በጋዛ ከተኩስ አቁም ፋታው በኋላ 200 ፍልስጤማውያን በእስራኤል ጥቃት ተገደሉ

ለሰባት ቀናት የቆየውን የጋዛ የተኩስ አቁም ፋታ ተከትሎ 200 ፍልስጤማውያን በእስራኤል ጥቃት መገደላቸውን በሐማስ አስተዳደር ስር ያለው የጋዛ የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል። እስራኤል እየፈጸመችው ባለው ጥቃት ከ15 ሺህ በላይ ፍልስጤማውያን ሲገደሉ 6 ሺህ ህጻናት መሆናቸውን ሚኒስቴሩ ገልጿል።

የቀጥታ ሽፋን

  1. እስራኤል የገደለችው የሐማስ መሪ ያህያ ሲንዋር ማን ነበር?

  2. የተኩስ አቁም ፋታው ካበቃ በኋላ ስለእስራኤል እና ሐማስ ጦርነት የምናውቀው ምንድን ነው?

    በጥቃቱ ከፈራረሱት ሕንጻዎች በቅርብ ርቀት ላይ ተቀምጠው ከቤታቸው የተረፈውን የሚያዩ ነዋሪዎች

    የፎቶው ባለመብት, AFP

    የምስሉ መግለጫ, በጥቃቱ ከፈራረሱት ሕንጻዎች በቅርብ ርቀት ላይ ተቀምጠው ከቤታቸው የተረፈውን የሚያዩ ነዋሪዎች
    • ለአንድ ሳምንት የዘለቀው የተኩስ አቁም ፋታ ስምምነት ዐርብ ዕለት ከተጠናቀቀ በኋላ እስራኤልበጋዛ ላይ የማያባራ የአየር ጥቃት እየፈጸመች ትገኛለች።
    • እስራኤል ጦርነቱ ከጀመረ አንስቶ የከፋ የአየር ጥቃት በደቡባዊ ጋዛ ከተማ ኻን ዩኒስ ላይ መፈፀሟን ነዋሪዎች ተናግረዋል።
    • ከኻን ዩኒስ ከተማ ምሥራቃዊ አካባቢ የሚኖሩ ነዋሪዎችም ወደ ደቡብ እንዲሄዱ ቀደም ብሎ በእስራኤል ጦር ተነግሯቸዋል።
    • የተኩስ አቁም ፋታው ዐርብ እለት ካበቃ በኋላ የእስራኤል ጦር ከ400 በላይ የሐማስ ኢላማዎችን መትቻለሁ ብሏል።
    • በጋዛ በሐማስ የሚተዳደረው ጤና ሚኒስቴር እስራኤል አዲስ እየፈፀመች ባለችው ጥቃት ወደ 200 የሚጠጉ ሰዎች መገደላቸውን ገልጿል።
    • ሚኒስቴሩ ጦርነቱ ከጀመረ አንስቶ በጋዛ የተገደሉ ሰዎች ቁጥር ከ15 ሺህ 200 በላይ መድረሱን አስታውቆ፣ከእነዚህም ውስጥ 6 ሺህ ያህሉ ሕጻናት ናቸው ብሏል።
    • የተኩስ አቁም ፋታውን ለማስቀጠል በኳታር ሲካሄድ የነበረው ድርድር አልተሳካም።እስራኤልም ተደራዳሪዎቿ ዶሃን ለቀው እንዲወጡ ትዕዛዝ ሰጥታለች።
    • እንደ ፍልስጤም ቀይ ጨረቃ ከሆነ ወደ 100 የሚደርሱ ሰብዓዊ እርዳታ የጫኑ ተሽከርካሪዎች በግብፅ በኩል ወደ ጋዛ ገብተዋል።
    • ሆኖም የእርዳታ ድርጅቶች የገባው እርዳታ በቂ አለመሆኑን ገልጸው፣እስራኤል በሙሉ ከበባ ውስጥ ባስገባቻት ጋዛ ያለው የሰብዓዊ ሁኔታ አሳሳቢ እንደሆነ አስጠንቅቀዋል።
  3. ካማላ ሐሪስ እስራኤል ዓለም አቀፍ እና ሰብዓዊ ሕጎችን ማክበር አለባት አሉ

