ጦርነቱ ከጀመረ ወዲህ እስራኤል ከባድ የአየር ጥቃት መፈፀሟን ነዋሪዎች ተናገሩ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
እስራኤል በደቡባዊ ጋዛ በምትገኘው ኻን ዩኒስ ከተማ ከባድ የአየር ድብደባ ፈፀመች። የከተማዋ ነዋሪዎች ድብደባው ጦርነቱ ከጀመረ ወዲህ የከፋው ነው ብለዋል።
በከተማዋ ምሥራቃዊ አካባቢዎች የሚኖሩ ነዋሪዎችም አካባቢውን ለቀው ወደ ደቡባዊ ክፍል እንዲሄዱ በእስራኤል ጦር ተነግሯቸዋል።
እስራኤል የሰሜን ጋዛ ተፈናቃዮችን ባስጠለለችው በዚች ከተማ የተወሰኑ የሐማስ መሪዎች እንዳሉ ታምናለች።
በሐማስ የሚተዳደርው የጋዛ ጤና ሚኒስቴር አዲስ በተፈፀመው የእስራኤል የአየር ድብደባዎች ቢያንስ 193 ሰዎች ተገድለዋል ብሏል።
አርብ ዕለት የእስራኤል መከላከያ ኃይል መስከረም ወር መጨረሻ ላይ ሐማስ በእስራኤል ላይ ለፈፀመውና 1ሺህ 200 ሰዎች ለተገደሉበት ጥቃት አፀፋ፣ በሐማስ ላይ የሚፈፅመውን ጥቃት ከጊዜያዊ ተኩስ አቁሙ በኋላ እንደገና ጀምሯል።
በሐማስ የሚተዳደረው ጤና ሚኒስቴር እንዳለው እስካሁን በጋዛ የተገደሉ ሰዎች ቁጥር ከ15 ሺህ 200 በላይ ደርሷል።
የእስራኤል ጥቃት እንደገና የጀመረው በሐማስ እና በእስራኤል መካከል የተደረሰው ጊዜያዊ የተኩስ አቁም ስምምነት አርብ ዕለት ካበቃ በኋላ ነው።
ጦርነቱ እንደገና በጀመረበት የመጀመሪያው ቀን ከ400 በላይ የሐማስ የሽብር ኢላማዎች መምታቱን የእስራኤል መከላከያ ኃይል አስታውቋል።
ጦርነቱ ካገረሸበት ጊዜ አንስቶ ቅዳሜ አመሻሽ ላይ በቴል አቪቭ እና በማዕከላዊ እስራኤል አካባቢዎች ላይ የተፈፀመውን ድብደባ ጨምሮ ከጋዛ ወደ እስራኤል ሮኬቶች በተደጋጋሚ ተተኩሰዋል።
ይህንን ጥቃት ተከትሎም ከቴል አቪቭ በደቡባዊ ከፍል በምትገኘው ሆሎን ከተማ ውስጥ ቀላል ጉዳት ለደረሰበት የ22 ዓመት ወጣት ሕክምና መስጠቱን የእስራኤል የአምቡላንስ አገልግሎት ገልጿል።
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ ቅዳሜ ዕለት በሰጡት መግለጫም፣“ሐማስን ለማጥፋት እና የቀሩ ታጋቾችን ለማስለቀቅ ያስቀመጥነውን ግባችንን እስከምናሳካ ድረስ ወታደራዊ ዘመቻው ይቀጥላል” ብለዋል።
“ከባዱ ጦርነት ከፊታችን ያለው ነው” ሲሉም ተናግረዋል።
ከግብፅ ጋር የሚዋሰኑት ኻን ዮኒስ እና ራፋህ ከተሞች ከባድ የአየር ድብደባ ከተፈፀመባቸው አካባቢዎች ጥቂቶቹ ሲሆኑ ቀጣዩ የጥቃቱ ምዕራፍ በደቡብ ጋዛ ላይ ሊያተኩር እንደሚችልም ተነግሯል።
በመጀመሪያው የጦርነት ወቅት የእስራኤል ዋነኛ ኢላማ ከነበረው ሰሜን ጋዛ ወደ ደቡባዊ ጋዛ እንዲሸሹ ከተነገራቸው በኋላ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያን በአካባቢው ተጠልለው ይገኛሉ።
