የሕዝባቸውን ሰቆቃ በርቀት ሆነው እየተጋፈጡ ያሉት ፍልስጤማዊ አሜሪካውያን

ለፍልስጤም አጋርነት በዲሲ የተደረገ ሰልፍ

የፎቶው ባለመብት, EPA

የምስሉ መግለጫ, ለፍልስጤም አጋርነት በዲሲ የተደረገ ሰልፍ

ጋዛ እንዳልነበረች ሆናለች። ሕንጻዎች በደቂቃዎች ውስጥ ወደ ፍርስራሽነት ክምርነት ተቀይረዋል።

በሰባት ሳምንቱ ያላባራ የእስራኤል ጥቃት ከአስራ አራት ሺህ በላይ ፍልስጤማውያንም ረግፈዋል። ከተገደሉት ውስጥም አብዛኞቹ ሕጻናት ናቸው።

የጋዛ ሰርጥ ወደ ሕጻናት የመቃብር ስፍራነት እየተቀየረችም ነው ሲል የተባበሩት መንግሥታት የጦርነቱን ክፉኛ ገጽታ አሳይቷል።

በርካታ ወላጆች ሕጻናት ልጆቻቸውን ከፍርስራሾች ውስጥ ለማውጣት ሲታገሉም ዓለም በቴሌቪዥን መስኮት ተመልክቷል።

ክፉኛ የቆሰሉ ሕጻናት ሲንቀጠቀጡ እና ደማቸውን ሲያዘሩ የሚያሳዩ ቪዲዮዎች ወጥተዋል።

የእስራኤልን አገረ መንግሥት ምሥረታን ተከትሎ በዓለም ላይ የተበተኑ ፍልስጤማውያንም የሕዝባቸውን ሰቆቃ በርቀት ለመመልከት ተገደዋል።

ከጋዛ በብዙ ሺዎች ኪሎ ሜትሮች ርቀት ላይ ለሚኖሩ ፍልስጤማውያን ሐዘናቸው ጥልቅ ነው። ጥቃቶቹን ሲመለከቱ ሐዘን ብቻ ሳይሆን በስፍራው ተገኝቶ ያለመጋራቱም የጥፋተኝነት ስሜትም አለው።

“በርካታ ዳያስፖራ ፍልስጤማውያን የጥፋተኝነት ስሜት የሚሰማቸው ይመስለኛል። ፍልስጤማዊ በየትኛውም አገር ብንኖር ፍልስጤም በልባችን ውስጥ ናት፤ መቼም አትጠፋም” ሲል በቨርጂኒያ የሚኖረው ፍልስጤማዊ አሜሪካዊ ሙዚቀኛ አኔስ ይናገራል።

የ31 ዓመቱ ሙዚቀኛ በኢንስታግራም ላይ 1.7 ሚሊዮን ተከታዮች አሉት። ባለፉት ሰባት ሳምንታትም የጦርነቱን አስከፊ ገጽታ በማሳየት እንዲሁም የተኩስ አቁም ጥሪ በማድረግ ቆይቷል።

“የደረሰውን ጥፋት ስናይ፣ ግድያዎቹን ስንመለከት በእነሱ ቦታ እኛም ልሆን እንችል ነበር የሚል የጥፋተኝነት ስሜት የሚሰማን ይመስለኛል” ብሏል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ሐማስ መስከረም መጨረሻ ላይ በእስራኤል ላይ በከፈተው ጥቃት 1200 ሰዎች ተገድለዋል፣ እንዲሁም 240 ሰዎች ታግተዋል።

እስራኤል ለጥቃቱ ምላሽ ነው በሚል የማያባራ የአየር ጥቃት በጋዛ ሰርጥ ስታካሂድ ቆይታለች። እስራኤል ጥቃቶቹ በሐማስ ላይ ያነጣጠሩ ናቸው ብትልም የተባበሩት መንግሥታት “ሙሉ የቤተሰብ አባላትን እንዲሁም መንደሮችን የፈጀ ጥቃት ነው” ብሎታል።

በእነዚህም ጥቃቶች ከ14 ሺህ በላይ ፍልስጤማውያን ሲገደሉ በርካቶቹ ሕጻናት መሆናቸውን በሐማስ አስተዳደር ስር ያለው የጋዛ ጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።

ቢቢሲ ያነገገራቸው በርካታ ፍልስጤማዊ አሜሪካውያን በጋዛ እየሆነ ያለውን ነገር በማኅበራዊ ድረ ገጾች እና በቴሌቪዥን መመልከት መንፈሳቸውን እንደሰበረው ገልጸዋል።

“እያንዳንዱን የምታስደስተኝ ነገር፣ ትንሽም ይሁን ትልቅ በጋዛ ያሉ ፍልስጤማውያን አያገኙትም የሚለው ከሃሳቤ አይጠፋም” ይላል አኔስ።

