በጋዛ የካቶሊክ መነኮሳት፡ “ሕዝባችንን ጥለን ወደ የትም አንሄድም”

ማሪያ ዴል ፒላሰር እና ማሪያ ዴል ፔርፔቶ ሶኮሮ ቫርጋስ

የፎቶው ባለመብት, AP

የምስሉ መግለጫ, ማሪያ ዴል ፒላሰር እና ማሪያ ዴል ፔርፔቶ ሶኮሮ ቫርጋስ

ማሪያ ዴል ፒላሰር እና ማሪያ ዴል ፔርፔቶ ሶኮሮ ቫርጋስ ይባላሉ። መንታ መነኮሳት ናቸው። አሁን በጋዛ ነው የሚገኙት። የፔሩ ዜግነት አላቸው። የሆሊ ፋሚሊ ቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች ናቸው።

መንትዮቹ ሲስተሮች የሚገኙበት ሆሊ ፋሚሊ ቤተ ክርስቲያን በፍልስጥኤም ግዛት ብቸኛው የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ነው።

በጋዛ በችግር ላይ ያሉ ከ600 በላይ ክርስቲያን ምዕመናን እየተንከባከቡ ነው።

1 ሺህ 400 ሰዎች የተገደሉበትን የሐማስ ጥቃት ተከትሎ እስራኤል በጋዛ ላይ መጠነ ሰፊ የአየር ጥቃት እየፈጸመች ነው።

ከ5 ሺህ በላይ ንጹሐን ሲገደሉ ከእነዚህ መካከል 2 ሺህ የሚሆኑት ሕጻናት ናቸው። ይህ አሐዝ ግን በሐማስ የሚመራው የጋዛ ጤና ሚኒስትር ያቀረበው ነው።

የፔሩ ኤምባሲ መነኮሳቱን ወደ ግብፅ እንዲወጡ ሁኔታዎችን አመቻችቶ የነበረ ቢሆንም፣ መንትዮቹ መነኮሳት ለጊዜው ፍቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል።

ሲስተር ማሪያ ዴል ፒላር ከቢቢሲ ጋር ቆይታ አድርገው ነበር።

ቢቢሲ፦ ቤተ ክርስቲያናችሁ መብራትም ውሃም ተቋርጦበታል። አሁን ያላችሁበት ሁኔታ ምን ይመስላል?

ሲስተር ማሪያ፦ 600 ሰዎች እኛ ዘንድ ተጠልለዋል። ልክ እንደ ሌላው የጋዛ ክፍል እኛም ውሃ የለንም። ነገር ግን የጉድጓድ ውሃ አለን። ለእጥበት እና ለመጸዳጃ ቤት እንጠቀምበታለን። ይህ ነገር ምን ያህል ሊያዘልቅ እንደሚችል አናውቅም። የታሸገ ውሃ ከሌላው ጊዜ ሦስት እጥፍ ገዝተን የተጠሙ እንዲጠጡ እያደረግን ነው።

ቢቢሲ፦ የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን በሚሳኤል መመታቱን ተከትሎ 18 ክርስቲያኖች ቀብር ላይ ተገኝተዋል። እስራኤል ጥቃቱን አስተባብላለች። በዚያ ዕለት ምን እንደተከሰተ ሊያብራሩልን ይችላሉ?

ሲስተር ማሪያ፦ ምዕመናኑ የሞቱት በእስራኤል ቦምብ ነው። ተኝተውበት የነበረው አንዱ ክፍል ተደረመሰ። በዚህ የተነሳ በርካታ ክርስቲያን ወንድም እና እህቶቻችን ሞቱ። እነሱን ለማጽናናትና ቀብር ለመታደም ለመጀመሪያ ጊዜ ወጥቻለሁ።

ቤተክርስቲያን

የፎቶው ባለመብት, Familia Religiosa IVE

ቢቢሲ፦ የት ነው ምዕመናኑ የተቀበሩት?

ሲስተር ማሪያ፦ እዚህ ሁሉም ቤተ ክርስቲያን የራሱ የመቃብር ሥፍራ አለው።

ቢቢሲ፦ በቀብር ሥነ ሥርዓቱ ላይ ከአእምሮዎ መቼም የማይጠፋ ምስል ማየትዎን ተናግረዋል። ምንድነው?