የእስራኤል መከላከያ ኃይል የአረብኛ ቋንቋ ቃል አቀባይ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ባጋሩትና ሰላማዊ ሰዎች የትኞቹን አካባቢዎች ለቀው መውጣት እንዳለባቸው በሚያመላክተው ካርታ ላይ በምሥራቅ ኻን ዩኒስ አካባቢ ወደ በደቡባዊዋ ራፋህ እንዲወጡ መመሪያ ሰጥተዋል።ይህም የምድር ጥቃት ሊፈፀም እንደሚችል አመላካች ነው ተብሏል።
ለሳምንታት በዘለቀው ጦርነት ምክንያት የቁሳቁስ እጥረት ያጋጠማቸው ሆስፒታሎችም በተጎዱ ሰዎች ተጨናንቀዋል። በኻን ዩኒስ ከተማ በሚገኘው ናስር ሆስፒታል ውስጥም የተወሰኑ ተጎጂዎች ባዶ ወለል ላይ ተኝተው ሲታከሙ ታይተዋል።
የአራት ልጆች እናት የሆነችው ሰሚራ፣ኻን ዩኒስ ከተማ ከደረሱ በኋላ በቆዩባቸው ስድስት ሳምንታት ውስጥ ካሳለፉት “አሰቃቂ ምሽቶች” አንደኛው መሆኑንና ጦሩ ኻን ዩኒስ ይገባሉ ብለው መስጋታቸውን ለሮይተርስ የዜና ወኪል ተናግራለች።
ቅዳሜ ዕለት በኻን ዩኒስ ከተማ የነበሩት የዩኒሴፍ ቃል አቀባይ ጀምስ ኢልደርም፣ ጥቃቱ ከመጀመሩ በፊትም ሆስፒታሎች በተጎጂዎች መጨናነቃቸውን ገልጸው፣ “በየመተላለፊያዎቹ ደም ይታያል፤ የተገደሉ የሚመስሉ ሕጻናትን የያዙ እናቶች አሉ” ሲሉ በሥፍራው ስላለው ሁኔታ ገልጸዋል።
በሌላ በኩል የፍልስጤም ቀይ ጨረቃ ቅዳሜ ዕለት ሰብዓዊ እርዳታ የጫኑ 100 ተሽከርካሪዎች ከግብፅ ወደ ጋዛ እንዲገቡ መፈቀዱን አረጋግጧል። አርብ ዕለት ወደ ግዛቱ የገባ ሰብዓዊ አቅርቦት አልነበረም።
በጋዛ የቀሩ እስራኤላውያን ታጋቾችን ለማስለቀቅ ሌላ ጊዜያዊ የተኩስ አቁም ስምምነት ለማድረግ የተደረገው ጥረትም ሳይሳካ ቀርቷል።
ለውይይቱ ቅርበት ያላቸው የፍልስጤም ባለሥልጣን ግን ምንም ዓይነት ግንኙነት አሊያም አዲስ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ለመድረስ ሙከራ ሳይደረግ ድርድሩ መቆሙን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
እስራኤልም ተደራዳሪዎቿን በኳታር ከሚካሄደው ድርድር ማስወጣቷን ቅዳሜ ዕለት አስታውቃለች።
የሐማስ የፖለቲካ ቢሮ ምክትል ኃላፊ ሳልህ አል አሮሪ፣ አሁን ላይ የሚካሄድ ድርድር አለመኖሩንና ጦርነቱ ካላበቃ በስተቀር ከእስራኤል ጋር የሚደረግ የእስረኞች ልውውጥ እንደማይኖር ቅዳሜ ዕለት ለአል ጀዚራ ተናግረዋል።
ኔታንያሁ ቅዳሜ ዕለት በሰጡት መግለጫቸው ሕጻናትና ሴቶችን ጨምሮ ታግተው የነበሩ 110 እስራኤላውያን እና የሌላ አገር ዜጎች መለቀቃቸውን አወድሰዋል።
ታጋቾቹ የተለቀቁት በእስራኤል ታስረው ከነበሩ 240 ፍልስጤማውያን እስረኞች ጋር በተደረገው ልውውጥ ነው።
ሆኖም አሁንም በጋዛ የቀሩት ወደ 140 የሚደርሱ ታጋቾች ያሉ ሲሆን ወንዶች እና የጦር ሰራተኞች መሆናቸው ተገልጿል።