“እቃ ለመግዛት ብወጣ የቦምብ ጥቃት አይጠብቀኝም። እራት ለመብላት ስሄድ የቦምብ ጥቃት አያስፈራኝም” ሲልም ያስረዳል።

በአሜሪካ ውስጥ ነዋሪ የሆኑ ፍልስጤማውያን ከአገራቸው በሺዎች ኪሎ ሜትሮች ርቀው ለምን ተገኙ? የሚለውም በራሱ የማይሽር ቁስል ነው።

በርካቶቹ ከዚህ ቀደም የተደረጉ ጦርነቶችን ሸሽተው እንዲሁም በአስገዳጅ ሁኔታ ተፈናቅለው የመጡ የፍልስጤማውያን ልጆች እንዲሁም የልጅ ልጆች ናቸው።

በዓለም ላይ ሰባት ሚሊዮን ፍልስጤማውያን ተበትነው ይኖራሉ። ከእነዚህም ውስጥ በኦሃዮ የተወለደችው ጂናን ዴና አንዷ ናት። እሰራኤል በአውሮፓውያኑ 1948 መመሥረቷን ተከትሎ በተካሄደው ጦርነት እንዲሁም ጠመንጃ ተደግኖባቸው ከቤታቸው እንዲወጡ ከተደረጉ ፍልስጤማውያን መካከል የጂናን ሴት አያት አንዷ ናቸው።

በዚህ ወቅት 750 ሺህ ፍልስጤማውያን ቀያቸውን፣ ቤታቸውን ለቀው እንዲወጡ አዲስ በተመሠረተው የእስራኤል መንግሥት ተገደዋል።

ይህንን አስገዳጅ አሰቃቂ መፈናቀል ፍልስጤማውያን ዘንድ ናቅባ ወይም 'መቅሰፍት' ብለው ይጠሩታል። የጂናንም አያቶች ከአገራቸው እና ከቤታቸው እንዲፈናቀሉ የተደረጉት በዚህ መንገድ ነው።

ቤተሰቦቿ በአውሮፓውያኑ 1981 ጠቅልለው ወደ አሜሪካ ከመምጣታቸው በፊት በዌስት ባንክ መኖሪያቸውን አድርገው ነበር። የጂናን እናትም የተወለደችው በዌስት ባንክ ነው።

“አንዳንድ ጊዜ እናቴ በዌስት ባንክ ብትቆይ እና በዚያው ተወልጄ ባድግ እንዴት ይሆን? ብዬ አስባለሁ” ትላለች።

ፍልስጤማዊ አሜሪካዊቷ ጂናን ዴና

የፎቶው ባለመብት, Chris Gale

የምስሉ መግለጫ, ፍልስጤማዊ አሜሪካዊቷ ጂናን ዴና

የ41 ዓመቷ ጂናን በዌስት ባንክ የክረምት ወቅቶችን አሳልፋለች። በአስራዎቹ ዕድሜም ውስጥ እያለች ለሁለት ዓመታት ኖራለች።

ነገር ግን እስራኤል በወረራ በያዘቻት ዌስት ባንክ መኖር ለቤተሰቡ ቀላል አልነበረም። በአሜሪካ እና በዌስት ባንክ መኖር ቀላል ባለመሆኑም ጠቅልለው ተመለሱ።

የእስራኤል ወታደራዊ ታንኮች በከተማዋ መገኘት፣ የፍተሻ ኬላዎች በየስፍራዎቹ መበራከት እንዲሁም የእስራኤል የፀጥታ ኃይሎች የፍልስጤማውያንን ተቃውሞ ለመበተን የሚጠቀሙት የአስለቃሽ ጭስ እና የጎማ ጥይት ሰቆቃን መቀበል ለቤተሰቡ ከበደው። እናም ዌስት ባንክን ተሰናብተው ጠቅልለው ወጡ።

“ጠቅልለን መውጣታችንን ሳስበው ምናልባት ያንን ማድረጋችን ሃሞተ ቢስነትን ያሳይ ይሆን? ከቀሩት ፍልስጤማውያን የተሻለ ያደረገኝ ምንድን ነው? ፍልስጤማዊ ስትሆን የጥፋተኝነት ስሜቱ የተለያየ ደረጃ አለው” ትላለች።

አሜሪካ በየዓመቱ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ዶላሮችን ለእስራኤል ወታደራዊ ድጋፍ በሚል ትሰጣለች። ተጨማሪ ድጋፍ መላክ የሚያስችል ረቂቅም በምክር ቤቱ አባላት ተረቋል።

“እኔም እንደ አሜሪካዊነቴ የጥፋተኝነት ስሜት ይሰማኛል። ምክንያቱም የምክፍለው ግብር ይህንን ጦርነት ለመደገፍ እየዋለ በመሆኑ ነው” ትላለች ጂናን።

