውስጥ የተካተቱበት ምክንያት

አፋር የሚገኘው የደናክል ዲፕሬሽን

የፎቶው ባለመብት, Edward Burtynsky

የምስሉ መግለጫ, አፋር የሚገኘው የደናክል ዲፕሬሽን

ታዋቂው ፎቶግራፈር ኤድዋርድ በርቲኒስኪ የአፋሩን ደናክል ጨምሮ ‘የሰው ልጅ በተፈጥሮ ላይ ያደረሰው ጠባሳ ማሳያ’ ያላቸውን ፎቶዎች ይፋ አድርጓል።

ካናዳዊው ፎቶ አንሺ በርትኒስኪ ላለፉት 40 ዓመታት የሰው ልጅ ተፈጥሮ ላይ ያደረሰውን ጉዳት በመቅረፀ-ምስል ሲያስቀር ቆይቷል።

እነዚህ ፎቶዎች ልክ እንደ ውስብስብ ሥዕል ያሉ ትንታኔ የሚሹ የጥበብ ሥራዎች ናቸው።

የፎቶ አንሺው ሥራዎች ‘ኖማድ ሴንቸሪ በተሰኘው’ የጋያ ቪንስ መጽሐፍ ውስጥ መካተት ችለዋል።

የአፋር ደናክል እና የሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ በዚህ መጽሐፍ ውስጥ የተካተቱ ፎቶዎች ናቸው።

ድንቅ የጥበብ ሥራዎች ከተባሉት 17 ፎቶዎች መካከል ዋናዎቹን እንመልከት።

‘የምድር ገሃነም’

የአፍር በረሃ

የፎቶው ባለመብት, Edward Burtynsky

“ቻይና ወደ አፍሪካ እያቀናች ነው የሚል ነገር የሆነ ቦታ አነበብኩ። እስቲ ይህን ነገር ልከተለው ብዬ ተነሳሁ” ይላል እንዴት ወደ አህጉረ አፍሪካ እንዳቀና ሲያስረዳ።

በጠቅላላው ለአስር ዓመት ያክል በተለያየ የአፍሪካ አገራት ውስጥ ቆይቷል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

“ከኬንያ ተነሳሁ፤ ወደ ኢትዮጵያ አቀናሁ፤ ከዚያ ደግሞ ወደ ደቡብ አፍሪካ።”

በርቲኒስኪ፤ ወደ አፋር ባቀናበት ወቅት ይዞት የተጓዘው ቴክኖሎጂ ሙቀቱን መቋቋም አቅቶት ሊሠራለት እንዳልቻለ ያወሳል።

“የያዝነው ድሮን ሊሠራልን አልቻለም። ምክንያቱም ከምድር ወለል 400 ሜትር ዝቅ ብለን ነው ያለነው። የድሮኑ ጂፒኤስ (አቅጣጫ ጠቋሚ) ‘እዚህ መሆን የለባችሁም። የውቅያኖስ ወለል ላይ ነው ያላችሁት’ ይለን ገባ።”

በርቲኒስኪ እና የሥራ አጋሮቹ አቅጣጫ ጠቋሚያ መሣሪያቸውን አጥፍተው ሥራቸውን ተያያዙ።

“የአፋር ደናክል ዝቅተኛ ቦታ (ዲፕሬሽን) 200 ኪሎ ሜትር በ50 ኪሎ ሜትር ላይ የተዘረጋ በረሃ ነው። በዓለማችን ካሉ እጅግ ሞቃት ሥፍራዎች አንዱ በመሆኑ “የምድር ገሃነም” የሚል ስም ተሰጥቶታል።”

ፎቶ አንሺው ከ50 ዲግሪ ሴንቲግሬድ በላይ ወደሚሞቅ ሥፍራ ሄዶ እንደማያውቅ ይናገራል።

“ማታ ማታ 40 ዲግሪ ይደርሳል። እሱን እንኳ መቋቋም ከባድ ነበር። ምንም ዓይነት ሕንፃ ስላልነበረ ውጭ ነበር የምናድረው።”

ፎቶግራፈሩ ከሙያ አጋሮቹ ጋር በመሆን ለሦስት ቀናት ያህል ደናክል ውስጥ ቆይቷል። ንጋት ላይ 25 ኪሎ ሜትር ያክል ተጉዘው ፎቷቸውን ያነሳሉ።

“ዳሎል የሚባል ቦታ አለ። ሰልፈር (ድኝ) እንደ እሣት የሚፈልቅበት። ወደዚያ ለማቅናት መሣሪያዎቻችንን ይዘን ለ1.5 ኪሎ ሜትር ያክል ድንጋይ በመቧጠጥ መጓዝ ነበረብን።”