    የአሜሪካ ምክትል ፕሬዚደንት ካማላ ሐሪስ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የአሜሪካ ምክትል ፕሬዚደንት ካማላ ሐሪስ እስራኤል ዓለም አቀፍ እና የሰብዓዊ መብት ሕጎችን ልታከብር ይገባል አሉ።

    ምክትል ፕሬዚደንቷ አገራቸው ፍልስጤማውያን በአስገዳጅ መፈናቀላቸውን እንደማትፈቅድም ተናግረዋል።

    ካማላ ሐሪስ ይህን ያሉት በኮፕ28 የአየር ንብረት ጉባኤ ወቅት ከግብጹ ፕሬዚደንት አብደል ፈታህ አል ሲሲ ጋር ባደረጉት ውይይት ወቅት ነው።

    ምክትል ፕሬዚደንቷ ይህን ከተናገሩ ከሰዓታት በኋላም እስራኤል ከሐማስ እራሷን የመከላከል መብት አላት፤ ነገርግን ዓለም አቀፍ እና ሰብዓዊ ሕጎችን ማክበር አለባት ሲሉ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

    ሐሪስ በርካታ ፍልስጤማውያን ተገድለዋል ሲሉም እስራኤል ሰላማዊ ሰዎችን ለመጠበቅ ብዙ ማድረግ አለባት ብለዋል።

    “ሁላችንም ይህ ጦርነት በተቻለ ፍጥነት እንዲቆምና የእስራኤል እና የፍልስጤማውያን ደኅንነት መጠበቁን ማረጋገጥ እንፈልጋለን፤ በመሆኑም ዘላቂ ሰላምን ለመፍጠር ጥረቶቻችንን ማፍጠን አለብን” ብለዋል።

  4. ተኩስ አቁሙ ካበቃበት ከአርብ ጀምሮ በጋዛ 193 ሰዎች ተገድለዋል፡ የጤና ሚኒስቴር

    ሐዘንተኞች በጋዛ ናስር ሆስፒታል

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, ሐዘንተኞች በጋዛ ናስር ሆስፒታል

    ለአንድ ሳምንት ያህል የቆየው የእስራኤል እና የሐማስ ጊዜያዊ ተኩስ አቁም አብቅቶ እስራኤል በጋዛ ላይ ጥቃት ከጀመረችበት ከትናንት አርብ አንስቶ ወደ 200 የሚጠጉ ሰዎች መገደላቸው ተነገረ።

    በሐማስ የሚመራው የጋዛ ሰርጥ ጤና ሚስኒቴር ዛሬ ቅዳሜ ከሰዓት በኋላ እንዳስታወቀው፣ ከአርብ ጀምሮ እስራኤል እያካሄደችው ባለው ጥቃት 193 ሰዎች ተገድለዋል።

    ለሰባት ቀናት የዘለቀው ጊዜያዊ ተኩስ አቁም ካበቃ በኋላ እስራኤል በጀመረችው ጥቃት ከተገደሉት ፍልስጤማውያን በተጨማሪም 652 ሰዎች የመቁሰል ጉዳት እንደደረሰባቸው ሚኒስቴሩ አሳውቋል።

    ከመስከረም 26ቱ የሐማስ ጥቃት በኋላ እስራኤል በጋዛ ሰርጥ በከፈተችው ጥቃት የተገደሉ ሰዎች አጠቃላይ ቁጥር ደግሞ ከ15,000 ማለፉን እንዲሁም ከ40,000 በላይ ሰዎች እንደቆሰሉ ሚኒስቴሩ አመልክቷል።

    አክሎም በጥቃቱ ሰለባ ከሆኑት መካከል 70 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች እና ሕጻናት መሆናቸውም ተገልጿል።

  5. ከሁለት ወር ባነሰ ጊዜ 100 ሺህ ሕንፃዎች የወደሙባት የፍርስራሽ ክምሯ ጋዛ በሳተላይት ዕይታ

  6. ተመድ በሐማስ ተፈጽመዋል የተባሉ ፆታዊ ጥቃቶች አሳሳቢ ናቸው አለ

    UN Women

    የፎቶው ባለመብት, UN Women

    የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሴቶች ጉዳይ ተቋም መስከረም 26/2016 ዓ.ም. በሐማስ ጥቃት ወቅት ተፈጽመዋል የተባሉ ፆታን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች አሳሳቢ ናቸው አለ።

