አፍሪካን ክፉኛ እያጠቃት ባለው ድርቅ ላይ ዓለም አቀፍ ስምምነት መደረስ ለምን አልተቻለም?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ከየትኛውም አህጉር በላይ ባለፉት ሁለት ዓመታት ብቻ በከፍተኛ ድርቀች የተጠቃችው አፍሪካ፣ ዘንድሮም ዝናብ ባለማግኘታቸው 20 ሚሊዮን ሰዎች ስጋት ላይ መሆናቸውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስታውቋል።
በድርቅ፣ በበረሃማነት እና በመሬት መራቆት ዙሪያ የተካሄደውን የዚህን ወር የመንግሥታቱ ድርጅት ስብሰባ አይቮሪ ኮስት አስተናግዳለች።
ለሁለት ሳምንታት በዋና ከተማዋ አቢጃን ውስጥ በተስተናገደው ስብሰባ ችግሮቹን ለመቅረፍ ብዙም ርቀት መጓዝ አልተቻለም።
እአአ በ1970 የካርቦን ልቀትን ለመቀነስ የተደረሰው የኪዮቶ ስምምነት አይነት ተመሳሳይ ዓለም አቀፍ ስምምነት፣ ድርቅን ለመዋጋት እንዲደረግ በርካታ የአፍሪካ አገራት መሞገታቸውን ቢቢሲ ለማወቅ ችሏል።
ዩጋንዳ እና አንጎላ ደግሞ የአፍሪካን ድምጽ ከፍ አድርገው ለማሰማት ግንባር ቀደም የሆኑት ናቸው።
አገራቱ ጉዳዩ የአፍሪካ ችግር ብቻ እንዳልሆነም ለማሳወቅ ጥረዋል። ዓለም አቀፍ ትኩረት እንዲያገኝና እንደ ዓለም አቀፍ ችግር እንዲታይ ነው ፍላጎታቸው።
ድርቅ የሚስፋፋው በአየር ንብረት ለውጥ በመሆኑ፣ ዓለም አቀፍ እርምጃ ብቻ እንደሚያስተካክለው ይሞግታሉ። በአፍሪካ የመሬት መራቆት እና በረሃማነት ተጨማሪ ምክንያት ናቸው።
"የአፍሪካ ብቻ ሳይሆን ዓለም አቀፍ ችግር ነው" ያሉት የዩጋንዳው ተደራዳሪ ካባንጎ ፍሬዲ ናቸው።
"በመንግሥታቱ ድርጅት የበረሃማነትን መከላከል ጥላ ስር የሚገኙ ሁሉም አገራት ሕጋዊ የሆነ ተመሳሳይ አቋም ቢይዙ፣ በድርቅ የተጎዱ ማኅበረሰቦችን መርዳት ወይም ተጋላጭ የሆኑትን መደገፍ ይቻላል።"
ሃሳቡ ከተቀረው ዓለም ይሁንታ አላገኘም። ችግሩን ለመቅረፍ እንደ የተባበሩት መንግሥታት የበረሃማነትን መከላከል፣ ዘላቂ ልማት ጎሎች ወይም የፓሪሱ የአየር ንብረት ለውጥ ስምምነትን የመሳሰሉ ሌሎች ዓለም አቀፍ ስምምነቶች አሉ ሲሉም ይሞግታሉ።
ሌላ ስምምነት መፍጠር አይበጅም ባይ ናቸው።
ላቲን አሜሪካን እና ካሪቢያንን የወከሉት አርጀንቲና እና ዶሚኒካን ሪፐብሊክ እንደሚሉት በድርቅ እና በረሃማነት የተጎዱ አገራትን ለመርዳት ከፍተኛ የገንዘብ እና የቴክኒክ ድጋፍ ያስፈልጋል ብለዋል።
ተደራራቢ ስምምነት ከመፈጸም ይልቅ ያሉትን መተግበር ያስፈልጋል ያለው ደግሞ የአውሮፓ ሕብረት ነው።