በርቲኒስኪ፤ እኒህን ፎቶዎች ለማስቀረት ፀሐይ ከመውጣቷ በፊት አሊያም ልትጠልቅ አካባቢ ነው ካሜራውን የሚዘረጋው።

ይህ ማለት በቂ እረፈት ማግኘት ዘበት ነው ማለት ነው።

“ግን የሆነውን ሆነህ ትወጣዋለህ። እኔ አንድ ችግር ሲገጥመኝ መፍትሔ ነው የማፈላልገው። ይህ ለማድረግ ከእኔ ምን ይጠበቃል? ስል እጠይቃለሁ።”

ከሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ፋብሪካዎች በአንዱ ሠራተኞች ሥራ ላይ እያሉ

የፎቶው ባለመብት, Edward Burtynsky

የምስሉ መግለጫ, ከሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ፋብሪካዎች አንዱ

‘የአፍሪካ ተፈጥሮ ሃብትና ውበት’

ካናዳዊው ፎቶ አንሺ እንደሚለው አህጉረ አፍሪካ ተፈጥሮ አንጡረ ሃብት እና ውበቱን የለገሳት ናት።

ለምሳሌ በቅርቡ በታንዛኒያ እና ኬንያ ነዳጅ ተገኝቷል። በርካታ ነዳጅ አውጪዎች ይህን ዜና ሲሰሙ ወደ ሥፍራው እየመጡ ነው።

እሱ እንደሚለው በተለይ ደግሞ የቻይና ኩባንያዎች መሠረተ-ልማት እንዘርጋ እና የተፈጥሮ ሃብት እንቋደስ ይላሉ።

ይህን የሚያደርጉት ምጣኔ ሃብታዊ ጥቅም ለማግኘት አስበው እንደሆነ የሚናገረው በርቲኒስኪ፣ ይህ ጉዳይ ተፈጥሮ ላይ እያደረሰ ያለው ጫና ቀላል እንዳልሆነ ያሳስባል።

ፎቶግራፈሩ ወደ ሐዋሳ አቅንቶ፤ ወደ ኢንስዱስትሪ ፓርክ ገብቶ፤ ፎቶ አንስቶ ወጥቷል።

“እነዚን ፎቶዎች ያነሳኋቸው ሐዋሳ አንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ ነው። 200 80 ሄክታር ላይ ያረፈ የኢኮኖሚ ዞን ነው። ልክ እንደ ቻይናው ሼንዤን።”

በርቲኒስኪ፤ ወደ ፓርኩ ገብቶ መሃል መንገዱን ታከው በጎን እና በጎን የተሰደሩትን ፋብሪካዎች ሕንጻዎችን ጎብኝቷል።

“ሁሉም ነገር የተገነባው በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ነው። ሁሉም ነገር በመርከብ ተጭኖ መጥቶ ወደ ኢትዮጵያ በባቡር ተጓጉዞ ሲገነባ እዚያው ነበርኩ። ማሽኖቹን ገጣጥመው ልብስ ማማረቻ ሲያደርጓቸውም ተመልክቻለሁ።”

የናሚቢያ በረሃ

የፎቶው ባለመብት, Edward Burtynsky

የምስሉ መግለጫ, የናሚቢያ በረሃ

በርቲኒስኪ እንደሚያምነው ቻይና መሰል ፋብሪካዎች እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገራት ውስጥ የምትገነባው ከዚህ በኋላ አገሯ ውስጥ ማድረግ ስለማትችል ነው።

“አየራቸው ተበክሏል። ውሃቸው ተበክሏል። የቻይና ዜጎች ‘መሰል ፋብሪካዎች ውስጥማ አንሠራም’ ማለት ጀምረዋል” ይላል።

በምትኩ ቻይና ወደ ኢትዮጵያ እና ሴኔጋል በመሄድ በተለይ ደግሞ ሴቶች በርካሽ ዋጋ ይቀጥራሉ። አብዛኞቹ 16 አሊያም 17 ዓመት ዕድሜ ያላቸው ናቸው። ከቤተሰቦቻቸው ተነጥለው ከልብስ ማሽን በፊት ቁጭ ብለው ይሰፋሉ።”

በርቲኒስኪ ኬንያ በነበረበት ወቅት የማጋዲ ሶዳ ኩባንያን፣ የሴኔጋል ጨው ኩሬ፣ የናይጀር ዴልታን ነዳጅ ማውጫን ጎብኝቷል።

ናሚቢያ፣ ቦትስዋና፣ ደቡብ አፍሪካም ተጉዞ ምን ያህል የሰው ልጅ የተፈጥሮ ሃብት እየጎዳ እንዳለ የታዘበውን በካሜራው አስቀርቷል።