“በውሻ መነከስ፣ ድብደባ እና ምግብ መከልከል” የፍልስጤማውያን መከራ በእስራኤል እስር ቤቶች

የጋዛ የተኩስ አቁም ፋታ ለማድረግ በተደረሰው ስምምነት ከእስራኤል እስር ቤቶች የተፈቱ ፍልስጤማውያን ስቃይ እና ግፎች እንደደረሰባቸው ተናገሩ።
በእስራኤል እስር ቤቶች ውስጥ ውሻ ይለቀቅባቸው፣ ድብደባ ይፈጸምባቸው እንዲሁም ምግብ ይከለከሉ እንደነበር ለቢቢሲ ገልጸዋል።
የእስር ቤት ጠባቂዎቹ ልብሳቸውን እና ብርድ ልብሳቸውን በመግፈፍ የሚመገቡትነ ምግብም መሬት ላይ ይደፉባቸው ነበር ብለዋል።
በቅርቡ ከተለቀቁ ፍልስጤማውያን መካከል አንደኛዋ “እንደፍርሻለን” የሚል ዛቻ ከእስራኤላውያን መኮንኖች ደርሶብኛል ብላለች።
ጠባቂዎቹ ታሳሪዎቹ ማደሪያቸው ውስጥ ባሉበትም ወቅት አስለቃሽ ጭስ በመርጨት ስቃይ እንዳደረሱባቸው ለቢቢሲ አስረድተዋል።
ቢቢሲ ስድስት ፍልስጤማውያንን ያነጋገረ ሲሆን፣ ሁሉም በእስር ቤቶቹ ድብደባ እንደተፈጸመባቸው ተናግረዋል።
የፍልስጤም እስረኞች ማኅበር በበኩሉ አንዳንድ የእስር ቤቱ ጠባቂዎች እጃቸውን በካቴና በታሰሩ ፍልስጤማውያን እስረኞች ላይ ሽንታቸውን እንደሸኑባቸውም አስታውቋል።
ባለፉት ሰባት ሳምንታትም በእስራኤል እስር ቤቶች የነበሩ ስድስት ፍልስጤማውያን እስረኞች ሕይወታቸው እንዳለፈ ማኅበሩ አስታውቋል።
እስራኤል በበኩሏ በእስር ቤቶቿ ያሉት ፍልስጤማውያን በሕግ አግባብ እንደታያዙ ተናግራለች።
በሐማስ እና በእስራኤል መካከል ከተደረሰው የተኩስ አቁም ፋታ ጋር ተከትሎ በልውውጡ ከተፈቱት መካከል የ18 ዓመቱ መሐመድ ናዝል አንዱ ነው። መሐመድ ከነሐሴ ወር ጀምሮ ናፍሃ በተሰኘው እስር ቤት ታስሮ ነበር። በእነዚህ ወራት ውስጥም ክስ አልተመሠረተበትም። ለምን እንደታሰረም አያውቅም።
እስራኤል በወረራ በያዘቻት ዌስት ባንክ ውስጥ በጄኒን ከተማ እቅራቢያ በምትገኘው ቃባቲያ መንደር ወደሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው ቢቢሲን ጋብዞ ነበር።
ቢቢሲ መሐመድን ሲያገኘው ሁለቱም እጆቹ በፋሻ ተጠቅልሎ በዘመዶቹ ተከቦ ነበር።

ከመለቀቁ ከአስር ቀናት በፊት እስራኤላውያን የእስር ቤት ጠባቂዎች የድምጽ ማጉያ ይዘው መጥተው በታራሚዎቹ ክፍል ውስጥ ስማቸውን በመጥራት፣ በከፍተኛ ድምጽ በማደንቆር እና በመጮህ ሊተነኩሷቸው ሞክረዋል።
“ምንም ምላሽ ሳንሰጣቸው ስንቀር። ይደበድቡን ጀመር” ብሏል።
