በኮንሶ በምግብ እጥረት ምክንያት ሕጻናት መሞታቸው ተነገረ

የኮንሶ አርሶ አደር በማሳ ውስጥ

የፎቶው ባለመብት, KULE

በደቡብ ክልል ውስጥ በሚገኘው ኮንሶ ዞን በተከሰተ የምግብ እጥረት ሳቢያ 13 ሕጻናት መሞታቸውን የዞኑ ዋና የመንግሥት ተጠሪ ለቢቢሲ ተናገሩ።

በኮንሶ ዞን ባለፉት ሦስት ተከታታይ ዓመታት የሚጥለው ዝናብ ወቅቱን የጠበቀ ባለመሆኑ እንዲሁም በተከታታይ በነበሩ ግጭቶች የተነሳ ለከፋ ረሃብ የተጋለጡ ሰዎች ቁጥር መጨመሩን ባለሥልጣኑ አስረድተዋል።

አቶ ተስፋዬ ጫሬ የኮንሶ ዞን ዋና የመንግሥት ተጠሪ ለቢቢሲ እንዳሉት፣ ከሐምሌ 01/2014 ዓ.ም. ጀምሮ ባሉት ስድስት ወራት በዞኑ አስቸኳይ የምግብ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ሰዎች ቁጥር 190 ሺህ 825 ይሆናል።

ከእነዚህ መካከል 122 ሺህ 735 በዝናብ እጥረት ምክንያት ለችግር የተጋለጡ ሲሆኑ፣ በግጭት ምክንያት ተፈናቅለው እርዳታ የሚጠብቁ ደግሞ 68,087 መሆናቸውን አመልከተዋል።

በካራት ሆስፒታል ሄድ ነርስ የሆነው እና በምግብ እጥረት የተጎዱ ሕጻናት ክፍል የሚሰራው ሰምበቶ በሪሻ ለቢቢሲ እንደተናገረው ወደ ሆስፒታላቸው በምግብ እጥረት ተጎድተው የሚመጡ ሕጻናት ቁጥር በየጊዜው እየጨመረ ነው።

ከዚህ ቀደም በወር እስከ 40 ሕጻናት በምግብ እጥረት ተጎድተው ይመጡ እንደነበር አስታውሶ፣ በአሁን ሰዓት ግን ይህ ቁጥር በእጥፍ አድጎ እስከ 80 ሕጻናት በምግብ እጥረት ተጎድተው እንደሚመጡ ገልጿል።

ወደ ካራት ሆስፒታል የሚመጡ አብዛኞቹ ሕጻናት ከገጠር ቀበሌዎች መሆኑን ያስታወሰው አቶ ሰምበቶ፣ በግጭት ምክንያት ከሰገን ዙሪያ የተፈናቀሉ እንደሚገኙበትም ገልጿል።

በምግብ እጥረት ከተጎዱ ሕጻናት መካከል ዘግይተው ወደ ሆስፒታላቸው በመምጣታቸው ምክንያት ሕይወታቸው ያለፈ እንደሚገኝበትም ተናግረዋል።

አቶ ተስፋዬ በበኩላቸው በኮንሶ ዞን ስር በሚገኙት ሦስት ወረዳዎች በምግብ እጥረት የተጎዱ እንዲሁም በምግብ እጥረት ምክንያት በጽኑ የታመሙ እና ወደ ጤና ተቋም የመጡ ሕጻናት ቁጥር መጨመሩን አስረድተዋል።

244 በምግብ እጥረት ምክንያት የተጎዱ ሕጻናት በሕክምና ተቋማት የጽኑ ሕሙማን ክፍል ውስጥ እንደሚገኙም ጨምረው ገልፀዋል።

ዞኑ የአካባቢውን የምግብ ዋስትና ሁኔታ ለመተንበይ ይቻል ዘንድ የአደጋ ስጋት አመልካች መረጃዎችን ዳሰሳ ማድረጉን አቶ ተስፋዬ ለቢቢሲ ገልፀዋል።

በዚህም የ2014 ዓ.ም. በልግ ቅድመ ምርት ዳሰሳ ጥናት የዝናብ፣ የሰብል ሁኔታ፣ የእንስሳት መኖና የመጠጥ ውሃ አቅርቦት እንዲሁም የጤና ሁኔታ፣ የሰው ጤናና ሥርዓተ-ምግብ፣ የሰው ጤናና መጠጥ ውሃ አቅርቦት ሁኔታ፣ የሰብልና እንስሳት ገበያ አቅርቦትና ዋጋ ሁኔታን ዳሰሳ ማድረጋቸውን ይናገራሉ።