    ሐማስ ጥቃቱን ሲያደርስ በእስራኤል ማኅብረሰብ አባላት ላይ ተፈጽመዋል የተባሉ ፆታን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች ምርመራ እንዲደረግባቸው እና ጥፋተኞች በሕግ እንዲጠየቁ ተቋሙ ጠይቋል።

    ሐማስ ተዋጊዎቹ ጾታን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶችን አልፈጸሙም በማለት ሲያስተባብል ቆይቷል።

  7. በምሥል፡ ከተኩስ አቁም ፋታ በኋላ በቀጠለው ጦርነት በጋዛ የደረሰ ውድመት

    በጋዛ የደረሰ ውድመት

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የተኩስ አቁም ፋታ ካበቃ በኋላ እስራኤል ድብደባዋን ቀጥላበታለች።

    የአገሪቱ ጦር እስካሁን ከ400 ያላሱ የሐማስ መገኛዎችን መትቻለሁ ብሏል።

    በጥቃቱ ቤተሰቦቻቸውን እና ንብረታቸውን ያጡ ፍልስጤማውያን ሲያነቡ ተይተዋል።

    በሁለተኛው ዙር ጥቃት በእስራኤል ዒላማ ውስጥ የገባው እና ከባድ ጉዳት የደረሰበት በደቡብ ጋዛ የሚገኘው ኻን ዩኒስ ነው።

    ከፍርስራሽ ስር የሟቾች አስክሬንን ለማውጣት የሚጣጣሩ ፍልስጤማውያን

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, ከፍርስራሽ ስር የሟቾችን አስክሬን ለማውጣት የሚጣጣሩ ፍልስጤማውያን
    በደቡባዊ ጋዛ በአየር ጥቃት የተገደሉ ሰዎች አስክሬን ሲወጣ የቤተሰብ አባላት ሲያለቅሱ ታይተዋል።

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, በደቡባዊ ጋዛ በአየር ጥቃት የተገደሉ ሰዎች አስክሬን ሲወጣ የቤተሰብ አባላት ሲያለቅሱ
  8. የእስራኤል ጦር ጋዛ ውስጥ ከ400 በላይ ዒላማዎችን መምታቱን ገለጸ

    በእስራኤል ጥቃት የፈረሰ ሕንጻ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    ለቀናት የቆየው ጊዜያዊ የተኩስ አቁም ትናንት አርብ አብቅቶ እስራኤል ማለዳ በጋዛ ላይ ጥቃቷን መልሳ ከጀመረች በኋላ እስከ ዛሬ ቅዳሜ ጠዋት ድረስ ከ400 በላይ ዒላማዎችን ማጥቃቷን ጦር ሠራዊቷ አስታወቀ።

    የእስራኤል መከላከያ ኃይል (አይዲኤፍ) እንዳለው የአገሪቱ የአየር፣ የባሕር እና የምድር ኃይል ደቡባዊ የጋዛ ሰርጥን ጨምሮ መላዋን ጋዛን ዒላማ ያደረጉ ጥቃቶችን መፈጸማቸውን አመልክቷል።

    ጨምሮም “ተዋጊ ጄቶች በኻን ዩኒስ አካባቢ ባሉ ከ50 በሚልቁ ዒላማዎች ላይ መጠነ ሰፊ ጥቃት ፈጽመዋል” ብሏል።

    ጦር ኃይሉ የፍልስጤማ እስላማዊ ጂሃድ የተባለው ቡድን እንደ ማዘዣ ማዕከል ይጠቀምበታል ያለውን በሰሜናዊ ጋዛ የሚገኝ አንድ መስጂድን በአየር ጥቃት መምታቱን ገልጿል። ቢቢሲ ይህንን የእስራኤል ሠራዊት ክስ ከገለልተኛ ወገን ማረጋገጥ አልቻለም።