“ታዳጊዎች እና ወጣቶችን ከፊት እንዲሁም አረጋውያኑን ከኋላ አሰለፉን። እኔን ወሰዱኝ እና ይደበድቡኝ ጀመር። ጭንቅላቴን እንዳይመቱ እየተከላከልኩ ነበር፤ እነሱ ደግሞ እግሬን እና እጄን ለመስበር እየሞከሩ ነበር” ብሏል።
ከእስር ከተፈታ በኋላም በራማላህ ምርመራ የተደረገለትን የህክምና ምርመራዎች እንዲሁም የራጅ ውጤቶችን ቤተሰቡ ለቢቢሲ አሳይቷል።
የራጅ ውጤቶቹን በዩናይትድ ኪንግደም ያሉ ሁለት ዶክተሮች ያዩት ሲሆን፣ ሁለቱም እጆቹ ስብራት እንደገጠማቸው አረጋግጠዋል።
“መጀመሪያ ላይ በጣም ከፍተኛ ህመም ይሰማኝ ነበር። ከዚያ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ እንደተሰበሩ ሳውቅ እጆቼን መገልገል አቆምኩኝ። እጆቼን የምጠቀመው መጸዳጃ ቤት ስሄድ ብቻ ነው።”
ሌሎች እስረኞች ምግብ በማብላት፣ ውሃ በማጠጣት እንዲሁም መታጠቢያ ቤትም ሲገባ ያግዙት እንደነበር ይናገራል።
የእስር ቤት ጠባቂዎቹን እርዳታ ለመጠየቅ አልደፈረም፤ ምክንያቱም በድጋሚ ሊደበድቡኝ ይችላሉ በሚል ፍርሃት ነው።
የእስራኤል የእስር ቤት አገልግሎት በበኩሉ መሐመድ ላይ የተፈጸመውን ድብደባ ያልተቀበለ ሲሆን፣ ከእስር ቤት ከመውጣቱም በፊት ምርመራ ተደርጎለት ምንም ዓይነት የጤና ችግር አልነበረውም የሚል ምላሽ ሰጥቷል።
በተጨማሪም ታዳጊው ከእስር ቤት ወጥቶ በቀይ መስቀል አውቶብስ ውስጥ ሲገባ የሚያሳይ ቪዲዮ ያወጣው እስር ቤቱ መሐመድ ደረሰብኝ ያለው ሐሰት ነው ብሏል።
በቪዲዮው ላይ የመሐመድ እጆች በፋሻ አልተጠቀለሉም። ተንጠልጥለው የሚታዩ ይመስላሉ፤ ነገር ግን ቪዲዮው በደንብ አይታይም።
መሐመድ ከእስር ከወጣ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ሕክምና ያገኘው በቀይ መስቀል አውቶብስ ውስጥ እንደሆነም ለቢቢሲ ተናግሯል።
በራማላህ የሚገኘው ሆስፒታልም መሐመድ የእጆቹ ስብራት በራሱ መጠገን ካልቻለ ጠፍጣፋ ብረት መገጠም እንዳለበት በሕክምና ሪፖርቱ ላይ አስፍሯል።
የመሐመድን ታሪክ እንዲያረጋግጥ ቢቢሲ ቀይ መስቀልን የጠየቀ ሲሆን፣ ተቋሙም “በእስረኞች ላይ የሚያሳስብ የጤና እክሎች ካሉ በቀጥታ ካሰሩት ባለሥልጣናት ጋር እንነጋገራለን። በዚህ ውይይትም ምክንያት ስለ እያንዳንዱ ግለሰብ ጉዳይ በይፋ አናሳውቅም” የሚል ምላሽ ሰጥቷል።