ሲስተር ማሪያ፦ እውነት ነው። በቀብር ሥነ ሥርዓቱ ልጅ አባቱን ሲሰናበት ማየት ያማል። ወላጆች ደግሞ ልጆቻቸውን ሲሰናበቱ የበለጠ ያማል። አንዳንድ ቤተሰቦች ግን ነበሩ፤ ሁሉንም ልጆቻቸውን ያጡ። በቃ ሁሉንም ልጆቻቸውን በሞት ያጡ። ልጆቹን አውቃቸዋለሁ። ሁሉም ተገደሉ። ይህ በጣም ያማል።

ቢቢሲ፦ ለመሆኑ ምግብ ታገኛላችሁ? ምክንያቱም ጥቂት የሰብአዊ ረድኤት ተሽከርካሪ ነው ወደ ጋዛ እንዲገባ የተደረገው።

ሲስተር ማሪያ፦ ክብሩ ይስፋ! ሕዝቡ እየረዳን ነው። በተለይ የላቲን እና የኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት እየተጋገዙ ነው። ይህ የፈጣሪ ጸጋ ነው። ምግብ እየገዛን ነው። በእርግጥ በጣም ውድ ነው። ቢሆንም የሚላስ የሚቀመስ አላጣንም።

መንታዎቹ መነኮሳት

የፎቶው ባለመብት, Familia Religiosa IVE

ቢቢሲ፦ ከኦርቶዶክስ ቤተክስርቲያን ጥቃት የተረፉትም እናንተ ዘንድ ነው የተጠለሉት?

ሲስተር ማሪያ፦ አዎ፣ እኛ ዘንድ አሉ። ምክንያቱም ቤተ ክርስቲያናቸው ግማሹ ፈርሷል። የተወሰኑት እዚህ ናቸው።

ቢቢሲ፦ በግብፅ የሚገኘው የፔሩ ቆንስላ ዜጎች ወደ ግብፅ እንዲሄዱ ሁኔታዎችን እያመቻቸ ነው። ከጋዛ ለመውጣት ፍቃደኛ ናችሁ?

ሲስተር ማሪያ፦ በፍጹም። ከእስራኤል የፔሩ ኤምባሲ ደውለውልን ነበር። ከግብፅም እንደዚያው። መሄድ ከፈለግን ሁሉም ነገር እንደተመቻቸልን ነግረውናል።

እኛ ሕዝባችንን ጥለን የትም አንሄድም። ላለፉት አራት ዓመታት እዚህ ነው የኖርኩት። ሕይወቴ እዚህ ነው ያለው። ይህ ቤታችን ነው። እነዚህ የእኛ ናቸው። የእኛን እርዳታ ይፈልጋሉ። የትም ጥለናቸው አንሄድም።

መንታዎቹ መነኮሳት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ቢቢሲ፦ ግን እኮ በየቀኑ በሚጣለው ቦምብ የመሞት ዕድላችሁ እየሰፋ ነው።

ሲስተር ማሪያ፦ እውነት ነው። ያን እንረዳለን። ምክንያቱም ቦምብ ሲወድቅ እንሰማለን። እዚህ የተጠለለው ምዕመን በሙሉ ይህን ይረዳል።

ሁሉም ክርስቲያን ሕዝብ ሕይወቱን ለማዳን ወደ ደቡብ ጋዛ መሄድ ይችላል። ማንም ግን መሄድ አልፈለገም። እዚሁ በቤተክርስቲያኒቱ መጠለል ነው የሚሻው። በሌላ ቋንቋ ሁሉም ከፈጣሪ ቤት መሆንን ነው የሚሻው።

ቢቢሲ፦ እስራኤል በራሪ ወረቀቶችን በትናለች። ወደ ደቡብ ጋዛ የማይሄዱ የአሸባሪ ደጋፊዎች ናቸው ብለዋል።

ሲስተር ማሪያ፦ በዚህ ቤተ ክርስቲያን አቅመ ደካሞች፣ አካል ጉዳተኞች አሉ። በዊልቼር የሚንቀሳቀሱ አሉ። ብዙ መራመድ የማይችሉ አዛውንት አሉ። የጭንቅላት ቀዶ ጥገና ያደረገ ሰው አለ ከመሀላችን። የቆሰሉ አሉ።

በዚች ቤተ ክርስቲያን መጠለልን የሚሹ ናቸው። ከመሀላችን ሐኪሞችም አሉ። እንዴት ነው 600 አቅመ ደካሞችን ይዘን የምንሄደው? ይህን ልናደርገው አንችልም። እነሱም [እስራኤሎች] ይህን ይረዳሉ ብዬ አስባለሁ።

ሰላም እንሻለን። ለዚያ ተግተን መጸለይ ይኖርብናል። ሁላችንም በአንድ ሆነን ለሰላም መጸለይ ነው የሚኖርብን።

መንታዎቹ መነኮሳት

የፎቶው ባለመብት, Familia Religiosa IVE