በተለይም እየተገደሉ ያሉ የፍልስጤማውያን ቁጥር ከማሻቀቡ ጋር ተያይዞ የፍልስጤማዊ አሜሪካውያን ሰቆቃም ጨምሯል። ወደ ሕጻናት የመቃብር ስፍራነት ተቀይራለች በተባለችው ጋዛ ቢያንስ 5600 ሕጻናት መገደላቸውን በሐማስ አስተዳደር ስር ያለው የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታውቋል።

“አቅመ ቢስነት ይሰማኛል። ተስፋ የመቁረጥ እና ምንም ማድረግ እንደማልችል ይሰማኛል” ትላለች ጂናን፤ አክላም “በምንም ነገር ደስታ አይሰማኝም” በማለት እያለፈችበት ያለውን ስሜት ታስረዳለች።

በተለይም በጋዛ ሰርጥ ያለውን የኑሮ ሁኔታ ደግሞ ስትሰማ የበለጠ የጥፋተኝነት ስሜት ይሰማታል።

እስራኤል ጋዛን በሙሉ ከበባ ውስጥ በማስገባት ውሃ፣ መብራት እንዲቋረጥ እንዲሁም ምግብ እና ነዳጅ እንዳይገባ አድርጋለች።

በርካታ ፍልስጤማውያንም ለችግር ተዳርገዋል። ለበሽታዎችም እየተጋለጡ ይገኛሉ። አንዳንድ የጋዛ ነዋሪዎች ለቢቢሲ እንደተናገሩት የባሕር ውሃ ለመጠጣት እየተገደዱ ነው።

“ድንች በብረት ድስት ለመቀቀል ውሃ ከቧንቧ እየቀዳሁ እንባዬ ቀደመኝ” ይላል ማርሴል አፍራም።

“እዚህ በቀላሉ ቧንቧውን ከፈት አድርጌ ድንች መቀቀል እችላለሁ። አሁን ድንች ለማብሰል የምጠቀምበትን ውሃ በጋዛ በሳምንት ውስጥ አንድ ሰው ማግኘት አይችልም” በማለትም ያስረዳል።

በዋሽንግተን ዲሲ ምግብ የሚያቀርብ ንግድ ባለቤት የሆነው ማርሴል እየተሰማው ያለው የጥፋተኝነት ስሜት ሥራዎችን እንዳይቀበል እንዳደረገው ይናገራል።

ጦርነቱ ከተቀሰቀሰ በኋላ የሚቀበለው ሥራ ከፍልስጤም ጉዳዮች ጋር በተገናኘ የገንዘብ ማሳሰቢያ ብቻ ከሆነ ነው።

“ማድረግ የምችለውን ካላደረግኩኝ ከጸጸቱ ጋር መኖር አለብኝ” ብሏል።

ፍልስጤማዊ አሜሪካዊው ማርሴል አፍራም

የፎቶው ባለመብት, Farrah Skeiky

የምስሉ መግለጫ, ፍልስጤማዊ አሜሪካዊው ማርሴል አፍራም

አኔስ ማኅበራዊ ሚዲያውን በብቸኝነት የሚጠቀመው ስለ ጦርነቱ ለመናገር ብቻ ነው።

በቦስተን የሚኖሩ ፍልስጤማውያን የፌስቡክ ገጽን የምትቆጣጠረው ስቴፋኒም ስሜታቸውን ትጋራለች።

ለፍልስጤም ያላትን ድጋፍ በግልጽ በማጋራቷ ማስፈራሪያዎች እንደደረሷት የገለጸችው ስቴፋኒ፣ የአባቷን ስም እንዳይጠቀስ ቢቢሲን ጠይቃለች።

ነፍሰጡር የሆነችው ስቴፋኒ ከእርግዝናዋ ጋር ተያይዞ ከፍተኛ የማቅለሽለሽ እና የድካም ስሜት ለፍልስጤም ከሚደረጉ የአጋርነት ሰልፎች መጀመሪያ ላይ አርቋት ነበር።

በቤት ውስጥም የተቻላትን ለማድረግም ወደ ምትኖርባት ከተማ የምክር ቤት ተወካዮች ጋር ስልክ በመደወልም የተኩስ አቁም ጥሪ እንዲያደርጉም ወትውታለች።

“መጥፎ ስሜት ይሰማኛል። ሰዎች እየሞቱ ባለበት ወቅት አንቺ ታመሽ ቤትሽ ትቀመጫለሽ? እያልኩ ራሴን እጠይቃለሁ” ትላለች።

ይህም ስሜቷ እየጨመረ ሲመጣም ህመሟን እና አለመመቸቷን ዋጥ አድርጋም ለፍልስጤም በሚደረጉ የአጋርነት ሰልፎች መሳተፍ ጀመረች።

በተለይም ጥቅምት መጨረሻ ላይ በነበረው ትልቁ የቦስተን ሰልፍ ላይ መሳተፏ “ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል” ተስፋ በውስጧ አንዲያንሰራራ አድርጎታል።