    እስራኤል የሰሜናዊ ጋዛ ነዋሪዎች አካባቢያቸውን ለቀው ወደ ደቡብ እንዲሄዱ ካዘዘች በኋላ፣ በመቶ ሺዎቸ የሚቆጠሩ የጋዛ ነዋሪዎች በደቡባዊ የሰረጡ ክፍል ውስጥ በምትገኘው የኻን ዩኒስ ከተማ በአብዛኛው በጊዜያዊ የድንኳን መጠለያ ውስጥ ይገኛሉ።

  9. አንድ ግለሰብ አሜሪካ ውስጥ በሚገኝ የእስራኤል ቆንስላ በር ላይ እራሱን በእሳት አቃጠለ

  10. ኳታር ለግጭቱ ዳግም ፋታ ለመስጠጥ ንግግር እየተካሄደ ነው አለች

    ለ7 ቀናት ጋብ ብሎ የነበረው ግጭት ዳግም ተጀምሯል።

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የምስሉ መግለጫ, ለ7 ቀናት ጋብ ብሎ የነበረው ግጭት ዳግም ተጀምሯል።

    የኳታር መንግሥት እስራኤል እና ሐማስ ዳግም ለጦርነቱ ፋታ ለመስጠት ድርድር እያደረጉ እንደሆነ ገለጸ።

    የኳታር መንግሥት ሁለቱን ኃይሎች አደራድሮ ባለፉት 7 ቀናት ጦርነቱ ጋብ ብሎ የእስረኞች እና የታጋቾች ልውውጥ ከመደረጉ በተጨማሪ ሰብዓዊ እርዳታ ጋዛ ሲደርስ ነበር።

    ይሁን እንጂ ሐማስ እና እስራኤል የደረሱት ስምምነት በማብቃቱ ከዛሬ ማለዳ ጀምሮ ሁለቱ ኃይሎች ዳግም ወደ ጦርነት ተመልሰዋል።

    የኳታር የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እስራኤል ዳግም በጋዛ ሰርጥ ወታደራዊ ዘመቻ መጀመሯ አሳዛኝ ነው ብሏል።

    ይሁን እንጂ የኳታር መንግሥት ከሌሎች አጋሮች ጋር በመሆን “ለሰብዓዊነት ሲባል ግጭት እንዲቆም ስምምነት እንዲደረስ” ጥረት ማድረጉን እንደሚቀጥል አስታውቋል።

  11. የተመድ ዋና ፀሐፊ ግጭት መጀመሩ “እጅግ አሳዛኝ ነው” አሉ

    አንቶኒዮ ገተሬዝ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, አንቶኒዮ ገተሬዝ

    የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በጋዛ ግጭት መጀመሩ “በጣም አሳዛኝ ነው” አሉ።

    ዋና ፀሐፊው በማኅበራዊ ገጻቸው በኩል ባሰፈሩት መልዕክtእ ባለፉት ቀናት ተግባራዊ ተደርጎ የነበረው ስምምነትን ማስቀጠል ይቻላል የሚል ተስፋ እነeዳላቸው ገልጸዋል።

    ባለፉት ሰባት ቀናት እስራኤል እና ሐማስ ለጦርነቱ ፋታ ለመስጠት ተስማምተው ታጋቾች እና እስረኞችን ሲለዋወጡ ቆይተዋል።

    ከመስከረም 26ቱ ድንገተኛ ጥቃት በኋላ በጋዛ ሰርጥ 6ሺህ ሕጻናትን ጨምሮ 14ሺህ 800 ሰዎች መገደላቸውን በሐማስ የሚተዳደረው ጤና ሚንስቴር አስታውቋል።

