ዩናይትድ ኪንግደም የሐማስ ታጋቾችን ለመፈለግ የቅኝት በረራዎችን ልታካሂድ ነው

የፎቶው ባለመብት, AFP
ዩናይትድ ኪንግደም የሐማስ ታጋቾች ያሉበትን ቦታ ለመፈለግ በመካከለኛው ምሥራቅ የቅኝት በረራዎች እንደምታካሂድ መከላከያ ሚኒስቴር አስታወቀ።
በረራዎቹ ታጋቾቹ የት እንዳሉ የሚጠቁሙ የደኅንነት መረጃዎችን ለመሰብሰብ ይረዳሉ ተብሏል።
ሐማስ በእስራኤል ላይ የፈፀመውን ጥቃት ተከትሎ አምስት የእንግሊዝ ዜጎች የጠፉ ሲሆን፣ የዩኬ መንግሥት ምን ያህሎቹ በሐማስ እገታ ሥር ሊሆኑ እንደሚችሉ አልገለጸም።
ሚኒስቴሩ “ የዜጎቻችን ደኅንነት ከሁሉም በላይ ቅድሚያ የምንሰጠው ጉዳይ ነው” ብሏል።
በመሆኑም ታጋቾችን ለማስለቀቅ እየተደረገ ያለውን እንቅስቃሴ ለማገዝ፣ ሚኒስቴሩ በጋዛ እና በእስራኤል የአየር ክልል ጨምሮ በምሥራቃዊ ሜዴትራኒያን የቅኝት በረራዎችን እንደሚያካሂድ ገልጿል።
ሚኒስቴሩ እንዳለው የቅኝት አውሮፕላኖቹ ያልታጠቁ እና ታጋቾቹ የት እንደሚገኙ የሚጠቁሙ ናቸው።
“ በቅኝቱ የሚሰበሰበው ታጋቾቹን ከማዳን ጋር የተገናኘው መረጃ ብቻ ጉዳዩ ለሚመለከታቸው ባለሥልጣናት ይተላለፋል” ብሏል።
አውሮፕላኖቹ ሮያል አየር ኃይል የደኅንነት መረጃዎችን ለመሰብሰብ የሚጠቀምበትን ሻዶው አር1ን እንደሚያካትትና ታጋቾቹ ሊገኙበት የሚችሉ ቦታዎችን በተመለከተ የሚሰበስበው መረጃም ለእስራኤል እንደሚተላለፍ የሚኒስቴሩ ባለሥልጣናት ተናግረዋል።
ከ130 በላይ ታጋቾች አሁንም በጋዛ እንደሚገኙ ይታሰባል።
የአሜሪካ መከላከያ መሥሪያ ቤት ፔንታገንም በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ ታጋቾችን ለመታደግ በተደረገው ጥረት ድጋፍ ለማድረግ በጋዛ ላይ ያልታጠቁ ዩኤቪ ሰው አልባ አውሮፕላኖችን አሰማርቶ እንደነበር ገልጿል።
“ አሜሪካ በጋዛ ሰማይ ላይ ያልታጠቁ ዩኤቪ በረራዎችን እያደረገች ነው። በተጨማሪም የእስራኤል አጋራችን ታጋቾችን ለማስለቀቅ በሚያደርገው ጥረት ምክር እና እርዳታ እየሰጠች ነው” ብሎ ነበር።
ለአንድ ሳምንት ከዘለቀ ጊዜያዊ ተኩስ አቁም በኋላ በሐማስ እና በእስራኤል መካከል ያለው ጦርነት ዐርብ ዕለት እንደገና ተጀምሯል።
የእስራኤል መከላከያ ኃይል በመጀመሪያው ቀን ከ400 በላይ የሐማስ ኢላማዎችን መምታቱን አስታውቋል።
በሐማስ የሚተዳደረው የጋዛ ጤና ሚኒስቴር በበኩሉ አዲስ በተጀመረው የእስራኤል ጥቃት ቢያንስ 193 ሰዎች ተገድለዋል ብሏል።
መስከረም መጨረሻ ላይ ሐማስ የእስራኤልን ድንበር ጥሶ በመግባት የፈፀመውንና ቢያንስ 1 ሺህ 200 ሰዎች የተገደሉበትን ጥቃት ተከትሎ እስራኤል በሐማስ ላይ እየወሰደችው ያለው የአጸፋ እርምጃ አጠናክራ ቀጥላለች።
በዚህም ጦርነቱ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ከ15 ሺህ 200 በላይ ፍልስጤማውያን መገደላቸውን በሐማስ የሚተዳደረው የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።












