በአምስተርዳም “የሐጢያት ሰፈር” ካናቢስ ማጨስ ሊከለከል ነው

ሬድ ላይት ዲስትሪክት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ሬድ ላይት ዲስትሪክት የሚባለው ሰፈር በወሲብ ንግድና በካናቢስ ዝናው የናኘ ነው

በኔዘርላንድስ ዋና ከተማ አምስተርዳም በሚገኘው እና “ሬድ ላይት ዲስትሪክት” በሚል በስፋት በሚታወቀው ሰፈር ካናቢስ (ሃሺሽ) ማጨስ ሊከለከል ነው።

ይህ ሥፍራ መጠጥ፣ ዕጽ እና ሌሎች ነገሮች በስፋት የሚገኙበት አካባቢ ሲሆን ይህ ስፍራ የወሲብ ንግድ እና በካናቢስ መዝናናት የሚዘወተርበት ነበር።

በዓለም የቱሪስት መዳረሻዎች አንዱ የሆነው ይህ ሰፈር ሰዎች ያለ ቅጥ ለመዝናናት ሲሹ የሚሰለፉበት ሰፈር ነው።

ይህ የአምስተርዳም ክፍል ካናቢስ ማጨስ ሕጋዊ ሆኖ ቆይቷል።

አሁን ግን ከግንቦት አጋማሽ ጀምሮ ካናቢስ ማጨስ ወንጀል ሆኖ ተደንግጓል።

የከተማዋ አስተዳደር እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው ነዋሪዎች “የሰላም እንቅልፍ በዐይናችን ከዞረ ሰነበት” ሲሉ አቤት በማለታቸው ነው።

ከመላው ዓለም ቱሪስቶች ለመዝናናት ይህን ስፍራ ያዘውትሩታል።

ከበርካታ አገራት በወሲብ ንግድ የተሰማሩ ሰዎችም በዚህ ስፍራ ገላቸውን እየሸጡ ይኖራሉ።

አሁን ግን 24 ሰዓት መሥራት አትችሉም ነው የተባሉት።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

አዲሱ ሕግን ተከትሎ የወሲብ ንግድ ላይ የተሰማሩ ሴቶች ሌሊት ዘጠኝ ሰዓት ሲሆን ሥራ ማቆም ይኖርባቸዋል።

ምግብ ቤቶች እና መጠጥ ቤቶች ደግሞ ከሌሊቱ 8 ሰዓት በኋላ መሥራት እንደማይችሉ ተደንግጓል።

አሁን ባለው ሕግ በዚህ ሰፈር ውስጥ መጠጥ ቤቶች ከሐሙስ እስከ እሑድ ከቀኑ 10፡00 ሰዓት በኋላ አስካሪ መጠጥ መሸጥ አይችሉም።

በአዲሱ ሕግ ደግሞ ጭራሽ ከዚህ ሰዓት በኋላ ማንኛውም የአልኮል መጠጥ በአካባቢው እንዳይሸጥ ተደንግጓል። የመጠጥ ቤት መደርደሪያዎችም ከባልኮኒዎቻቸው የመጠጥ ጠርሙሶችን ማንሳት ይገደዳሉ።

በአምስተርዳም በአብዛኛዎቹ የሕዝብ አደባባዮች አስካሪ መጠጦችን መጠጣት ክልክል ነው።

የደቾች ከተማ አምስተርዳም በዓመት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ቱሪስቶችን መሳብ ያስቻላትና ‘የሐጢያት ከተማ’ ያስባላት ይኸው ዝነኛው የከተማዋ ሰፈር ነው።

በዚህ ሰፈር የሚገኙ ቴያትር ቤቶችም የልቅ ወሲብ ተንቀሳቃሽ ፊልሞችን ለሕዝብ በይፋ ሲያሳዩ ቆይተዋል።

ካናቢስን በኬክ መልክ መሸጥም በዚህ ሰፈር የሚገኙ ቡና ቤቶች ዕለታዊ ተግባር ነበር።

ይሁንና የአካባቢው ነዋሪዎች ለዓመታት ለመንግሥት አቤት ሲሉ ነው የኖሩት። ሰላማችንን አጥተናል፤ ወንጀል ተበራክቷል ይላሉ።

ይህን የአምስተርዳም ሰፈር ከዚህ ተግባር እናቅበው ወይስ አናቅበው የሚለው ክርክር በፖለቲከኞች ዘንድ ሲያከራክር ዓመታትን አስቆጥሯል።

አሁን ባለው የኔዘርላነድ ሐግ ካናቢስን መያዝ፣ ማምረት እና መሸጥ ወንጀል ነው። ይሁንና ከ18 ዓመት በላይ የሆነ ሰው ካናቢስ ቢጠቀም ግን ወንጀል አይደለም።

ምንም እንኳ በአገሪቱ ካናቢስን መያዝም መሸጥም ሕገ ወጥ ቢሆንም፣ ኔዘርላንድስ ሬድ ላይት ዲስትሪክት ቡና ቤቶች ውስጥ ግን ካናቢስ እንዲሸጥ ትታገስ ነበር።

በዚህ የተነሳ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ቱሪስቶች ለወሲብ እና ለካናቢስ ሲሉ የአምስተርዳምን ‘የሐጢያት ሰፈር’ ያዘወትሩ ነበር።

ይህን አዲስ ክልከላ ሕግ ተከትሎ የከተማዋ ገቢ በከፍተኛ ሁኔታ ሊያሽቆለቁል እንደሚችል ይገመታል።