    በእስራኤል ደግሞ ከ1200 የማያንሱ ሰዎች ተገድለዋል።

  12. በምስል፡ ሮኬቶች እና የአየር ጥቃቶች

    ከሰባት ቀናት የጦርነት ፋታ በኋላ የእስራኤል እና ሐማስ ውጊያ ተጀምሯል።

    ከዛሬ አርብ ንጋት ጀምሮ ሮኬቶች ከጋዛ እና ወደ ጋዛ ሲወነጨፉ ታይተዋል።

    የእስራኤል ጦር “ዘመቻ ጀምሬያለሁ” ያለ ሲሆን በጋዛ ሰርጥ የአየር ድብደባዎችን እያደረገ ይገኛል።

    በጋዛ ሰማይ ላይ ትልቅ ጭስ ታይቷል

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የምስሉ መግለጫ, ዛሬ ረፋድ በጋዛ ሰማይ ላይ ትልቅ ጭስ ታይቷል
    በደቡባዊ ጋዛ የወደመ መኖሪያ ቤት

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የምስሉ መግለጫ, በደቡባዊ ጋዛ የወደመ መኖሪያ ቤት
    ጦርነት ዳግም መቀስቀሱን ተከትሎ ፍልስጤማውያን መኖሪያቸውን ጥለው ለመሸሽ ተገደዋል

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የምስሉ መግለጫ, ጦርነት ዳግም መቀስቀሱን ተከትሎ ፍልስጤማውያን መኖሪያቸውን ጥለው ለመሸሽ ተገደዋል
    ሮኬቶች ከጋዛ ሰርጥ ወደ እስራኤል ሲወነጨፉ ታይተዋል

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የምስሉ መግለጫ, ሮኬቶች ከጋዛ ሰርጥ ወደ እስራኤል ሲወነጨፉ ታይተዋል
  13. እስራኤል በ3 ሰዓታት ውስጥ በፈጸመቻቸው የአየር ጥቃት 32 ፍልስጤማውያን መገደላቸው ተገለጸ

    የጋዛ ጥቃት

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    እስራኤል የተኩስ አቁም ፋታው ማብቃቱን ተከትሎ ባሉ ሶስት ሰዓታት በፈጸመቻቸው የአየር ጥቃቶች 32 ፍልስጤማውያን መገደላቸውን የጋዛ የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።

    በሐማስ አስተዳደር ስር የሚገኘው የጤና ሚኒስቴር እስራኤል በበርካታ የጋዛ ስፍራዎች የአየር ጥቃት እየፈጸመች ነው ብሏል።

    ለሰባት ቀናት የዘለቀውን የተኩስ አቁም ፋታ ተከትሎ የተከተለው ጥቃትም አስደንጋጭ ነው ተብሏል።

    የተባበሩት መንግሥታት የህጻናት መርጃ ድርጅት፣ ዩኒሴፍ ለቢቢሲ እንደተናገረው በደቡባዊ ጋዛ ያለው ሁኔታ "አስፈሪ ነው" ብለዋል።

    "ያለው ሁኔታ ለነዋሪዎች አሰቃቂ ነው። በፊታቸው ላይም ፍርሃት ይነበባል" ሲሉ የዩኒሴፍ ባልደረባ ጄምስ ኤልደር ለቢቢሲ ተናግረዋል።

    በአሁኑ ወቀድት በደቡባዊ ጋዛ በሚገኝ ሆስፒታል ውስጥ እንደሚገኙ የተናገሩት ጄምስ ከተቋሙ በ50-100 ሜትር ርቀትም ላይ የአየር ጥቃት ተፈጽሟል ብለዋል።

    የተኩስ አቁም ፋታው ማብቃቱንም "ሁሉም ሰው የሚፈራው ቅዠት" ደርሷል ሲሉ ገልጸው ሰብዓዊ ቀውሱም ለበርካቶች ሞት እንደሚሆንም አስጠንቅቀዋል።

  14. ሐማስ እና እስራኤል የተኩስ አቁም ፋታ ስምምነቱን በመጣስ እየተወነጃጀሉ ነው

    የጋዛ ጥቃት

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    ሐማስ እና እስራኤል ለሰባት ቀናት የቆየው የተኩስ አቁም ፋታ ስምምነትን በመጣስ እየተወነጃጀሉ ነው።

    ሐማስ የስምምነቱ አካል የሆነው በሰሜናዊ ጋዛ ሰርጥ ነዳጅ እንዲገባ መፈቀድ ቢኖርበትም እስራኤል በመከልከሏ ስምምነቱን ጥሳለች እንዳለ ለድርድሩ ቅርብ የሆኑ ምንጭ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

