“አንዳንድ ጊዜ ከካሜራ ጀርባ ቆሜ አለቅሳለሁ” የጋዛው ጋዜጠኛ

የጋዛው ጋዜጠኛ ማህሙድ ባሳም

የፎቶው ባለመብት, Mahmoud Bassam

የምስሉ መግለጫ, የጋዛው ጋዜጠኛ ማህሙድ ባሳም

ጋዛ ትላልቅ ሕንጻዎቿ ወደ ክምር ፍርስራሽነት ተቀይረውባታል።

ተስፋ ያልቆረጡ ቤተሰቦች ከፍርስራሾች ውስጥ ዘመዶቻቸውን ለማውጣት በእጃቸው ይፍጨረጨራሉ።

በአሰቃቂ ሁኔታ የተገደሉ ሕጻናትን የተዝለፈለፈ ሰውነት አቅፈው ሲወጡም መዘገብ የጋዛ ጋዜጠኞች የየቀኑ እውነታ ሆኗል።

እስራኤል በሙሉ ከበባ ስር ባስገባቻት ጋዛ ኤሌክትሪክ እና ውሃ ተቋርጧል። የነዳጅ እና የምግብ አቅርቦት እየተመናመነ ነው።

የጋዛው ጋዜጠኛ ማህሙድ ባሳም ስልኩ እንደ ድሮው አይጠራም።

ስልኩን በየቀኑ ቻርጅ አያደርግም። ቻርጅ ባደረገበት ቀን የስልክ ጥሪዎች ተከታትለው ይመጣሉ።

ምግብ ሲያገኝ ይበላል፤ ካላገኘም ጦሙን ያድራል።

መላዋ ጋዛ በማያባራ የአየር ጥቃት ስትደበደብ ሦስት ሳምንታት አልፏታል።

ማህሙድም ከአየር ጥቃቱ ለማምለጥ ባለቤቱን እና የ11 ወር ጨቅላ ልጁን ይዞ በየቀኑ ደህና ወደ መሰለው ስፍራ ያንቀሳቅሳቸዋል።

ጥዋት ለሥራ ወጥቶ እስኪመለስ ግን እዚያው ስፍራ ላይ እንደሚያገኛቸው እርግጠኛ አይደለም።

ለራሱም መመለሱን አያውቅም።

መንገዱ ካልተዘጋ ወይም የእስራኤል የአየር ጥቃት ከፍቶ ለመጓዝ ከባድ ካልሆነ ነው የሚመለሰው።

ማህሙድ ዕጣ ፈንታውን ለዕድል ትቶታል። በርካቶችም የሚወዷቸውን ሲነጠቁ አይቷል።

ማህሙድ የሕዝቡን የየዕለት ስቃይ ይዘግባል። ባለፉት ሦስት ሳምንታት ወደ ሆስፒታሎች እና የስደተኞች መጠለያ ስፍራዎች መካከል በተደጋጋሚ ተመላልሷል።

ጥቃቶቹ እያደረሱ ያሉትን ውድመትም በየቀኑ ይመዘግባል፣ ለዓለም ያስተላልፋል።

ከቢቢሲው የጋዛ ዘጋቢ ራሽዲ አቡአሎፍ በተጨማሪ እንደ ማህሙድ ያሉ ጋዜጠኞችም ናቸው የጋዛ ሕዝብ በማያቋርጥ የአየር ጥቃት ሰቆቃ ውስጥ ያሉ ሰላማዊ ዜጎችን ስቃይ ለቢቢሲ ታዳሚዎች እያደረሱ ያሉት።

ቢቢሲ ከሰዓታት የስልክ ሙከራ በኋላ ማህሙድን አግኝቶታል።

“የማየውን ነገር ለመመልከት የሚከብደኝን ያህል መልዕክቱንም ለማድረስ ይፈትነኛል። አንዳንድ ጊዜ ከካሜራ ጀርባ ሆኜ ቆሜ አለቅሳለሁ። ማድረግ የምችለው ብቸኛው ነገር ዝምታ ነው” ብሏል ለቢቢሲ።

የጦርነት ቀጠናዎችን የሚዘግቡ የማውቃቸው በርካታ ጋዜጠኞች በሰው ልጆች የማያባራ ሰቆቃ ምክንያት ከፍተኛ የሆነ አቅመ ቢስነት ይሰማቸዋል።

በችግር ላይ ያሉት በርካታ መሆናቸውን ስታዩ እንዴት ታግዛላችሁ? ምግብ ወይም የመጀመሪያ እርዳታ ለመስጠት ከቆምንስ ሥራችንን እንዴት እንሰራለን?

እኛ የእርዳታ ሠራተኞች ወይም የሕክምና ባለሙያዎች ባንሆንም ሰዎች ነን።

ጦርነቱን ለሚዘግቡ የውጭ አገር ጋዜጠኞች ሁኔታው ቀለል ያለ ሊሆን ይችላል። ከፈለጉም በአውሮፕላን ተሳፍረው ወደ ቤታቸው የመሄድም አማራጭ አላቸው። ሕዝቡ እና አገሩ በአየር ጥቃት እየተናጡ ላሉት ማህሙድ ይሄ አማራጭ አይደለም።

ለበርካታ ዓመታት በከበባ ውስጥ ያለችው የጋዛ ሰርጥ የምትሸፍነው አነስተኛ ቦታን ነው።

አጠቃላይ የመሬት ስፋቷም 366 ካሬ ኪሎ ሜትር ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ማህሙድም የሚያውቃቸውን ተጎጂ የጋዛ ነዋሪዎች የማግኘት ዕድሉ ሰፊ ነው።

