ዩናይትድ ኪንግደም፣ፈረንሳይ እና ጀርመን በኢራን ላይ እንደገና ማዕቀብ ሊጥሉ ነው

የኢራኑን ፕሬዚደንት አያቶላህ አሊ ኻሜኒን ፎቶ የያዙ ሰልፈኞች

የፎቶው ባለመብት, EPA

ዩናይትድ ኪንግደም፣ ፈረንሳይ እና ጀርመን በአውሮፓውያኑ 2015 ስምምነት መሠረት ተነስቶ የነበረውን የተባበሩት መንግሥታት ማዕቀቦችን በኢራን ላይ እንደገና ለመጣል እንቅስቃሴ ጀመሩ።

አገራቱ ሒደቱን የጀመሩት ከቴህራን የኒውክሌር ፕሮግራም ጋር በተያያዘ ያለው ውጥረት እንደገና በመባባሱ ነው።

እርምጃው ኢራን በ30 ቀናት ውስጥ እንደገና በማዕቀብ ሥር እንድትሆን ሊያደርግ ይችላል።

የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ለአውሮፓ ኅብረት የፖሊሲ ጉዳዮች ኃላፊ በጻፉት ደብዳቤ፣ ሦስቱ አገራት ማዕቀቡን እንደገና ለመመለስ "ሕጋዊ ሥልጣን የላቸውም" ሲሉ የገለጹ ሲሆን፣ሩሲያ እና ቻይና የኢራንን አቋም እንደሚደግፉ አመልክተዋል።

ሚኒስትሩ ጨምረውም አወዛጋቢ በሆነው የኒውክሌር ፕሮግራም ላይ ሌሎች አካላት "በጎነት እና ቁርጠኝነት" ካሳዩ ኢራን "ፍትሐዊ እና ሚዛናዊ" የሆነ ድርድር ለመጀመር ዝግጁ መሆኗን በደብዳቤያቸው ላይ አሳውቀዋል።

በ2015 በተደረሰው የኒውክሌር ስምምነት የተሳተፉት ሦስቱ የአውሮፓ አገራት፣ ኢራን እስከ ነሐሴ መጨረሻ ድረስ ዲፕሎማሲያዊ መፍትሔ ላይ ካልደረሰች ማዕቀቡን እንደገና ለመመለስ እየተዘጋጁ እንደሆነ ያስጠነቀቁት ከሁለት ሳምንት በፊት ነበር።

የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርም እርምጃው ከዓለም አቀፉ የአውቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ ጋር እየተካሄደ ያለውን ጥረት "ያሳንሳል" ሲሉ እርምጃውን "ተንኳሽ እና አላስፈላጊ ማባባስ" ሲሉ ገልጸውታል።

የኒውክሌር ፕሮግራሟን በተመለከተ በኢራን እና በአሜሪካ መካከል ሲደረግ የነበረው ንግግር አሜሪካ የኢራን የኒውክሌር ጣቢያዎችን ከደበደበች እና ኢራን የተባበሩት መንግሥታት ተቆጣጣሪዎች ወደ ጣቢያዎቹ እንዳይገቡ ከከለከለችበት ሰኔ ወር ጀምሮ አልቀጠለም።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ኢራን የኒውክሌር ፕሮግራሟን እንድታቆም ከአሜሪካ፣ ከፈረንሳይ፣ ከጀርመን፣ ከቻይና እና ከአውሮፓ ኅብረት ጋር በደረሰችው እና በተባበሩት መንግሥታት በተደገፈው ስምምነት ምክንያት ለዓመታት ተጥሎባት የቆየው የኢኮኖሚ ማዕቀብ ተነስቶላት ነበር።

ሆኖም ዶናልድ ትራምፕ በመጀመሪያው የሥልጣን ዘመናቸው አሜሪካን ከስምምነቱ ካስወጡ በኋላ በኢራን ላይ እንደገና ማዕቀብ ጥለዋል። ኢራንም በምላሹ የኒውክሌር ፕሮግራሟን የቀጠለች ሲሆን፣ ይህም አዲስ ቀውስ እንዲፈጠር አድርጓል።