“ከእግዚአብሔር ወይ ከመንግሥት እየጠበቅኩ ነው”

እየደረቀ ያለ ሰብል በኮንሶ

የፎቶው ባለመብት, KULE

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

አቶ ኮታና አሌ ለሚታ በኮንሶ ዞን ካራት ዙሪያ ወረዳ ሶሮቦ ቀበሌ ነዋሪ ናቸው።

የ12 ልጆች አባት የሆኑት አቶ ኮታና ባለፉት ዓመታት ጤፍ፣ ማሽላ፣ በቆሎ፣ ዳጉሳ እና አደንጓሬ ቢዘሩም በዝናብ እጥረት ምክንያት ለፍሬ እንዳልበቃ ይናገራሉ።

ላለፉት ሦስት ወራት በቂ ዝናብ እንዳልዘነበ አስታውሰው፣ ይህ ላለፉት ሦስት ዓመታት በተደጋጋሚ በማጋጠሙ ለከፋ ችግር መጋለጣቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በአሁኑ ሰዓት በጎተራቸው ያላቸውን በልተው ጨርሰው ባዶ እጃቸውን መቅረታቸውን የሚናገሩት አቶ ኮታና፣ አንዳች ነገር “ከእግዚአብሔር ወይ ከመንግሥት እየጠበቅኩ ነው” ይላሉ።

እንዲህ ዓይነት ድርቅ በእድሜያቸው ለሁለተኛ ጊዜ ማጋጠሙ የሚናገሩት አቶ ኮታና፣ ለመጀመሪያ ጊዜ በ1977 ዓ.ም. ተመሳሳይ ክስተት ማጋጠሙን ያስታውሳሉ።

የኮንሶ ዞን ዋና የመንግሥት ተጠሪ አቶ ተስፋዬ እንደሚሉት በዞኑ በምግብ እጥረት ምክንያት የተጎዱ አዋቂዎች ቁጥርም እየጨመረ ነው።

“አዋቂዎች የሚነግሩን አሁን ያለው ረሃብ ከ77ቱ የባሰ መሆኑን ነው” የሚሉት አቶ ተስፋዬ፣ ከክልሉ እና ከፌደራል መንግሥት ባሻገር በዞኑ የሚንቀሳቀሱ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ድጋፍ እንዲያደርጉ መጠየቃቸውን ገልፀዋል።

በኮንሶ ዞን ውስጥ በሚገኙ ሦስት ወረዳዎች በተከታታይ ዓመታት ዝናብ ዘግይቶ መግባቱን እና ቀድሞ ማቋረጡን፤ በተጨማሪ ስርጭቱ ሲታይ በቦታም ሆነ በጊዜ የተስተካከለ አለመሆኑን ጠቅሰው፣ በዚህ የተነሳ የተዘራው ሰብል በቂ ምርት ሳይሰጥ መቅረቱን ጠቁመዋል።

በዞኑ በዝናብ እጥረት የተነሳ ሙሉ በሙሉ ለማለት በሚያስችል መልኩ የተዘራ ሰብል መጥፋቱን አቶ ተስፋዬ ጨምረው ተናግረዋል።

አቶ ተስፋዬ አክለውም ከአጎራባች ልዩ ወረዳዎች እና ቀበሌዎች ጋር በተፈጠሩ ግጭቶች ምክንያት ብዙ ማሳዎች በበልጉ ወቅት በዘር ሳይሸፈኑ ቀርተዋል።

ግጭቱ ለረጅም ጊዜ የቆየ በመሆኑም በ2013/14 ዓ.ም. መኸር ወቅት የተዘሩ ማሳዎችም ቢኖሩም ምርቱ በአግባቡ ሳይሰበሰብ ለውድመት በመደረጉ ምክንያት በበልጉ የምግብ ዋስትና ሁኔታ ላይ ከፍተኛ ጫና ሊፈጥር ችሏል።

