በከፋው ድርቅ ምክንያት ግማሹ የሶማሊያ ሕዝብ ለረሃብ ተጋልጧል

የተንቀሳቃሹ ምስል መግለጫ, በተለይ ህጻናትን ለከፋ አካላዊና ሥነ ልቦናዊ ችግር የዳረገው የረሃብ አደጋ በሶማሊያ አሳሳቢ ሆኗል

በአራት አስርት ዓመታት ውስጥ ታይቶ የማይታወቅ የከፋ ድርቅ በአፍሪካ ቀንድ እየተከሰተ ነው።

የዓለም ምግብ ፕሮግራም በኬንያ፣ በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ በዚህ የአውሮፓውያን ዓመት መጨረሻ ለረሃብ የተጋለጡ ሰዎች ቁጥር እስከ 20 ሚሊዮን የሚደርስ መሆኑን አስታውቋል።

በአሁኑ ወቅት በሶማሊያ ግማሽ ያህሉ ሕዝብ ለረሃብ ተጋልጧል።

በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች ከሶማሊያ ገጠራማ አካባቢዎች ቀያቸውንና ቤታቸውን ጥለው ወደ ተፈናቃዮች መጠለያ ማዕከላት እያመሩ ነው።

ማሳቸው ባዶ ነው፣ አዝመራው አልያዘም፣ የሞቱ እንስሳት በየጎዳናዎቹ ላይ ይታያሉ። ባለፉት አስርት ዓመታት ከታየው የከፋ ድርቅ እንደሆነ ባለሙያዎች የሚገልጹ ሲሆን ረሃብም ተጋርጦባታል።

በመጠለያ ማዕከላቱ ውስጥ ያለ ወላጆቻቸው በሺዎች የሚቆጠሩ ህጻናት አሉ።

አባቶች ምግብ ፍለጋ ወደ ከተማ በመውጣታቸው እንዲሁም ከፍተኛ በሆነ የምግብ እጦት ምክንያት እናቶች ወደ ሆስፒታሎች በመግባታቸው የቤቱ ትልልቅ ወንድሞችና እህቶች ታናናሾቻቸውን የመንከባከብ ሚና ወስደዋል።

በአሁኑ ወቅት በረሃብ የሚሞቱ ሰዎች እንዳሉ እየተመዘገበ ነው። በባይዶዋ በሚገኝ አንድ ማዕከል ከግንቦት እስከ ሰኔ ባለው ጊዜ ውስጥ ቢያንስ 26 ህጻናት መሞታቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ።

“ቀድሞ አብረን እንጫወት የነበሩ ጓደኞቼ አንዳንዶቹ በህይወት አሉ። አንዳንዶቹ ሞተዋል፣ ሌሎች ደግሞ ወደ ዋና ከተማዋ ሞቃዲሾ ተሰደው በቤት ሰራተኝነት ተቀጥረዋል” በማለት በባይዶዋ ጊዜያዊ መጠለያ ነዋሪ የሆነችው የ13 ዓመቷ ፈርዶሳ ለቢቢሲ ተናግራለች።

የበጎ አድራጎት ተቋሙ ሴቭ ዘ ችልድረን በህፃናት እና በእንክብካቤ ሰጭዎቻቸው ላይ የሥነ ልቦና ጭንቀቶች መጨመሩን መመልከታቸውን አሳውቋል።

"ከገመገምናቸው ህጻናት መካከል ወደ 72 በመቶ የሚጠጉት የሥነ-ልቦና ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል። ወላጆች ህፃናቱ ጠበኛና አላስፈላጊ ባህርይ እያየንባቸው ነው በማለት ሪፖርት እያደረጉልን ነው” ይላሉ የድርጅቱ የሶማሊያ ዳይሬክተር መሃሙድ ሐሰን።