የጋዛ ጥቃት

የፎቶው ባለመብት, EPA

“እኔ ጋዜጠኛ ነኝ። ተልዕኮዬም ያየሁትን ነገር መዘገብ ነው። ነገር ግን አንዳንድ ጊዜን ሥራዬን አቁሜ ከልጆች ጋር ቁጭ እላለሁ። ውሃ እሰጣቸዋለሁ። የሚያስፈልጋቸውን ነገር አይቼ ላቀርብላቸው እሞክራለሁ” ሲል ያስረዳል።

ማህሙድ በዚህ ሁሉ መከራ ውስጥ እያለፈም ሥራውን የሚያከናውነው በእርጋታ ነው።

የሚቀርጻቸው እና ቃለ መጠይቅ የሚያደርግላቸው ፍልስጤማውያን ምናልባትም ይህ የመጀጨረሻ ቀረጻቸው ሊሆን እንደሚችል በጭራሽ አይዘነጋም።

በአስከፊ እና ሊታሰብ በማይችል ህመም እና ሰቆቃ ውስጥ ሆነው ታሪካቸውን እየተናገሩ መሆኑንም ልብ ባለ መልኩ ነው ዘገባውን የሚያቀርበው።

በጦርነቱ ሰላማዊ ሰዎች ብቻ ሳይሆን በርካታ ጋዜጠኞችም ተቀጥፈዋል። በባለፉት ሦስት ሳምንታት 33 ጋዜጠኞች የተገደሉ ሲሆን፣ ከእነዚህም ውስጥ 28ቱ ፍልስጤማውያን መሆናቸውን የጋዜጠኞች መብት ተቆርቋሪው ሲፒጄ አስታውቋል። በተለይም የጋዛ ጋዜጠኞች ከዚህ በፊት ታይቶ የማያውቅ ዋጋ እየከፈሉ ነው ብሏል።

“ለጋዛ ጋዜጠኞች ገዳይ ወቅት ነው” ሲሉም የመካከለኛ ምሥራቅ የሲፒጄ ባለሙያ ሸሪፍ ማንሱር ተናግረዋል።

“በባለፉት 21 ዓመታት ጦርነቶች ሲዘግቡ ከተገደሉት በላይ ባለፉት ሦስት ሳምንታት በርካታ ጋዜጠኞች ተገድለዋል። በርካታ ጋዜጠኞች ቤተሰቦቻቸውን፣ የሥራ ባልደረቦቻቸውን አጥተዋል። ቤቶቻቸው ወድሟል እናም ደኅንነቱ የተጠበቀ መሸሸጊያ በሌለበት ሁኔታ ለመሸሽ ተገደዋል” ሲሉም አስረድተዋል።

የአልጀዚራ የአረብኛ ቢሮ ኃላፊ የሆነው ዋኤል አል ዳህዱ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የጋዜጠኞች ትስስር ጥብቅ በሆነባት ጋዛ የሥራ ባልደረቦች መገደል ከፍተኛ ሕመምን መፍጠሩ የማይቀር ነው።

በአሁኑ ወቅት ኑሯዋን በብሪታንያ ያደረገችው ፍልስጤማዊዋ ጋዜጠኛ ያራ ኢድ ትውልዷ እና እድገቷ በጋዛ ነው። በጦርነቱ ጅማሬ ላይ የተገደለው ጓደኛዋን የኢብራሂም ላፊ ሐዘን ልቧ ተሰብሯል።

“የልብ ወዳጄን ኢብራሂምን አጣሁት። ፍልስጤማዊ ጋዜጠኛ ነበር፣ ነገር ግን ጋዜጠኛ ብቻ አልነበረም። 21 ዓመቱ ነበር። ወንድም፣ የቅርብ ጓደኛ፣ ህልመኛ ነበር” ትላለች።

“የፎቶ ባለሙያ ነበር። ሕይወትን በጣም ያፈቅር ነበር። ከሁሉም በላይ ፈገግታ ከፊቱ አይታጣም። በሕይወት ዘመኔ ኢብራሂምን ፈገግ ሳይል አይቼው አላውቅም። ፊቱ በፈገግታ የበራ ነበር” በማለት ታስታውሳለች።

“በሕይወቴ ከገጠሙኝ ደጋፊ ጓደኞች አንዱ ነበር። ትልልቅ ህልሞች ነበሩት። ለዓለም ሁሉ የጋዛን ድንቅ ውበት በፎቶው ለማሳየትም ያልም ነበር” በማለት በሐዘን በተሰበረ ሁኔታ ትናገራለች።

የጋዛ ጋዜጠኞች ራሳቸው ብቻ ሳይሆን ቤተሰቦቻቸውም የከፋ ስጋት ላይ ናቸው።

ለምሳሌ የአልጀዚራ የአረብኛ ቢሮ ኃላፊ የሆነው ዋኤል አል ዳህዱ በእስራኤል የአየር ጥቃት ባለቤቱ፣ ሁለት ልጆቹ እና ጨቅላው የልጅ ልጁ ተገድለውበታል።

የእስራኤልን የአየር ጥቃት በከፍተኛ ሁኔታ ያወገዘው ዋኤል፣ የዘገባ ሥራውን እንደማያቆም ተናግሮም ከአንድ ቀን በኋላ ወደ ሥራ ተመልሷል። እነዚህ የጋዛ ጋዜጠኞች በዓለም ላይ ላሉ ታዳሚዎችም በጋዛ ውስጥ ምን እየተከናወነ እንደሆነ ሕይወታቸውንም ጭምር በመክፈል እየዘገቡ ይገኛሉ።