በኢራን ላይ እንደገና ማዕቀብ ለመጣል የተወሰደው እርምጃ በ2015 ስምምነት ላይ የተመሠረተ ሲሆን፣ የስምምነቱ ተሳታፊዎች ኢራን የኒውክሌር ፕሮግራሟን በተመለከተ የገባችውን ስምምነት አልጠበቀችም ብለው ካመኑ ለፀጥታው ምክር ቤት በማሳወቅ ማዕቀቡን እንዲመልሱ ይፈቅድላቸዋል።

በዚህም መሠረት ኢ3 በመባል የሚታወቁት ዩኬ፣ ፈረንሳይ እና ጀርመን ይህንኑ በሚመለከት ሐሙስ ዕለት ለፀጥታው ምክር ቤት ደብዳቤ በማስገባት እርምጃቸውን ጀምረዋል።

ደብዳቤው ኢራን በ2015 የተገባውን የኒውክሌር ስምምነት አለማክበሯ "ግልጽ እና ሆነ ተብሎ የተደረገ " እንደሆነ ገልጿል።

ጨምሮም ኢራን ለምታበለጽገው ከፍተኛ የዩራኒየም ክምችት "ምንም ዓይነት ሰላማዊ ምክንያት አልበራትም ፤ ዩራኒየም የምታጣራው የጦር መሣሪያ ለማምረት ነው።ይህም ለዓለም አቀፍ ሰላም እና ደኅነንት ስጋት ሆኗል" ብሏል።

ሆኖም አገራቱ በሚቀጥሉት 30 ቀናት ኢራን ስምምነቱን እንድታከብር ዲፕሎማሲያዊ ጥረታቸውን እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።

የብሪታኒያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴቪድ ላሚ እንዳሉት በቅርቡ ዩኬ እና አጋሮቿ ለኢራን የተወሰኑ ሁኔታዎችን በማስቀመጥ የማዕቀብ እፎይታዋን አራዝመውላታል።

ሆኖም ኢራን እነዚህን ሁኔታዎች ለማሟላት "የሚጨበጥ ጥረት አላደረገችም፤ በተደጋጋሚ የኒውክሌር ፕሮግራሟን ምንነት በተመለከተ ማረጋገጫ መስጠት አልቻለችም" ብለዋል ሚኒስትሩ።

የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ ይህንን ያስተባበለ ሲሆን፣ የቀደመውን ስምምነት ለማክበር እና መፍትሔ ለመፈለግ ለዲፕሎማሲያዊ ጥረት ያለውን ቁርጠኝነት ማሳየቱን ገልጿል።

ኢራን ከሌሎች የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት አባላት ጋር ለመነጋገር ዝግጁ መሆኗን በመግለጽም ማዕቀቡን ለመመለስ የተወሰደው እርምጃ ውድቅ እንዲደረግ አሳስቧል።

አሜሪካ በበኩሏ ማዕቀቡን ለመመለስ የተወሰደውን እርምጃ በበጎ የተቀበለችው ሲሆን፣ ተግባራዊ እንዲሆን ከሦስቱ የአውሮፓ አገራት ጋር እንደምትሠራ ገልጻለች።

"በተመሳሳይ ጊዜም አሜሪካ ሰላማዊ እና ለኢራን የኒውክሌር ጉዳይ ዘላቂ እልባት ለመስጠት ከኢራን ጋር በቀጥታ ለመነጋገር ዝግጁ ናት" ሲሉ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ቃል አቀባይ ተናግረዋል።

ምዕራባውያን አገራት እና ዓለም አቀፉ የአውቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ የኢራን የኒውክሌር ፕሮግራሟ ሲቪል (ሰላማዊ) ጥቅም እንዳለው አላመኑም።

ኢራን ግን የኒውክሌር ጦር መሳሪያ እንደማትፈልግ እና የኒውክሌር ፕሮግራሟ ፍፁም ሰላማዊ እንደሆነ በተደጋጋሚ ገልጻለች።