ዳግም ከመጋቢት 01/2014 ዓ.ም. ጀምሮ በተፈጠረው ግጭት በኮልሜ ክላስተር ሦስት ቀበሌዎች (ቦርቃራ፣ ማደራ ግዛባ እና ማሶያ) በሰገን ዙሪያ ወረዳ ሰባት ቀበሌዎች (ጋርጨ፣ አይሎታ ዶካቱ፣ አዲስ ገበሬ፣ በቾ፣ ሠገን ከተማ፣ ሠገን ገነት፣ መለካና ዱጋያ) እንዲሁም በካራት ዙሪያ ወረዳ አራት ቀበሌዎች (ገላቦ፣ አርፋይዴ፣ በዓይዴና ፉጩጫ) ላይ የተወሰኑ የእርሻ መሬቶች በዘር ባለመሸፈናቸው እንዲሁም የተዘራውም ሰብል መሰብሰብ ባለመቻሉ ለምግብ ምርት መታጣት ምክንያት መሆኑን ጠቅሰዋል።

በዞኑ የተሻለ ሰብል አምራች የነበሩ አካባቢዎችም ቢሆኑ በግጭት ምክንያት በአግባቡ አለመዝራታቸውን፣ በሌሎች ወረዳዎችም ተዘርተው የነበሩ ሰብሎች ለመኖ እንኳ ሳይደርሱ መድረቃቸውን ጨምረው አስረድተዋል።

በአካባቢው ከብት በማድለብ የሚታወቅ ቦታ ላይ የመኖ እጥረት መፈጠሩ እንዲሁም ፍየሎች የሚመገቡት ቅጠል ጭምር እየደረቀ በመሆኑ አርሶ አደሮች ከፍተኛ ስጋት ውስጥ መውደቃቸው ተነግሯል።

እንደ አቶ ተስፋዬ ገለጻ ከሆነ በአሁን ሰዓት ዝናብ ቢጥል እንኳ ለእንስሳት መኖ ጠቃሚ ቢሆንም አርሶ አደሮች ግን ሰብል ቢዘሩም ከቀጣይ ዓመት ታኅሣሥ በኋላ ብቻ ምርት መሰብሰብ ቢችሉ ነው።

በዞኑ ከ5 ሚሊየን በላይ የቤት እንስሳት መኖራቸውን ያስታወሱት ኃላፊው፣ ዝናብ በወቅቱ መጣል ካልቻለ እነዚህ እንስሳት አደጋ ላይ እንደሚወድቁ ይናገራሉ።

ዞኑ በምግብ እጥረት፣ በግጭት እና በኑሮ ውድነት እየተፈተነ መሆኑን ያነሱት ኃላፊው፣ ግጭት በተከሰተባቸው አካባቢዎች 20 ትምህርት ቤቶች በመቃጠላቸው የተነሳ 10 ሺህ 430 ተማሪዎች ትምህርታቸውን አቋርጠዋል።

እነዚህ ትምህርት ቤቶች ከአሁኑ ጥገና ካልተደረገላቸው በ2015 ዓ.ም ተማሪዎቹ ከትምህርት ገበታ ውጪ ሆነው እንደሚቆዩ ስጋታቸውን ይገልጻሉ።

የደቡብ ክልል የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ጋንታ ጋምኣ በኮንሶ ዞን በተለያየ ወቅት በተፈጠሩ ግጭቶች ምክንያት ለተፈናቀሉ እንዲሁም ሰብላቸው በዝናብ እጥረት ምክንያት ለተጎዳባቸው ሰዎች የምግብ እርዳታ እየቀረበ መሆኑን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

አቶ ተስፋዬ በበኩላቸው የሴፍቲኔት እርዳታው እየቀረበ ቢሆንም በቂ አለመሆኑን ያስረዳሉ።

በደቡብ ኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ውስጥ የሚገኘው የኮንሶ ዞን፣ ኮልሜ ክላስተርን ጨምሮ በሦስት ወረዳዎች እንዲሁም በአንድ የከተማ አስተዳደር የተዋቀረ ነው።

በአካባቢው ባሉ ማኅበረሰቦች መካከል በይዞታ ይገባኝል ምክንያት በተደጋጋሚ በተከሰቱ ግጭቶች በርካታ ሰዎች የሞትና የአካል ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን፣ ቤት ንብረታቸው ወድሞ የተፈናቀሉት ጥቂት የሚባሉ አይደሉም።