ትራምፕ ቃለ መሐላ መፈጸማቸውን ተከትሎ ስደተኞችን ማባረር እና ግዛት ማስፋፋትን ተግባራዊ እንደሚያደርጉ ተናገሩ

ትራምፕ ቃለ መሐላ ሲፈጽሙ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ትራምፕ ቃለ መሐላ ሲፈጽሙ

በአሜሪካ ባለፈው ኅዳር ወር የተካሄደውን ምርጫ ያሸነፉት ዶናልድ ትራምፕ ዋሺንግተን ውስጥ በተካሄደ ሥነ ሥርዓት ቃለ መሐላ ፈጽመው የፕሬዝዳንትነት ሥልጣኑን ተረከቡ።

ትራምፕ ከአራት ዓመት በፊት 45ኛ ፕሬዝዳንት ሆነው አሜሪካን ከመሩ በኋላ በጆ ባይደን ተሸንፈው ከመንበራቸው ተሰናብተው ከቆዩ በኋላ ነው በአስደናቂ ሁኔታ በድጋሚ ተመርጠው ለሁለተኛ እና ለመጨረሻ ዙር የሥልጣን ዘመን ወደ ሥልጣን የተመለሱት።

በከፍተኛ ቅዝቃዜ ምክንያት በዋይት ሐውስ ውስጥ የተወሰኑ ተጋባዦች በተገኙበት በተካሄደው ሲመተ በዓል ላይ ዶናልድ ትራምፕ እና ጄዲ ቫንስ ፕሬዝዳንት እና ምክትል ፕሬዝዳንት ሆነው ቃለ መሐላቸውን ፈጽመዋል።

ሰኞ ጥር 12/2017 ዓ.ም. በዋሽንግተን ሰዓት አቆጣጠር እኩለ ቀን ላይ በተካሄደው የፕሬዝዳንት ሲመተ በዓል ላይ የቀድሞዎቹ የአሜሪካ ፕሬዝዳንቶች ቢል ክሊንተን፣ ዶርጅ ደብሊው ቡሽ፣ ባራክ ኦባማ እና ተሰናባቹ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ታድመዋል።

የቀድሞው ፕሬዝደንት ጆ ባይደን እና የትራምፕ ተፎካካሪ የነበሩት ምክትላቸው ካማላ ሐሪስ ወደ አዳራሹ ሲገቡ ጭብጨባ ተደርጎላቸዋል።

የትራምፕ የቅርብ አጋሮች የሆኑት ቢልየነሮቹ ሊላን መስክ፣ ጄፍ ቤዞስ፣ ማርክ ዙከርበርግ፣ ሰንደር ፒቺ እና ሎውረን ሳንቼዝም በዓለ ሲመቱን ታድመዋል።

ትራምፕ በሜክሲኮ ድንበር አቅራቢያ "ብሔራዊ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ" ያወጁ ሲሆን፣ ወደ አሜሪካ "በሕገ ወጥ መንገድ መግባት ይቆማል" ብለዋል።

ትራምፕ በመጀመሪያው ንግግራቸው ቀደም ሲል ሲናገሩት እንደነበረው በአሜሪካ ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ሕገወጥ ስደተኞች ከአገሪቱ እንደሚያናርሩ ገልጸዋል።

በተጨማሪም የፓናማ ካናልን መልሰው በአመሪካ ቁጥጥር ሥር እንሚያስገቡ እንዲሁም፣ የአገራቸው ሰንደቅ ዓላማ በማርስ ላይ እንደሚውለበለብ አመልክተዋል።

በተጨማሪም በእሳቸው የአስተዳደር ዘመን በአሜሪካ ውስጥ ዕውቅና የሚኖራቸው ሁለት ፆታዎች እነሱም ወንድ እና ሴት ብቻ እንደሚሆኑ ተናግረዋል።

"ወንጀለኛ መጤዎች ወደ መጡበት ይመለሳሉ" ሲሉም ትራምፕ ተደምጠዋል።

ትራምፕ በተጨማሪም አደገኛ ዕፅ አዘዋዋሪዎችን "አሸባሪ" ብለው ፈርጀዋል።

ትራምፕ ምጣኔ ሀብተን፣ ሕግን፣ ዓለም አቀፍ ግንኙነትን እና ሌሎችንም ቁልፍ ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርገው ሲናገሩ ከታዳሚው ሞቅ ጭብጨባ ተለግሷቸዋል።

ምክትል ፕሬዝዳንት ቫንስ ቃለ መሐላ ሲፈጽሙ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ምክትል ፕሬዝዳንት ቫንስ ቃለ መሐላ ሲፈጽሙ

47ኛው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ሆነው ቃለ መሐላ ከፈጸሙ በኋላ ባሉት ሰዓታት ውስጥ "ብዙ ነገር እንደሚቀይሩ" የገቡትን ቃል እንደሚተገብሩ ይጠበቃል።

እንደ ሕገ ወጥ ስደት፣ የአየር ንብረት ለውጥ ሕግጋት፣ ምሥጢራዊ ሰነዶች እና ሌሎች ጉዳዮች ላይ ያነጣጠሩ መሆናቸውን ትራምፕ ገልጸዋል።

ትራምፕ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ዶናልድ ትራምፕ ባደረጉት ንግግር የቀድሞውን ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን እና ምክትላቸውን ካማላ ሐሪስ አስመልክተው "የአሜሪካ ወርቃማ ዘመን አሁን ይጀምራል" ብለዋል።

"ከዚህ ቀን በኋላ አገራችን ታድጋለች፣ ትከበራለች፣ አሜሪካ ትቀድማለች" ብለዋል።

ትራምፕ በዓለ ሲመታቸው በሚከናወንበት የካፒቶል ሂል አዳራሽ አካባቢ በደጋፊዎቻቸው ተሞልቷል። ከዜሮ በታች 5 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ቅዝቃዜ ቢኖርም የትራምፕን ንግግር ለመስማት ደጋፊዎቻቸው ተሰባስበዋል።

