በሞቃዲሾው ፍንዳታ የሟቾች ቁጥር 100 ሲደርስ የተጎዱት ደግሞ ከ300 በላይ ሆነዋል

በፍንዳታዎቹ የወደሙ ተሸካርካሪዎች

የፎቶው ባለመብት, AFP

በሶማሊያ መዲና ሞቃዲሾ በተፈጸሙ ሁለት የቦምብ ጥቃቶች የሟቾች ቁጥር ቢያንስ 100 መሆኑን ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼይክ ሞሐሙድ ገለጹ።

ባሳለፍነው ቅዳሜ ጥቅምት 19/2015 ዓ.ም. የሰዎች እንቅስቃሴ በሚበዛበት ቦታ መኪና ላይ የተጠመዱ ሁለት ቦምቦች ፈንድተው ከ100 በላይ ሰዎችን ገድለው ከ300 በላይ አቁስለዋል።

ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼይክ መሐሙድ በዚህ ጥቃት ከተገደሉት መካከል “በእናቶቻቸው እቅፍ ላይ የነበሩ ሕጻናት ይገኙበታል” ስለማለታቸው የፈረንሳይ የዜና ወኪል ዘግቧል።

ፕሬዝዳንቱ በጥቃቱ የተጎዱ 300 ሰዎችን ለማከም ዓለም አቀፍ ትብብርን ጠይቀዋል። የዓለም ጤና ድርጅት ለፕሬዝዳንቱ ጥሪ ምላሽ ሰጥቷል።

የአገሪቱን የትምህርት ሚንስቴር ዒላማ ላደረገው ጥቃት ተጠያቂው አል-ሸባብ መሆኑን ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል።

ለጂሃዲስት ቡድኑ ቅርበት ያለው ድረ-ገጽ አል-ሸባብ ለጥቃቱ ኃላፊነቱን እንደሚወስድ አስነብቧል።

ከአል-ቃይዳ ጋር ትስስር ያለው አል-ሸባብ ከሶማሊያ ፌደራል መንግሥት ጋር ለበርካታ ዓመታት የዘለቀ ጦርነት ውስጥ ይገኛል።

ይህ ቡድን ሰኔ 2014 ዓ.ም. ሞቃዲሾ በሚገኝ ዝነኛ ሆቴል ላይ ጥቃት አድርሶ 21 ሰዎች ከተገደሉ በኋላ ወደ ስልጣን በቅርቡ የመጡት ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼይክ ሞሐሙድ በአል-ሸባብ ላይ “ጦርነት” አውጀው ነበር።

ከትናንት በስቲያ ቅዳሜ ያጋጠሙት ሁለቱ ፍንዳታዎች የተፈጸሙት በጥቂት ደቂቃዎች ልዩነት ነበር። መኪና ላይ ተጠምደው የነበሩት ቦምቦች ፍንድተው በአካባቢዎች የነበሩ ሕንጻዎችን እና ተሸከርካሪዎችን አውድመዋል።

የመጀመሪያው ፍንዳታ የትምህርት ሚንስቴርን የመታ ሲሆን ሁለተኛ ፍንዳታ ደግሞ የደረሰው የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች በፍንዳታው ቦታ እንደደረሱ መሆኑን ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።

ከአምስት ዓመት በፊት በዚህ ቦታ ላይ ከባድ መኪና ላይ የተጠመደ ቦምብ ፈንድቶ 500 ሰዎች ተገድለው ነበር። ይህ ጥቃት በአገሪቱ ታሪክ በርካታ ሰዎችን የገደለ ሆኖ ተመዝግቧል።

ጥቃቶቹ ካጋጠሙ በኋላ ቤተሰብ የጠፋቸው በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ፍንዳታዎቹ ባጋጠሙባቸው ቦታዎች ሰዎችን ሲፈልጉ ታይተዋል።

ከሟቾቹ መካከል አንድ እውቅ ጋዜጠኛ እና ከፍተኛ የፖሊስ መኮንን እንደሚገኙበት ተገልጿል።

አሜሪካ፣ ቱርክ፣ ኳታር እና ጀርመን ጥቃቱን አውግዘዋል። የአፍሪካ ኅብረት ደግሞ ይህ ጥቃት አል-ሸባብን ለማጥፋት ወታደራዊ እርምጃው ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት የሚያሳይ ነው ብሏል።

አል-ሸባብ በአፍሪካ ኅብረት የሚደገፈውን የሶማሊያ መንግሥት ገርስሶ ስልጣን ለመያዝ ባለፉት 15 ዓመታት ሲዋጋ ቆይቷል።

ቡድኑ በአሁኑ ወቅት ሰፊውን መካከለኛ እና ደቡባዊ ሶማሊያ ተቆጣጥሮ ይገኛል።