የእስራኤል እስር ቤት ጠባቂዎች ባህርይ በተለይም መስከረም መጨረሻ ላይ ሐማስ ካደረሰው ጥቃት በኋላ እንደከፋ መሐመድ ያስረዳል። በእርግጫ፣ እንዲሁም በዱላ እንደበደቧቸው የሚያስረዳው መሐመድ አንድ ጠባቂም ፊቱን ረግጦታል።
“ውሾቻቸውን ይዘው በመምጣት እንዲያጠቁን ይለቁብንና ይደበድቡናል።”
“የምንተኛባቸውን ፍራሾች፣ ልብሳችንን፣ አውጥተው ጣሉት። ምግባችንን መሬት ላይ ደፉት። በርካቶች በፍርሃት ተዋጡ” ብሏል።
መሐመድ የደረሰበትንም ድብደባ በጀርባው እና በትከሻው የሚያሳዩ ቁስለቶች ለቢቢሲ አሳይቷል።
“ጥቃት ያደረሰብኝ ውሻ አፉ ስለታማ ጠርዝ ያለው ፍርግርግ ብረት አጥልቆ ነበር። ያጠለቀው ፍርግርግ ብረት እና ጥርሶቹ ያደረሰብኝ ጥቃት መላው ሰውነቴን አቁስሎታል” ሲልም የደረሰበትን ያስረዳል።

እንደነዚህ ዓይነት ድብደባዳዎች በመጊዶ እስር ቤት ሁለት ጊዜ የተፈጸመ ሲሆን፣ ወራትን ባሳለፈበት ናፍሃ እስር ቤት ለመቁጠር በሚያታክት ሁኔታ ይፈጸምባቸው ነበር።
የፍልስጤም እስረኞች ማኅበር ኃላፊ አብዱላህ አል ዛጋሪ ለቢቢሲ እንደተናገሩት በርካታ እስረኞች ፊታቸው እና አካላቸው ላይ ድብደባ እንደሚፈጸምባቸው መናገራቸውን ያስረዳሉ።
የእስራኤል ጠባቂዎች እጃቸውን በካቴና በታሰሩ ፍልስጤማዊ እስረኞች ላይ ሽንታቸውን ይሸኑባቸው እንደነበርም ከእስረኞች መስማታቸውን ገልጸዋል።
ለእነዚህ ክሶች ምላሽ እንዲሰጠው ቢቢሲ የእስራኤል እስር ቤትን የጠየቀ ሲሆን፣ በምላሹም እስረኞቹ መሠረታዊ መብታቸው ሳይጓደል በሕጋዊ አግባብ ተይዘዋል ብሏል።
“እነዚህን ክሶች አናውቃቸውም። እስረኞች እና በቁጥጥር ስር የዋሉ ግለሰቦች ባለሥልጣናት እንዲመረምሩት ቅሬታቸውን የማቅረብ መብት አላቸው” የሚል ምላሽ ሰጥቷል።
ሌላኛዋ ከእስራኤል እስር ቤት የተለቀቀችው ታዳጊ ላማ ካተር በበኩሏ አንድ እስራኤላዊ መኮንን “እደፍርሻለሁ” ብሎ እንደዛተባት በመግለጽ በማኅበራዊ ሚዲያዋ ላይ ቪዲዮ አጋርታለች።
ላማ ካተር ጥቅምት ወር አጋማሽ በቁጥጥር ስር ከዋለችም በኋላም እንዳስፈራሯት ተናግራለች።
“እጄ በካቴና ታስሮ ዐይኔን ሸፍነውት ነበር። እንደሚደፍሩኝ ዛቱ። አላማቸው እኔን ማስፈራራት እንደሆነ ግልጽ ነበር” ስትልም በወጣው ቪዲዮ ላይ ተናግራለች።
እስራኤል በበኩሏ ክሶቹ የመጡት ከጠበቃዋ እንደሆነ እና ታዳጊዋ ውድቅ ያደረጋቸው መሆኗን አስታውቃለች።
ታዳጊዋ በበኩሏ እሷን ጨምሮ ሌሎች ሴቶች የመደፈር ዛቻዎች እንደደረሰባቸው ለቢቢሲ ተናግራለች። በተጨማሪም በዳሞን እስር ቤት በነበረችበት ወቅት አስለቃሽ ጭሽ ጭምር እንደተጠቀሙባቸውም ገልጻለች።