    እስራኤል በበኩሏ ሐማስ ተጨማሪ ታጋቾችን ለመልቀቅ ፈቃደኛ ባለመሆኑ ስምምነቱ ተጥሷል ብላለች።

    ለድርድሩ ቅርብ የሆኑት እኚሁ ምንጭ በበኩላቸው ሐማስ በጋዛ የተወሰዱ ወንዶች ታጋቾችን፤ ሴቶችን እና ህጻናቶችን በለቀቀው መልኩ ለመልቀቅ ፈቃደኛ አይደለም ብለዋል።

    የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በበኩላቸው በስምምነቱ መሰረት ሐማስ ሁሉንም ሴቶች ታጋቾች እንዳልለቀቀ እና በእስራኤልም ላይ ሮኬት አስወንጭፏል ብለዋል።

    " እስራኤል ታጋቾችን ለማስለቀቅ፣ ሐማስን ለማጥፋት እና ጋዛ በእስራኤል ነዋሪዎች ላይ ስጋት እንዳትፈጥር የጀመረችውንም ወታደራዊ ዘመቻ ከግብ ለማድረስ ትቀጥላለች" ብለዋል።

  15. እስራኤል በራፋህ በፈጸመችው የአየር ጥቃት ስድስት ፍልስጤማውያን ተገደሉ

    ለሰባት ቀናት የዘለቀው የተኩስ አቁም ፋታ ማብቃቱን ያወጀው የእስራኤል ጦር በደቡባዊ ጋዛ ራፋህ ከተማ በፈጸመው የአየር ጥቃት ስድስት ፍልስጤማውያን ተገደሉ።

    ጥቃቱ ዛሬ ማለዳ መፈጸሙንም በሐማስ አስተዳደር ስር የሚገኘው የጤና ሚኒስቴር ቃለ አቀባይ ለአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ተናግረዋል።

    የተኩስ አቁም ፋታው ዛሬ ማለዳ ያቆመ ሲሆን እስራኤልም ሐማስ ሮኬት አስወንጭፏል በማለት ስምምነቱን ጥሷል ስትል ከሳለች።

    ከዚህ በተጨማሪም እስራኤል በሰሜን ጋዛ በፈጸመችው የአየር ጥቃት ሁለት ልጆች መገደላቸውን ኤኤፍፒ በአል አህሊ ሆስፒታል የህክምና ባለሙያ የሆኑትን ዶክተር ፋዴል ናይምን ዋቢ አድርጎ ዘግቧል።

    በርካታ የጋዛ ሰርጥ አካባቢዎችም በእስራኤል የአየር ጥቃት እንደተፈጸመባቸው የጋዛ የሃገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።

    በኳታር አሸማጋይነት የተደረሰውን የተኩስ አቁም ፋታ ተከትሎ ሐማስ 110 ታጋቾችን ሲለቅ እስራኤል ደግሞ 240 ህጻናት እና ሴቶች ፍልስጤማውያን እስረኞችን ፈታለች።

    ጦርነቱ ዳግም መጀመር በከበባ ውስጥ ባለች የጋዛ ሰርጥ የከፋ ስብዓዊ ቀውስ ያስከትላልም ተብሏል።

  16. የጋዛ የተኩስ አቁም ፋታ ማብቃቱን እና ጦርነት መቀጠሉን እስራኤል አስታወቀች

    የእስራኤል መከላከያ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    ለሰባት ቀናት የዘለቀው የጋዛ የተኩስ አቁም ፋታ ማብቃቱን እና ጦርነት መቀጠሉን እስራኤል አስታወቀች።

    የእስራኤል ጦር ሐማስ ስምምነቱን ጥሷል ሲል ከሷል። "ሐማስ ሰብዓዊ የተኩስ አቁም ፋታውን በመጣስ ሮኬት ወደ እስራኤል አስወንጭፏል።

    የእስራኤል መከላከያ ኃይል በጋዛ ሰርጥ ከሐማስ ጋር የሚያደርገውን ጦርነት ቀጥሏል" ሲልም የእስራኤል መከላከያ መግለጫ አውጥቷል። እስራኤል ይህንን ማወጇን ተከትሎ እስራኤል በጋዛ ሰርጥ የአየር ጥቃቶች እየፈጸመች ስለመሆኑ ሪፖርቶች ወጥተዋል።

