ክሪፕቶከረንሲዎች ለከፍተኛ ኪሳራ እንደተጋለጡ የግብይት ባለሙያዎች አስጠነቀቁ

ክሪፕቶከረንሲ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ክሪፕቶከረንሲን ጨምሮ ሌሎችም የበይነ መረብ ገንዘብ ማዘዋወሪያዎች አደጋ እንዳንዣበበባቸው የሆንግ ኮንግን የግብይት ተንታኞች ማስጠንቀቂያ ሰጡ።

“ኢንቨስተሮች ከፍተኛ አደጋ ማንዣበቡን ይገንዘቡ” ሲል 'ሴኪውሪቲስ ኤንድ ፊውቸርስ' ኮሚሽን የተባለው የባለሙያዎች ማኅበር አሳውቋል።

ማስጠንቀቂያውን የተሰጠው የክሪፕቶከረንሲ ገበያ በውዝግብ በተሞላበት ጊዜ ነው።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ የኤፍቲኤክስ ክሪፕቶከረንሲ መሥራች ሳም ባንክማን-ፍሬድ በዚህ ሳምንት ታስሮ ክስ ተመሥርቶበታል።

“አንዳንድ የበይነ መረብ ሀብት ማከማቻዎች [virtual asset] በመርኅ አይመሩም። እንደ ባንክ ተቀማጭ ሒሳብም አይወሰዱም። ስለዚህ ኢንቨስተሮች ለገንዘባቸው ከለላ የላቸውም” ሲሉ ባለሙያዎቹ አስጠንቅቀዋል።

“ኢንቨስተሮች እነዚህን አሠራሮች የማይረዷቸው ከሆነ ኪሳራ ሊገጥማቸው ስለሚችል ኢንቨስት እንዲያደርጉ አይመከርም” ሲሉም አክለዋል።

የኤፍቲኤክስ ክሪፕቶከረንሲ መሥራች ሳም ባንክማን-ፍሬድ ባህማስ ውስጥ በተያዘ በሰዓታት ውስጥ የአሜሪካ አመራሮች በአገሪቱ ታሪክ “ከፍተኛው የፋይናንስ ማጭበርበር” ክስ መስርተውበታል።

የሆንግ ኮንጉ ማኅበር ሊቀ መንበር ጌሪ ጊንስለር “ሳም በማጭበርበር ነው ቢዝነሱን ያዳበረው” ብለዋል።

ሳም በዋስ ለመለቀቅ ቢጠይቅም አልተፈቀደለትም።

የኤፍቲኤክስ ክሪፕቶከረንሲ ተፎካካሪ የሆነው ቢናንስ፣ ለተወሰነ ጊዜ መቋረጡን ተከትሎ ባለፉት 24 ሰዓታት ውስጥ በክሪፕቶከረንሲው ኢንቨስት ተደርጎ የነበረ ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ ተነስቷል።

የብሎክቼይን መረጃ ተቋም የሆነው ናንሳን እንደሚለው፣ የዓለም ትልቁ ክሪፕቶከረንሲ 1.9 ቢሊዮን ዶላር ተቀንሶበታል።

የቢናንስ ዋና ኃላፊ ቻንፔንግ ዛሆ ግን የተቀነሰው ገንዘብ ወደ 1.4 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ነው ብሏል።

“አንዳንድ ቀን ገንዘብ ይቀነሳል (ወጪ ይደረጋል)። በሌላ ቀን ደግሞ ገንዘብ ይጨመራል (ገቢ ይደረጋል)። ይሄ የተለመደ የንግድ አካሄድ ነው” ሲል አክሏል።

የበይነ መረብ ገንዘቡ ክሪፕቶከረንሲ በተለዋዋጭ የገቢ ሁኔታ ዋጋው ከፍና ዝቅ ሲል ቆይቷል። ትልቁ ክሪፕቶከረንሲ የሆነው ቢትኮይን ዘንድሮ 60 በመቶ ኪሳራ ገጥሞታል። ሌሎች ክሪፕቶከረንሲዎችም ገቢያቸው አሽቆልቁሏል።

የገንዘብ ምንጭና ገንዘቡ የሚቀመጥበት ቦታ አለመታወቅ እንዲሁም ከመንግሥታት ቁጥጥር ውጪ መሆኑ፣ እንደ አደንዛዥ እጽ እና እገታ ያሉ ወንጀሎችን ያበረታታል የሚል ስጋት ይደመጣል።