የአባትን አደራ ለመፈጸም በተደረገ ፍለጋ ከ50 ዓመታት በኋላ የተገናኙት ወንድማማቾች

አቶ ከራ ደለስ (ግራ) እና አቶ ቢቲማ ደለስ (ቀኝ)
የምስሉ መግለጫ, አቶ ከራ ደላስ (ግራ) እና አቶ ቢቲማ ደላስ (ቀኝ)

አቶ ቢቲማ ደለሳ የምዕራብ ሸዋ ዞን ቶኬ ኩታዬ ወረዳ ነዋሪ ናቸው።በ50ዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙት አቶ ቢቲማ የቤቱ ታላቅ ልጅ ናቸው።

የአቶ ቢቲማ አባት አቶ ደለሳ ሞጋሳ ይባላሉ።አቶ ደለሳ በወጣትነት ዘመናቸው የአቶ ቢቲማ እናትን ከማግባታቸው በፊት ሌላ ትዳር ነበራቸው።ይህ ታዲያ ለዘመናት የዘለቀ ምስጢር ሆኖ ቆይቷል።

አቶ ደለሳ ዕድሜያቸው ገፍቶ አይቀሬው ሞት ሳይቀድማቸው ለዘመናት ይዘው የቆዩትን ምስጢር ማውጣት እንዳለባቸው ይረዳሉ።

ከዚያም አቶ ደለሳ የሁለተኛ ትዳራቸውን ሁለተኛ ልጅ ጠርተው ለዘመናት ለብቻቸው ይዘውት የቆዩትን ምስጢር ያፈርጡታል።

አቶ ቢቲማ አባታቸው ያሏቸውን እንዲህ ሲሉ ይናገራሉ።

“አንድ ቀን አባቴ ለብቻዬ ጠርተውኝ ‘ልጄ’ አሉኝ። ‘ልጄ እኔ በሕይወቴ አንድ ክፋት ሠርቻለሁ’ አሉኝ። ምንድነው? ብዬ ጠየኩ። ‘በወጣትን ዘመኔ አንዲት ልጅ አግብቼ ነበር።ከዚያች ሴት ጋር በፍቅር እያለን ድንገት ተጣልተን ተለያየን።

“ስንለያይ ግን ከእኔ ጽንስ ሳትቋጥር የቀረች አይመስለኝም።ነገር ግን ያ ጽንስ በሕይወት ይኑር፣ ይሙት፣ ቀይ ይሁን ጥቁር ምንም አላውቅም።እኔም ይሄን ሁሉ ጊዜ የተፈጠረውን ነገር ለማወቅ አልፈለኩም። እባክህ ልጄ ፈልግልኝ’ አሉኝ።”

ዕድሜ ልካቸውን የአባታቸው የበኩር ልጅ እንደሆኑ ያውቁ ለነበሩት አቶ ቢቲማ ይህ የአባታቸው ምስጢር ትልቅ ግርታን ፈጠረባቸው።

አባታቸውንም ለምን ይህን ምስጢር እስካሁን ደብቀው እንደቆዩ ሲጠይቋቸው፤ እውነቱን ቢናገሩ ከሁለተኛ ባለቤታቸው ጋር ንትርክ ይፈጠራል እንዲሁም የሁለቱ ቤተሰብ ልጆች ላይግባቡ ይችላሉ በሚል ስጋት እንደሆነ ገልጸዋል።

“የአባቴ የመጀመሪያ ሚስት ስም በዳቱ እንደሚባል እና ትዳር መስርታ ልትኖር የምትችልበትን ቦታ ከነገሩኝ በኋላ ‘እዚያ መኖሯን ፈልግ፣ የመጀመሪያ ልጇ ወንድ ወይም ሴት መሆኑን አጣራ’ አሉኝ” ይላል ቢቲማ።

አቶ ደላስ ይህን ምስጢር ለልጃቸው ከተናገሩ ከስድስት ወራት በኋላ የመጀመሪያ ልጃቸውን መጨረሻ ሳይሰሙ በ2013 ዓ.ም. በ101 ዓመታቸው ማረፋቸውን ሰማሁ ይላል ልጃቸው።

ቤተሰብ

የአባት አደራ፤ ወንድምን ፍለጋ

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

አቶ ቢቲማ የአባታቸውን አደራ እስከሚፈጽሙ እረፍት አጡ።

ከአባታቸው ያገኙትን መረጃ በመያዝ የማያውቁትን የአባታቸውን የበኩር ልጅ፣ የእራሳቸውን ታላቅ ወንድም/እህት ፍለጋን ተያያዙ።

አባታቸው ወደነገሯቸው ወረዳ ሄደው ማጠያየቅ ጀመሩ። በሰዎች ጥቆማ ቶኬ ኩታዬ ወረዳ ወደ አንድ መንደር ሄዱ።እዚያ ሲደርሱም በዳቱ የተባሉት ሴት መሞታቸው ይነገራቸዋል።

አቶ ቢቲማ ወ/ሮ በዳቱ የተባሉት ሴት ትዳር ከመመሥረታቸው በፊት ልጅ ወልደው እንደሆነ ያጠያይቃሉ። ከሰዎች ያገኙት ምላሽ ‘አዎ’ የሚል ሆነ።

ከዚያ አባታቸው አቶ በዳቱ ከሁለተኛው ትዳራቸው በፊት የወለዱትን ልጅ ማንነትን ሲያጠያይቁ፣ አምቦ ወረዳ ዳሴ በሚባል አካባቢ እንደሚኖሩ ተነገራቸው።

