ትራምፕ በመጀመሪያ የሥልጣን ቀናቸው በርካታ ትዕዛዞችን ለማስተላለፍ ቃል ገቡ

ትራምፕ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ትራምፕ ወደ ዋይት ሐውስ በመመለሻቸው ዋዜማ በመጀመሪያው የሥልጣን ቀናቸው በርካታ ትዕዛዞችን ለማስተላለፍ ቃል ገብተዋል።

ለደጋፊዎች ንግግር ያደረጉት ትራምፕ ቃለ መሐላ በፈፀሙ በጥቂት ሰዓታት ውስጥ "በታሪካዊ ፍጥነት እና ጥንካሬ" እንደሚንቀሳቀሱ ተናግረዋል።

በዋሺንግተን ዲሲ በሺዎች ለሚቆጠሩ ደጋፊዎች ንግግር ያደረጉት ተመራጩ ፕሬዝደንት በሚቀጥሉት አራት ዓመታት ሊሠሯቸው ያሰቧቸውን ተግባራት ዘርዝረው ካበቁ በኋላ ባለፈው ኅዳር ዲሞክራቶችን በምርጫ በመርታታቸው ደስታቸውን ሲገልፁ ተስተውለዋል።

ሪፐብሊካኑ ፖለቲከኛ ያላቸውን ፕሬዝደንታዊ ኃይል ተጠቅመው ስደተኞችን በገፍ ለማባረር፣ የተፈጥሮ ጥበቃ ላይ የሚያተኩሩ መመሪያዎችን ለመቀነስ እና የስብጥር (ዳይቨርሲቲ) ፕሮግራሞችን ለማስቆም ቃል ገብተዋል።

"ቅድሚያ የምንሰጠው ለአሜሪካ ነው። እሱ ደግሞ ነገ ይጀምራል" ሲሉ ለደጋፊዎቻቸው ተናግረዋል። አክለው "ነገ ቴሌቪዥን ስትመለከቱ እንደምትዝናኑ እርግጠኛ ነኝ" ብለዋል።

ትራምፕ ከበዓለ ሲመታቸው በኋላ 200 ገደማ ትዕዛዞች ላይ ፊርማቸውን እንደሚያሰፍሩ ይጠበቃል። አንዳንዶቹ ትዕዛዞች እንደ ሕግ የሚቆጠሩ ሲሆን ሌሎች ደግሞ ፕሬዝደንታዊ መመሪያዎች ናቸው።

"እኔ ሥልጣን በያዝኩ በጥቂት ሰዓታት ውስጥ የባይደን አስተዳደር ያስተላለፋቸው ትዕዛዞች ይሰረዛሉ" ብለዋል ትራምፕ።

አክለው የሰው ሰራሽ ክህሎትን ዕድገት የሚያፋጥን እንዲሁም ኢላን መስክ የሚመራው ዶጅ የተባለው መሥሪያ ቤት እንዲቋቋም የሚወጣ ትዕዛዝ እንደሚፈርሙ አሳውቀዋል።

አክለው በአውሮፓውያኑ 1963 ስለተገደሉት ጆን ኤፍ ኬኔዲ መረጃዎችን እንደሚለቁ፤ ወታደራዊ ኃይሉን 'አይረን ዶም' እንዲሠራ እንደሚያዙ እንዲሁም ብዝሀነት፣ እኩልነት እና አካታችነት የሚባሉ ፖሊሲዎችን ከጦር ሠራዊቱ እንደሚያስወግዱ ቃል ገብተዋል።

ለደጋፊዎቻቸው ባደረጉት ንግግር ፆታ የቀየሩ (ትራንስጀንደር) ሰዎች በሴቶች ስፖርት እንዳይሳተፉ እንደሚያደርጉ እና የትምህርትን ሥልጣን ለአሜሪካ ግዛቶች አሳልፈው እንደሚሰጡ ተናግረዋል።

"እናንተን በጣም ደስተኛ የሚያደርጉ ብዙ ትዕዛዞች ማየታችሁ አይቀርም" ብለዋል።

የአሜሪካ ፕሬዝደንቶች ሥልጣን ሲጨብጡ በመጀመሪያ ቀናቸው ትዕዛዝ ማስተላለፋቸው የተለመደ ቢሆንም ትራምፕ በቁጥር በርካታ ትዕዛዞችን ለማስተላለፍ ቃል ገብተዋል። አብዛኛዎቹም በፍርድ ቤት ሙግት እንደሚቀርብባቸው ይጠበቃል።

ትራምፕ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሕጋዊ ወረቀት የሌላቸውን ስደተኞች ከአሜሪካ እንደሚያባርሩ ቃል ገብተዋል።ገር ግን የስደት ተንታኞች የትራምፕ ዕቅድ ብዙ ሕጋዊ፣ የሎጂስቲክ፣ የገንዘብ እንዲሁም የፖለቲካ አንድምታ እንዳለው ይናገራሉ።

ትራምፕ በቤተሰቦቻቸው ታጅበው የቀረቡ ሲሆን ቢሊየነሩ ደጋፊያቸው ኢላን መስክ እና ሌሎች ታዋቂ አሜሪካዊያንም ተቀላቅለዋቸዋል።