    የእስራኤል መከላከያ በበኩሉ " የሐማስ ኢላማዎችን እያጠቃሁ" ነው ብሏል። በኳታር አሸማጋይነት የተደረሰውን የተኩስ አቁም ፋታ ተከትሎ ሐማስ 110 ታጋቾችን ሲለቅ እስራኤል ደግሞ 240 ህጻናት እና ሴቶች ፍልስጤማውያን እስረኞችን ፈታለች።

  17. ብሊንከን ከእስካሁኑ ጠንከር ባለ መልዕክታቸው እስራኤል ሲቪሎችን እንድትታደግ ጠየቁ

  18. ሩስያ ታጋቾችን በመልቀቁ ሐማስን አመሰገነች

    የሩሲያ ሰንደቅ ዓላማ

    የፎቶው ባለመብት, AFP

    ሐማስ ሁለት ሩሲያዊ ታጋቾችን በትናንትናው ዕለት መልቀቁን ተከትሎ የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ምስጋናውን ለሐማስ አቅርቧል።

    ሩሲያ እንዳሳወቀችው ታጋቾቹ የተለቀቁት በእስራኤል እና ሐማስ ከተደረገው ስምምነት ጋር የተያያዘ አይደለም ብላለች።

    "ወገኖቻችን በትናንትናው ዕለት የተለቀቁት ከሐማስ አመራሮች ጋር ባደረግነው ስምምነት መስረት" ነው ብሏል።

    "ለጥያቄቻችን አዎንታዊ ምላሽ ለሰጡን የሐማስ አመራሮች ምስጋናችንን እናቀርባለን። በጋዛ ሰርጥ የተያዙ ሌሎች ሩሲያውያን እንዲለቀቁም ጥረታችንን እንቀጥላለን" በማለት ባወጣው መግለጫ አትቷል።

  19. በእየሩሳሌም በተከፈተ ተኩስ ሶስት ሰዎች ተገደሉ

    የእስራኤል ፖሊስ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    በእየሩሳሌም የአውቶብስ ጣቢያ በተከፈተ ተኩስ ሶስት ሰዎች ተገደሉ።

    ተኩሱ የተከፈተበት የስራ ሰዓት መግቢያ ላይ እንደሆነም ተነግሯል።

    ፖሊስ እንዳስታወቀው ማለዳ በስራ ሰዓት መግቢያ እና ሰዎች በሚበዙበት ወቅት ሁለት ታጣቂዎች ከእየሩሳሌም ወጣ ብሎ በሚገኘው የአውቶብስ ጣቢያ ላይ ተኩስ ከፍተዋል ብሏል።

    ፖሊስ ሪፖርቱ የደረሰው በአገሬው ሰዓት አቆጣጠር ከጥዋቱ 1 ሰዓት ከ40 መሆኑን አስታውቋል። በተኩሱም የ24 ዓመት ሴትን ጨምሮ ሶስት ሰዎች ሲገደሉ ስድስት ሰዎች ቆስለዋል።

    የእስራኤል ብሄራዊ ደህንነት ሚኒስትር ኢታማር ቤን ግቪር እንደተናገሩት ተኩሱን የከፈቱት ሁለት ግለሰቦች የሐማስ አባላት ናቸው ብለዋል።

    ግለሰቦቹም በምስራቅ እየሩሳሌም ነዋሪዎች መሆናቸውንም አክለዋል። "በግልጽ ሐማስ የፈጸማቸው ናቸው። በአንደኛው በኩል የተኩስ አቁም ይላሉ በሌላኛው የሽብር ተግባር ይፈጽማሉ" ሲሉ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

    የደረሰው ጥቃት በእስራኤል ውስጥ ላሉ ሰላማዊ ዜጎች የጦር መሳሪያ ማከፋፈል አስፈላጊነትን የሚያሳይ ነው ብለዋል።

  20. እስራኤል በዌስት ባንክ ባደረሰችው ጥቃት ሁለት ፍልስጤማውያን ልጆች ተገደሉ