አርጀንቲና በሜሲ እየተመራች ለዓለም ዋንጫ ፍጻሜ ደረሰች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የኳታሩ 2022 የዓለም ዋንጫ ትናንት ማክሰኞ ምሽት በግማሽ ፍጻሜ ፍልሚያ አርጀንቲናን ከክሮሺያ አገናኝቶ በሜሲ የምትመራው ደቡብ አሜሪካዊት አገር ለፍጻሜ ማለፏን አረጋግጣለች።
ሊዮኔል ሜሲ እና ጁሊያን አልቫሬዝ ድንቅ ሆነው ባመሹበት ጨዋታ አርጀንቲና ተጋጣሚዋን ክሮሺያን 3ለ0 በሆነ ውጤት አሸንፋለች።
ሜሲ በትናንቱ ጨዋታ 5ኛውን የውድድሩን ጎል ከፍጹም ቅጣት ምት ያስቆጠረ ሲሆን ጎል የሆነ ኳስ ደግሞ በአስደናቂ ሁኔታ ለቡድን አጋሩ አልቫሬዝ አመቻችቶ አቀብሏል።
የማንችስተር ሲቲ አጥቂ አልቫሬዝ ሁለት ጎሎችን አስቆጥሯል።
ዛሬ ምሽት በሚከናወነው የግማሽ ፍጻሜ ፍልሚያ የፈረንሳይ እና ሞሮኮ አሸናፊ የፊታችን ዕሁድ ለዋንጫው ከአርጀንቲና ጋር የሚገናኝ ይሆናል።
የሜሲ የመጨረሻው የዓለም ዋንጫ
ይህን ዋንጫ ማንሳት ለሜሲ የሞት ሽረት ጉዳይ ነው።
ድንቅ የሚባለው የእግር ኳስ ሕይወቱ ሙሉ መልክ የሚኖረው የዓለም ዋንጫውን ከብሔራዊ ቡድኑ ጋር ሲያነሳ ነው።
ሜሲ በግሉ እና ከቡድኑ ጋር አስደናቂ ስኬቶችን አጣጥሟል።
በዓለማን ለምርጡ እግር ኳሰኛ የሚሰጠውን የባለንዶር ሽልማት ሪኮርድ በሆነ 7 ጊዜ ተቀብሏል። የፊፋ የወንዶች ምርጡ ተጫዋች ሽልማትንም ወስዷል።
በክለቡ ደግሞ አራት ጊዜ የአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ ዋንጫን አንስቷል። 11 የኮፓ አሜሪካን ጨምሮ ትልቅ ቦታ የሚሰጣቸው ውድድሮችን አሸንፏል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ድንቅ የሆነው እግር ኳሰኛ አንድ ያላሳከው ነገር አለ። ይህም የዓለም ዋንጫ ነው። ይህን ደግሞ ለማሳካት ያለው ዕድል አንድ ነው።
እርሱም የፊታችን እሁድ ከብሔራዊ ቡድኑ ጋር የሚያደርገው ጨዋታ የመጨረሻው የዓለም ዋንጫ እንደሚሆን ያምናል።
የ35 ዓመቱ እግር ኳሰኛ “ቀጣዩ የዓለም ዋንጫ እስኪመጣ ብዙ ዓመታት ይወስዳል። ያን ማድረግ (በቀጣዩ የዓለም ዋንጫ ተሰልፎ መጫወት) የምችል አይመስለኝም። በዚህ መልኩ መጨረሱ አስደናቂ ይሆናል” ብሏል።
በመጀመሪያው የምድብ ጨዋታዋ በሳኡዲ አረቢያ ስትሸነፍ ደጋፊዎችን ጥርጣሬ ወስጥ ከትታ የነበረችው አርጀንቲና ከዛ ጨዋታ በኋላ ባከናወነቻቸውን ጨዋታዎች ጥሩ ሊባል በሚችል ብቃት ተጋጣሚዎቿን ረትታ እዚህ ደርሳለች።
ቡድኑ በዚህ የዓለም ዋንጫ ካደረጋቸው አምስት ጨዋታዎች አራቱን አሸንፏል። በጥሎ ማለፍ የኔዘርላንድስ ብሔራዊ ቡድንን ያሸነፈ ሲሆን በምድብ ድልድል ደግሞ ሜክሲኮን እና ፖላንድን ረትቷል።












