በኢትዮጵያ 200 ሺህ የሚጠጉ ሕጻናት አስከፊ የምግብ እጥረት አጋጥሟቸዋል፡ ሴቭ ዘ ችልድረን

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በኢትዮጵያ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ሕጻናት በአስከፊ የምግብ እጥረት እየተሰቃዩ መሆኑን ሴቭ ዘችልድረን ገለጸ።
ዓለም አቀፍ ግብረ ሰናይ ተቋም የሆነው የሕጻናት አድን ድርጅት (ሴቭ ዘ ችልድረን) እንዳስታወቀው 185 ሺህ ኢትዮጵያውያን ሕጻናት ለከፋ የምግብ እጥረት ተጋልጠዋል።
የኢትዮጵያ አብዛኛው ክፍል በአርባ ዓመት ውስጥ ታይቶ በማይታወቅ ድርቅ ተጋልጧል ያለው ድርጅቱ፣ ሕጻናት በተለይም ጨቅላዎች በረሃብ አለንጋ እየተገረፉ መሆኑን ገልጿል።
የሴቭ ዘ ችልድረን የኢትዮጵያ ተወካይ ዣቪየር ጆበርት እንዳሉት እየተስፋፋ ያለውን ድርቅ የመቋቋም አቅሙም በግጭትና በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ተዳክሟል።
ነዋሪዎች እንስሳቶቻቸው ስለሚሞቱባቸው ባዶ እጃቸውን ቀያቸውን ጥለው ለመውጣትም መገደዳቸውን ዣቪየር አክለዋል።
"አራት የዝናብ ወቅቶች ተጨናግፈዋል። አምስተኛውም እንዲሁ ሊያልፍ ይችላል" ያለው ድርጅቱ፤ 30 ሚሊየን ኢትዮጵያውያን የሰብዓዊ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው አሳስቧል።
ግብረ ሰናይ ድርጅቱ የምግብ እጥረቱ ባለፉት 12 ወራት ብቻ 64 በመቶ መጨመሩን ገልጾ፣ ከዚህም ሊከፋ እንደሚችል አስጠንቅቋል።
ጨምሮም በአፍሪካ ቀንድ ያለው ቀውስ በኮቪድ ወረርሽኝ ፣ በዩክሬን እየተካሄደ ባለው ጦርነት ሳቢያ በተከሰተ የምግብ ዋጋ ንረት እና በድጋፍ እጥረት ተባብሷል ብሏል።
የተከሰተው አስከፊ የምግብ እጥረት በሚቀጥሉት ሁለት ወራት ውስጥ የበለጠ እንደሚባባስ የገለጸው ድርጅቱ፣ አስቸኳይ እርዳታ እንዲደረግ ጥሪ አቅርቧል።
"ረሃብ አስከፊ በመሆኑ አሁን ላይ እንስሳትም ሴቶችና ሕጻናትን መተናኮስ ጀምረዋል" ብሏል ድርጅቱ።
በምሥራቅ ኢትዮጵያ፣ ሶማሌ ክልል፣ ነዋሪዎች የተራቡ ዝንጀሮዎችን ዱላ ይዘው መከላከል ተጨማሪ ፈተና እንደሆነባቸው ድርጅቱ አብነት ጠቅሷል።
ሕጻናትም የዚሁ ቀውስ ገፈት ቀማሽ ሆነዋል፤ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩትም ለከፋ የምግብ እጥረት ተጋልጠዋል።
“ይህ በሽታ የመከላከል አቅማቸውን የሚያዳክም ለሕይወት አስጊ የሆነ ሁኔታ ነው። በመሆኑም ለሌላ ህመም ከተዳረጉ ሊሞቱ ይችላሉ” ሲልም አስጠንቅቋል።
ከወራት በፊት ዓለም አቀፉ የሕጻናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) በአፋር፣ በአሮሚያ፣ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች እንዲሁም በሶማሌ ክልሎች የከፋ ድርቅ ማጋጠሙንና ሚሊዮኖች ለችግር መጋለጣቸውን ማስታወቁ ይታወሳል።
ድርጅቱ በአራቱ ክልሎች የተከሰተው በአራት አስርተ ዓመታት ውስጥ ታይቶ የማይታወቅ ድርቅ 7 ሚሊየን ዜጎች ላይ አስከፊ ችግር በመደቀኑ አስቸኳይ ሰብዓዊ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው አሳስቦ ነበር።
በክልሎቹ ባጋጠመው ድርቅ ምክንያት በርካታ እንስሳት ሞተዋል፤ ሰብሎች ወድመዋል፤ የውሃና የምግብ እጥረት በርካቶችን አፈናቅሏል።
በቅርቡም በአፋር ክልል በጦርነት እና በተፈጥሯዊ አደጋዎች ምክንያት ከ1.3 ሚሊየን በላይ ሕዝብ ለምግብ እጥረት መጋለጡንና እየቀረበ ያለው እርዳታም በቂ አለመሆኑን የክልሉ ባለሥልጣናት አስታውቀዋል።
በዚህም ሳቢያ ሕጻናት ሕይወታቸው እያለፈ መሆኑን ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ገልጸዋል።
በ40 ዓመታት ውስጥ ታይቶ አይታወቅም በተባለው በዚህ ድርቅ ሌሎች የምሥራቅ አፍሪካ እና አፍሪካ ቀንድ አገራትም እየተፈተኑ ነው።
የኢትዮጵያ ጎረቤት አገራት የሆኑት ኬንያ እና ሶማሊያም የተወሰኑ አካባቢዎቻቸው በዚሁ ድርቅ ተጎድተዋል።
ግንቦት ወር የተባበሩት መንግሥታት ባለፉት ሁለት ዓመታት ብቻ አፍሪካ ከየትኛውም አህጉር በላይ በከፋ ድርቅ መጠቃቷን አስታውቆ ነበር።
ድርጅቱ በድርቅ፣ በበረሃማነት እና በመሬት መራቆት ዙርያ በአይቮሪ ኮስት ባካሄደው ስብሰባው ላይ ዘንድሮም ዝናብ ባለመኖሩ 20 ሚሊየን ሰዎች ስጋት ላይ ናቸው ብሏል።
በስብሰባው ወቅት ይፋ እንደተደረገው ሪፖርት ከሆነ፣ ባለፉት ሁለት ዓመታት በድርቅ ምክንያት አስቸኳይ ጊዜ ካወጁ 23 አገራት መካከል 14ቱ ከአፍሪካ ናቸው።
እአአ ከ2000 እስከ 2019 ከተመዘገቡት 134 ድርቆች መካከል በአህጉሪቱ የተከሰቱ መሆናቸውንም ሪፖርቱ አመልክቷል።
በምሥራቅ አፍሪካ እና በአፍሪካ ቀንድ በተከሰተው በዚህ ድርቅ 20 ሚሊዮን ሰዎችን ለከፋ ረሃብ ሊጋለጡ ይችላሉ ሲልም ድርጅቱ ስጋቱ መግለጹ ይታወሳል።