የፍልስጤም እስረኞች ማኅበር ባለፉት ሰባት ሳምንታት በእስራኤል እስር ቤት የሚገኙ ፍልስጤማውያን ሞት ቁጥር መጨመሩን አስታውቋል። በእነዚህ ሳምንታትም ስድስት ፍልስጤማውያን መሞታቸውንም ገልጿል።
እስራኤል የእስረኞቹን ሞት አስመልክቶ በቀጥታ ባትመልስም ነገር ግን ባለፉት ሳምንታት አራት እስረኞች በተለያዩ ቀናት መሞታቸውን እንዲሁም የማረሚያ ቤቱ አገልግሎት ስለ ሞታቸው መንስዔ ምንም አያውቅም የሚል ምላሽ ሰጥታለች።
መሐመድ በእጆቹ ስብራት ምክንያት አሁንም ህመም እንደሚሰማው እና በተለይም ምሸት ላይ እንደማያስተኛው ይናገራል።
ወንድሙ ሙታዝ በበኩሉ መሐመድ ከእስር ቤት ከተመለሰ በኋላ የማያውቀው ሰው እንደሆነ ይናገራል።
“ይህ እኛ የምናውቀው መሐመድ አይደለም። ደፋር እና ጎብዝ ነበር። አሁን ልቡ ተሰብሮ በፍርሃት ተሞልቷል” ይላል።
በቅርቡ የእስራኤል ጦር በአቅራቢያቸው በምትገኘው ጄኒን ከተማ ላይ ወረራ ሲፈጽም “በከፍተኛ ፍርሃት እንደተዋጠ ይታይ ነበር” ሲልም ያለበትን ሁኔታ ገልጿል።
ሐማስ እና እስራኤል ጊዜያዊ የተኩስ አቁም ፋታ ባደረጉበት ቀናት በአራት ዙሮች 240 ሕጻናት እና ሴቶች ፍልስጤማውያን እስረኞች ተፈትተዋል።
በእስራኤል እስር ቤቶች 6704 ፍልስጤማውያን ታስረው እንደሚገኙ የመብት ተቋማት ያስታወቁ ሲሆን፣ ከእነዚህም ውስጥ ሁለት ሺህ ሰባ የሚሆኑት ፍርድ ቤት አልቀረቡም ወይም ክስ አልተመሠረተባቸውም።
“አስተዳደራዊ እስር” ተብሎ በሚጠራውም ሁኔታ በእስራኤል እስር ቤቶች እንደሚገኙ ሃሞኬድ የተባለው የእስራኤል የመብት ድርጅት አስታውቋል።
እስረኞቹ ድንጋይ መወርወርን ጨምሮ በግድያ ሙከራ እንደተጠረጠሩ ቢገለጽም በርካቶቹም ክስም ሳይመሠረትባቸው በእስር ቤቶች ቆይተዋል።
በዌስት ባንክ የሚኖሩ ፍልስጤማውያን ቤተሰቦች ቢያንስ አንድ የቤተሰብ አባላቸው በእስራኤል እስር ቤቶች ውስጥ ታስረው እንደሚገኙ ይታሰባል።
ፍልስጤማውያኑ በእስራኤል ውስጥ በመታሰራቸው ዘመዶቻቸው ወደ እስራኤል ሄደው መጎብኘት አይችሉም።
መስከረም መጨረሻ የደረሰውንም ጥቃት ተከትሎ በእስራኤል እስር ቤቶች ያለ ፍርድ የታሰሩ ፍልስጤማውያን ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩንም የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች አስታውቀዋል።












