መስክ የዓለማችን ቁጥር አንድ ባለፀጋነት ደረጃውን ተነጠቀ

ኤሎን መስክ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ኤሎን መስክ

ኤሎን መስክ በዚህ ዓመት በኤሌክትሪክ መኪና አምራቹ ቴስላ ውስጥ የነበረው የድርሻ ዋጋ ቅናሽ በማሳየቱ የዓለማን ቁጥር አንድ ባለፀጋነት ቦታን ተነጥቋል።

እንደ ፎርብስ እና ብሉምበርግ ከሆነ መስክ የአንደኛነት ደረጃው በበርናርድ አርኖልት ተወስዶበታል።

በርናርድ አርኖልት የቅንጡ ምርቶች አምራች ኩባንያ የሆነው ኤልቪኤምኤች ዋና ሥራ አስኪያጅ ናቸው።

መስክ የኤሌክትሪክ መኪና አምራቹ ቴስላ ዋና ሥራ አስኪያጅ እና 14 በመቶ ከፍተኛው ድርሻ ባለቤት ነው።

ከጥቂት ወራት በፊት በ44 ቢሊዮን ዶላር ግዙፉን ማኅበራዊ ሚዲያ ትዊተርን መግዛቱ ይታወሳል።

እንደ ፎርብስ ከሆነ በአሁኑ ወቅት የመስክ ንብረት 178 ቢሊዮን ዶላር ይገመታል። ፈረንሳዊው በርናርድ አርኖልት ደግሞ ያላቸው ጠቅላላ ንብረት 188 በሊዮን ዶላር ነው።

አርኖልት የሚመሩት ኤልቪኤምኤች እንደ ሉዊ ቪቶን፣ ሲፎራ፣ ቲፋኒ & ኮ እና ዲዮር ያሉ ቅንጡ ምርቶች አምራች ኩባንያዎችን ያስተዳድራል።

መስክ ትዊተርን ለመግዛት በቴስላ ካለው ድርሻ በቢሊዮን ዶላር የሚገመተውን እንደሸጠ ተመላክቷል።

ከዚህ በተጨማሪ የቴስላ የኤሌክትሪክ መኪና ገበያው መቀዛቀዝ መስክ በመኪና አምራቹ የነበረው ድርሻ ቀንሶ የዓለም ባለፀጋነት ደረጃን አሳጥቶታል።

የዘርፉ ባለሙያዎች እንደሚሉት ምጣሄ ሃብት መዳከሙ፣ የብድር ወለድ ከፍተኛ መሆኑ እና ሌሎች የኤሌክትሪክ መኪና አምራች ኩባንያዎች ምርቶቻቸውን ተፎካካሪ ማድረጋቸው ሰዎች በቴስላ ላይ ገንዘባቸውን ፈሰስ ከማድረግ እንዲቆጠቡ ምክንያት እየሆናቸው ነው።

ፈረንሳያዊው በርናድር አርኖልት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ፈረንሳያዊው በርናድር አርኖልት

ፈረንሳዊው እና አሜሪካዊውን ባለሃብቶች ተከትለው በሦስተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ሕንዳዊው ጎይታም አዳኒ ናቸው። በመሠረተ ልማት እና በሸቀጦች ንግድ ላይ የተሰማሩት አዳኒ የተጣራ ንብረታቸው 135 ቢሊዮን ዶላር ይገመታል።

4ኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት ደግሞ የአማዞኑ ባለቤት ጄፍ ቤዞስ ናቸው። የብሉ ኦሪጅን እና የዋሽንግተን ፖስት ባለቤት የሆኑት አሜሪካዊው ባለፀጋ 116 ቢሊዮን የተጣራ ሃብት እንዳላቸው ፎርብስ አስነብቧል።

5ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ደግሞ ዋረን በፌት ናቸው። ገና በ11 ዓመታችው የገበያ ድርሻ ገዝተው በ13 ዓመታቸው ግብር መክፈል የጀመሩት ባለሃብት ካለኝ ንብረት 99 በመቶውን እሰጣለሁ ብለዋል።

አሜሪካዊው እስካሁን ድረስ 49 ቢሊዮን ዶላር ለበጎ አድራጊ ድርጅቶች ሰጥተዋል።