አቶ ቢቲማ ይህን መረጃ ይዘው ቀጣይ ጉዟቸውን ወደ ተባሉበት ቦታ አደረጉ።

“የተባልኩበት ቦታ ሄጄ የሚኖሩበት መንደር ደርስኩ።ግን ማነጋገር ፈራሁ። ምን ብዬ ላናግር?” ይላሉ የአባታቸው የመጀመሪያ ልጅ እንዲሁም ታላቅ ወንድማቸውን ማንነትን መለየት የቻሉት አቶ ቢቲማ።

ወንድማቸውን ፊት ለፊት ሄደው የማናገር አቅም ያጡት አቶ ቢቲማ፣ የወንድማቸውን ስልክ ከጎረቤት ተቀብለው ወደመኖሪያቸው ተመለሱ።

“ቤት ከገባሁ በኋላ ‘እኔ ወንድምህ ነኝ’ ብዬ ታሪኩን በዝርዝር በስልክ ነገርኩት” የሚሉት አቶ ቢቲማ፣ ከወንድማቸው ያልጠበቁትን ምላሽ ነበር ያገኙት።

“‘ከእኔ ምን ትፈልጋለህ? ለምን ደወልክልኝ?’ ብሎ ተቆጣኝ። በአካል ተገናኝተን እናውራ፣ ስለው ‘ከእኔ ምን ትፈልጋለሁ? ልትገድለኝ ነው?’ ብሎ እንቢ አለ።”

አቶ ቢቲማ ከማያውቁት ወንድማቸው ጋር ለመገናኘት ያደረጉት ጥረት ባይሳካም ተስፋ አልቆረጡም። የአባታቸውን አደራ ለመፈጸም፤ ታላቅ ወንድማቸውን ለማግኘትም ደግመው ደጋግመው ከመደወል አልቦዘኑም።

በመጨረሻም ተሳክቶላቸው ጉደር በተባለ ከተማ ቀጠሮ ያዙ። አቶ ቢቲማ በቀጠሮው መሠረት ጉደር ላይ ሲገናኙ ሰውዬው የአባታቸው ልጅ ስለመሆናቸው ምስክር አላስፈለጋቸውም ነበር።

“ይህ ሰው የአባቴ አምሳያ ነው።ቅንድባቸው አንድ አይነት ነው። ዐይናቸው የአባቴን ዐይን ይመስላል። አፍንጫቸው ከአባቴ አፍንጫ ጋር አንድ አይነት ነው።መዳፎቻቸው ሁሉ ተመሳሳይ ነው” ይላሉ አቶ ቢቲማ።

“ተቀጣጥረን ስንገናኝ በዕድሜ የገፉ ሆነው አገኘኋቸው። ‘እናትዎ የመጀመሪያ ትዳር እንደነበራቸው ያውቃሉ ወይ?’ ብዬ ጠየኳቸው።ጊምቢ በሚባል ቦታ አግብተው እንደነበር እንጂ ከዚያ ውጪ ምንም እንደማያውቁ ነገሩኝ” ይላሉ አቶ ቢቲማ።

ቤተሰብ

አቶ ቢቲማ የታላቅ ወንድማቸው ስም ከራ እንደሚባል፤ ዕድገታቸውም በእናታቸው በኩል ካሉት አያቶቻቸው ጋር እንደሆነ እንዲሁም እናታቸው ስለ አባታቸው ምንም አይነት ነገር እንዳልነገሯቸው ይረዳሉ።

ከዚህ በተጨማሪ አቶ ከራ 71 ዓመታትን በምድር ላይ ሲኖሩ ወንድም እና እህት እንደሌላቸው ነበር የሚያውቁት።አቶ ከራ በአያቶቻቸው ቤት ብቻቸውን ቢያድጉም ቤተሰብ መሥርተው የልጅ ልጆች አይተው 21 ቤተሰብ አፍርተዋል።

“የአባቴን አደራ ላለመብላት እና ወንድሜ ስለሆንክ ነው የፈለግኩህ፣ አንተ ብታረጅም ልጆች አሉህ። እነርሱ ይፈላለጋሉ” አልኳቸው” ይላሉ አቶ ቢቲማ።

አቶ ቢቲማ ወንድም በማግኘታቸው ተደስተው በባሕሉ መሠረት ድግስ ደግሰው የሁለቱን ቤተሰብ በአንድ ላይ ጠርተው የቤተሰብ ትውውቅ ተደረገ።

“ቤተሰቡን ሁሉ ጠራ። እኔም ቤተሰቤን በሙሉ ጠርቼ፣ በአንድ ቦታ ተገናኝተን ዝግጅት አድርገን ተዋወቅን። ለታላቅ ወንድሜ ሳር ሰጥተን፣ መርቀን፤ ጋቢ አልብሰን እጅ ነስተን ተቀበልን።”

“አባቴ ምስጢር ደብቆ ቢቆይም ቃሉን ፈጽሜ ለጠፋው ጥፋት እንደ ቤተሰብ ይቅርታ ተጠያይቀን።”

የ71 ዓመቱ አቶ ከራ ለቢቢሲ አፋን ኦሮሞ የተሰማቸውን ሲገልጹ “ዕድሜዬን ያለ ወንድም እና እህት በብቸኝነት ጨርሼ በመጨረሻም ቢሆን ወንድም በማግኘቴ ደስተኛ ነኝ” ብለዋል።

“ይህ ትልቅ ደስታ ነው። በጣም ነው ደስ ያለኝ። በሕይወት እያለሁ ይህን ከማየት ወጪ ሌላ ምን የሚያስደስት ነገር አለ?” በማለት ተናግረዋል።