የትራምፕን ውሳኔ ተከትሎ አሜሪካ ከአባልነት የመውጣት ዕቅዷን እንድታጤነው የዓለም ጤና ድርጅት ጠየቀ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ዶናልድ ትራምፕ በመጀመሪያው የሥልጣን ቀናቸው አሜሪካ ከዓለም ጤና ድርጅት አባልነት እንድትወጣ የማድረግ ውሳኔያቸውን እንዲያጤኑት ተቋሙ ጠየቀ።
ድርጅቱ ዛሬ ጥር 13/2017 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ አሜሪካ ከድርጅቱ አባልነት ለመውጣት መፈለጓ እንዳሳዘነው ገልጾ፣ ውሳኔውን መለስ ብሎ በማጤና በአባልነቷ ትቀጥላለች የሚል ተስፋ እንዳለው ገልጿል።
ድርጅቱ ይህን ያለው 47ኛው የአሜሪካ ፕሬዝደንት ሆነው ቃለ መሃላ የፈፀሙት ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አገራቸው ከዓለም ጤና ድርጅት መውጣት የሚያስችላትን ሂደት ለመጀመር የሥራ አስፈፃሚ ትዕዛዝ ከፈረሙ በኋላ ነው።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ወደ ዋይት ሐውስ በተመልሱ ዕለት ሰነዱን ሲያጸድቁ "ይህ ትልቅ ነገር ነው" ብለዋል። በመጀመሪያው የሥልጣን ቀናቸው ፊርማቸውን ካስቀመጡባቸው በደርዘን ከሚቆጠሩ እርምጃዎች መካከልም አንዱ ሆኗል።
ትራምፕ ከዓለም ጤና ድርጅት አሜሪካ እንድትወጣ ትዕዛዝ ሲሰጡ ይህ ለሁለተኛ ጊዜ ነው።
ትራምፕ ዓለም አቀፉ ድርጅት ኮቪድ-19ን ለመከላከል ያደረገው ጥረት ላይ ተቃውሞ ነበራቸው። ወረርሽኙ በተከሰተበት ወቅትም መቀመጫውን ጄኔቫ ካደረገው ተቋም የመውጣት ሂደት ቢጀምሩም ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ውሳኔውን ቀልብሰውታል።
ይህንን ውሳኔ በመጀመሪያው የሥራ ቀናቸው መፈረማቸው አሜሪካ ከዓለም አቀፉ ተቋም በይፋ የመውጣት ዕድሏን ከፍ አድርጎታል።
የዓለም ጤና ድርጅትን በመጥቀስ "እንድንመለስ ስለሚፈልጉ የሚሆነውን እናያለን" ሲሉ ትራምፕ በጽህፈት ቤታቸው ተናግረዋል። ይህም አሜሪካ ልትመለስ እንደምትችል ፍንጭ የሰጠ ሆኗል።
"ድርጅቱ ከዉሃን፣ ቻይና የተነሳው እና ሌሎች ዓለም አቀፍ የጤና ቀውሶች ያስከተለውን የኮቪድ-19 ወረርሽኝን በተሳሳተ መንገድ በመያዙ፤ አስቸኳይ ማሻሻያዎችን ባለማድረጉ እና ከዓለም ጤና ድርጅት አባል አገራት ፖለቲካዊ ተጽእኖ ነፃነቱን ማሳየት ባለመቻሉ" አሜሪካ ለመልቀቅ መንገድ መጀመሯን ትዕዛዙ ገልጿል።
ዩናይትድ ስቴትስ የተባበሩት መንግሥታት አካል ለሆነው የዓለም ጤና ድርጅት የምትሰጠው "ፍትሃዊ ያልሆነ ከባድ ክፍያ" ውጤት መሆኑንም የሥራ አስፈጻሚ ትዕዛዙ አክሏል።
ትራምፕ በመጀመሪያው ፕሬዝዳንትነት ዘመናቸው ድርጅቱ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን በመዋጋት ረገድ "ቻይናን ያማከለ" አሠራር ይከተላል ሲሉ ተችተው ነበር።
የዓለም ጤና ድርጅት ወረርሽኙ በተከሰተበት ወቅት መመሪያ የሚሰጥበት መንገድም ለቻይና ያዳላ ነው ሲሉ ትራምፕ ከሰው ነበር።
የዓለም ጤና ድርጅት በበኩሉ በኤክስ ገጹ ባጋራው መግለጫው የበሽታዎችን ምንጭ በመለየት፣ ጠንካራ የጤና ሥርዓት በመገንባት፣ አስቸኳይ የጤና አደጋዎችን በመለየት እና ምላሽ በመስጠት የአሜሪካውያንን ጨምሮ የዓለም ሕዝቦችን ጤና እና ደኅንነት ለመጠበቅ ወሳኝ ሚና እንደተጫወተ ጠቅሷል።
በመሆኑም አሜሪካ ውሳኔዋን እንደምታጤነው ተስፋ እንደሚያደርግ ገልጾ፣ በዓለም ላሉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ጤና እና ደኅንነት ሲባል በአሜሪካ እና በተቋሙ መካከል ያለውን ለአስርተ ዓመታት የዘለቀ አጋርነት ጠብቆ ለማቆየት ፍሬያማ ውይይት ለማድርግ ዝግጁ መሆኑን ገልጿል።
በባይደን አስተዳደር ወቅት አሜሪካ የዓለም ጤና ድርጅት ትልቁ ገንዘብ ሰጪ ሆና ቆይታለች። እአአ በ2023 ከድርጅቱ በጀት አንድ አምስተኛ የሚሆነውን አበርክታለች።
የድርጅቱ ዓመታዊ በጀት 6.8 ቢሊዮን ዶላር ነው።
የሕብረተሰብ ጤና ባለሙያዎች ትራምፕ ከዓለም ጤና ድርጅት ለቀው ለመውጣት መወሰናቸውን በመተቸት በአሜሪካውያን ጤና ላይ መዘዝ ሊኖር እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።
አንዳንዶች ደግሞ እርምጃው እንደወባ፣ ሳንባ እና ኤችአይቪ እንዲሁም ኤድስን የመሳሰሉ ተላላፊ በሽታዎችን በመዋጋት ረገድ የተገኘውን ለውጥ ሊቀለበስ እንደሚችል ጠቁመዋል።
ቀደም ሲል በፕሬዝዳንት ባይደን አስተዳደር የኮቪድ -19 ምላሽ አስተባባሪ ሆነው የሠሩት አሺሽ ጃሃ "በዓለም ዙሪያ ያሉትን ሰዎች ጤና ብቻ ሳይሆን የአሜሪካን አመራር እና ሳይንሳዊ ችሎታን ይጎዳል" ሲሉ ከዚህ ቀደም አስጠንቅቀዋል።
የዓለም አቀፍ የሕብረተሰብ ጤና ባለሙያ እና የጆርጅታውን ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር የሆኑት ሎውረንስ ጎስቲን በበኩላቸው "ይህ ከባድ ውሳኔ ነው። በዓለም ጤና ላይ ከባድ ቁስል ቢፈጥርም ግን በአሜሪካ ላይ የሚፈጥረው ጥልቅ የሆነ ቁስል ነው" ብለዋል።












