ድንበር ላይ የአስቸኳይ ጊዜ ያወጁት ትራምፕ አሜሪካ ውስጥ መወለድ ዜግነት አያስገኝም አሉ

ዶናልድ ትራምፕ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ማክሰኞ ጥር 12/2017 የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ሆነው የተሾሙት ዶናልድ ትራምፕ በመጀመሪያው ቀናቸው በርካታ ውሳኔዎችን አሳልፈዋል።

በአሜሪካ ድንበሮች ላይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ያወጁት ትራምፕ በተለይ በሜክሲኮ ድንበር በኩል ያለው ጥበቃ እንዲጠናከር አዘዋል።

ከዚህ በተጨማሪ አሜሪካ ውስጥ የሚወለዱ የስደተኛ ልጆች ዜግነት የሚያስገኝላቸው መብት እንዲነሳም አዘዋል። ነገር ግን ይህ ውሳኔያቸው ሕጋዊ ካልሆነ ተፈፃሚ አይሆንም የሚሉ ብዙዎች ናቸው።

ትራምፕ ምርጫ ካሸነፉ በኋላ የባይደን አስተዳደር ፖሊሲዎች "በአምስት ደቂቃ ውስጥ እንደሚሻሩ" ቃል ገብተው እንደነበር ይታወሳል።

በሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች ጥገኝነት ለመጠየቅ የነበራቸው ቀጠሮ ተሰርዟል። ይህ የሆነው ጥገኝነት የሚጠየቅበት መተግበሪያ በትራምፕ ትዕዛዝ ከጥቅም ውጭ እንዲሆን በመደረጉ ነው።

በአውሮፓውያኑ ጥር 2023 ሥራ የጀመረው ይህ የሞባይል ስልክ መተግበሪያ በሜክሲኮ ድንበር በኩል የሚገቡ ስደተኞች ጥገኝነት የሚጠይቁበት ነው። ነገር ግን የትራምፕ አስተዳደር ሥልጣን ከጨበጠበት ደቂቃ ጀምሮ መተግበሪያው ከጥቅም ውጭ ሆኗል።

ሲቢኤስ የተባለው የቢቢሲ አጋር ሚድያ እንደዘገበው በሚጥሉት ሶስት ሳምንታት 30 ሺህ ስደተኞች ይህን መተግበሪያ ተጠቅመው ጥገኝነት ለመጠየቅ ቀጠሮ ይዘው ነበር።

ትራምፕ በዓለ ሲመታቸው ላይ ባሰሙት ንግግር "በሕገ ወጥ መንገድ መግባት ከዚህ በኋላ አበቃ" እንዲሁም በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ "ሕገ ወጥ ስደተኞች" ይባረራሉ ሲሉ ቃል ገብተዋል።

አዲሱ ፕሬዝደንት የሜክሲኮ የዕፅ አዘዋዋሪ ቡድኖችን ሽብርተኞች ናቸው ሲሉ ፈርጀዋል።

ትራምፕ የባይደን አስተዳደር ተግባራዊ ያደርጋቸው የነበሩ 80 ያክል መመሪያዎችን ሰርዘዋል።

በካፒቶል ሂል በነበረው በዓለ ሲመት "እኔ ሀገሬን ከዛቻ እና ከወረራ ከመጠበቅ ውጭ ሌላ ምን የተሻለ ኃላፊነት የለብኝም" ሲሉ ተናግረው ነበር።

የትራምፕ አስተዳደር ባለሥልጣናት እንደሚሉት መከላከያ ሚኒስቴሩ ድንበር እንዲጠብቅ ተጨማሪ የሰው ኃይል እንዲሁም ድሮንን የመሳሰሉ ቴክኖሎጂዎች ይመደባሉ።

ትራምፕ ካስተላለፏቸው ውሳኔዎች ሕጋዊ ፈተና ይገጥመዋል ተብሎ የሚጠበቀው በመወለድ የሚገኝ ዜግነት ነው። ይህ ማለት ሕጋዊ ወረቀት ከሌላቸው ስደተኞች አሜሪካ ውስጥ የሚወለዱ ሕፃናት ዜግነት ያገኛሉ ማለት ነው።

ትራምፕ ይህን አስቀራለሁ ብለዋል። እንዴት ሊያስቀሩት እንደሚችሉ ግን ዝርዝር መረጃ አልሰጡም።

ማንኛውም ሰው አሜሪካ ውስጥ ከተወለደ አሜሪካዊ ዜግነት ያገኛል ሲል የሀገሪቱ ሕገ መንግሥት ይደነግጋል። ይህ ድንጋጌ ለመቀየር የኮንግረሱ ሁለት ሶስተኛ አባላት ይሁንታ መስጠት አለባቸው። ትራምፕ ይህ እንዴት ያሳኩታል የሚለው ግልፅ አይደለም።