ከትራምፕ ደጋፊዎች አንዷ "የቤተሰብ ዋጋ የሚጠበቅባቸው" እርምጃዎች ይወሰዳሉ ብላ እንደምትጠብቅ ተናግራለች።

የቀድሞው ፕሬዝደንት ጆ ባይደን እና የትራምፕ ተፎካካሪ የነበሩት ምክትላቸው ካማላ ሀሪስ ወደ አዳራሹ ሲገቡ ጭብጨባ ተደርጎላቸዋል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የቀድሞው ፕሬዝደንት ጆ ባይደን እና የትራምፕ ተፎካካሪ የነበሩት ምክትላቸው ካማላ ሀሪስ ወደ አዳራሹ ሲገቡ ጭብጨባ ተደርጎላቸዋል

ትራምፕ ቃለ መሐላ ሲፈጽሙ ለአሜሪካ ያላቸውን የወደፊት ዕቅዶች ተናግረዋል።

"ሉዓላዊነታችንን መልሰን እናስከብራለን። ደኅንነታችን የተጠበቀ ይሆናል። የተዛባው ፍትሕ ይሰፍናል" ብለዋል።

"ዋና ግባችን ኩሩ አገር መገንባት ነው። ኩሩ፣ ነጻና የበለጸገች" ሲሉም አክለዋል።

የቀድሞዎቹ የአሜሪካ ፕሬዝዳንቶች ቢል ክሊንተን፣ ዶርጅ ደብሊው ቡሽ፣ ባራክ ኦባማ እና ተሰናባቹ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ታድመዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የቀድሞዎቹ የአሜሪካ ፕሬዝዳንቶች ቢል ክሊንተን፣ ዶርጅ ደብሊው ቡሽ፣ ባራክ ኦባማ እና ተሰናባቹ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ታድመዋል።

ትራምፕ በንግግራቸው የቀድሞውን ፕሬዝዳንት ባይደን አስተዳደር ተችተዋል። በተለይም በስደተኞች ጉዳይ ቀውስ መከሰቱን ተናግረዋል።

"እነዚህ ችግሮች ይፈታሉ። አሜሪካ በሙሰኛ አስተዳደር ስትፈተን ነበር" ብለዋል ትራምፕ።

የቀድሞው አስተዳደር "ለአደገኛ ወንጀለኞች" መጠለያ ሰጥቷል ሲሉ ከሰው በዚህም ምክንያት "አሁን በአገራችን ትንሹንም ችግር የማንፈታ ሆነናል" ብለዋል።

የትራምፕ የቅርብ አጋሮች የሆኑት ቢልየነሮቹ ኤሎን መስክ፣ ጄፍ ቤዞስ፣ ማርክ ዙከርበርግ፣ ሰንደር ፒቺ እና ሎውረን ሳንቼዝም በዓለ ሲመቱን ታድመዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የትራምፕ የቅርብ አጋሮች የሆኑት ቢልየነሮቹ ኤሎን መስክ፣ ጄፍ ቤዞስ፣ ማርክ ዙከርበርግ፣ ሰንደር ፒቺ እና ሎውረን ሳንቼዝም በዓለ ሲመቱን ታድመዋል።

የአሜሪካ ማሽቆልቆል "አብቅቷል" ያሉት አዲሱ ፕሬዝዳንት ትራምፕ በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት የተደረገባቸውን የግድያ ሙከራ አስታውሰው የአገሪቱ "ታላቅ እጣ ፈንታ አይቀሬ ነው" ብለዋል።

"አንዳንዶች ሊያስቆሙን ሞክረዋል። ነጻነቴንና ሕይወቴን ሊነጥቁ ሞክረዋል። ሆኖም እግዚአብሔር ሕይወቴን ያተረፈው አሜሪካን ታላቅ እንዳደርግ ነው" ሲሉ ተደምጠዋል።

ትራምፕ በዓለ ሲመታቸው በሚከናወንበት የካፒቶል ሂል አዳራሽ አካባቢ በደጋፊዎቻቸው ተሞልቷል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ትራምፕ በዓለ ሲመታቸው በሚከናወንበት የካፒቶል ሂል አዳራሽ አካባቢ በደጋፊዎቻቸው ተሞልቷል።

ትራምፕ ምርጫውን ያሸነፉበትን ቀን "የነጻነት ቀን" ሲሉ ጠርተውታል።

መንግሥታቸው ቀውሶችን እንደሚፈታና "ለሁሉም ዜጎች፣ ያለ ቀለም፣ ሃይማኖች፣ ጎሳ ልዩነት ክብርና ጥንካሬ" እንደሚሰጥ ተናግረዋል።

በአሜሪካ የዋጋ ንረትንና የኃይል ማመንጫ ዘርፍ ቀውስን በተመለከተም ትራምፕ ንግግር አድርገዋል።

"የዋጋ ንረትን እናሸንፋለን። በፍጥነት የሸቀጦች ዋጋ ይቀንሳል። አሜሪካ ነዳጅ ለማግኘት ትቆፍራለች። አሜሪካ ዳግመኛ አምራች አገር ትሆናለች" ብለዋል ፕሬዝዳንቱ።

ትራምፕ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

አሜሪካን "በድጋሚ ሃብታም" አገር እንደሚያደርጓት ቃል የገቡት ፕሬዝዳንቱ ፖሊሲዎቻቸው ፆታና ቀለምን ያማከሉ እንደሆኑ ጠቅሰው "ያለ ቀለም መድልዎ" እንደሚሠራ ተናግረዋል።