በመጨረሻም ወደ መሐል በመምጣት የስምምነቱ ጉዳይ ከሁለት ዓመት በኋላ እንዲታይ እና በድርቅ መከላከል ዙሪያ የሚሠራ የበይነ መንግሥታት ቡድን እንዲቋቋም ተወስኗል።
ቡድኑ በጉዳዩ ዙሪያ ሪፖርቱን እአአ በ2024 ያቀርባል። በዚያ ወቅት የድርቅ፣ የበረሃማነት እና የመሬት መራቆት ችግር ከፍተኛ ይሆናል።
በ2030 አንድ ቢሊዮን ሄክታር የተራቆተ መሬትን ወደ ነበረበት ለመመለስ ስብሰባው ተስማምቷል። እንደዚህ ቀደሞቹ ግቦቹ ሁሉ ይህም የተለጠጠ ዕቅድ አይሳካም የሚል ፍራቻ ያደረባቸው አሉ።
ለግጭት ምክንያት የሆነው የመሬት እጦት
በስብበሳው ላይ ይፋ በተደረገ ሪፖርት መሠረት ባለፉት ሁለት ዓመታት በድርቅ ምክንያት አስቸኳይ ጊዜ ካወጁ 23 አገራት 14ቱ ከአፍሪካ ናቸው።
"አፍሪካ ከየትኛውም አህጉር በላይ በድርቅ በተደጋጋሚ ትጠቃለች። እአአ ከ2000 እስከ 2019 ከተመዘገቡት 134 ድርቆች 70ዎቹ በአህጉሪቱ የተከሰቱ ናቸው" ይላል ሪፖርቱ።
የበይነ መንግሥታት የአየር ለውጥ ስብስብ በቅርቡ ይፋ ባደረገው ሪፖርቱ ድርቅ በአፍሪካ መጨመሩን ገልጿል። ይህም በይበልጥ እንደሚያድግ አስታውቋል።
ሁለት ሦስተኛው የአፍሪካ ክፍል በረሃማ እና ደረቅ ነው። ለእርሻ የሚሆን ትንሽ ቦታ ነው ያለው። እንደ መንግሥታቱ ድርጅት ከሆነ ደግሞ መታረስ ከሚችለው መሬትም 65 በመቶ የሚሆነው ተራቁቷል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ዘላቂነት በሌለው ግብርና እና በከፍተኛ የምግብ ምርት ምክንያት የመሬት ምርታማነት በከፍተኛ ደረጃ ተጎድቷል።
ጥናቶች እንደሚያሳዩት አፍሪካ በየዓመቱ አራት ሚሊዮን ሄክታር ደን ታጣለች። በብዙ አገራት ከሰል ማምረት ለደን መመናመን ዋነኛው ስጋት ሆኖ እንደቀጠለ ነው።
እንደ ተመድ ከሆነ 45 በመቶ የሚሆነው የአፍሪካ መሬት በድርቅ መስፋፋት የተጎዳ ነው። ከግማሽ በላይ የሚሆነው ደግሞ በድርቅ መስፋፋት ተጨማሪ ጉዳት ይደርስበታል የሚል ስጋት አለ።
"ከዓመት ዓመት መጥፎ ነገሮችን እያየን ነው" ያሉት የዓለም አቀፉ የቀይመስቀል ማኅበር የአፍሪካ ዳይሬክተር ፓትሪክ ዩሱፍ ናቸው።
የበረሃማነት መስፋፋት ደግሞ ለምርታማ መሬቶች ሽሚያ ሲዳርግ ይህም ወደ ግጭት ያመራል።
"እንደ ሰሜን ማሊ ባሉ አካባቢች የመሬት መራቆት፣ በረሃማነት እና ድርቅ የግጦሽ መሬት እና ውሃ እንዲጠፋ ምክንያት እየሆነ ነው። በዚህ ምክንያት አርብቶ አደሮች ወደ ሌሎች ማኅበረሰቦች የእርሻ መሬቶች እየገቡ ነው" ብለዋል ዩሱፍ።
"ለአርሶ አደሮች መሬት ስጡ"
ብዙ የአፍሪካ ሃገራት እአአ ከ1999 ጀምሮ የመሬት መራቆትን እና በረሃማነትን ለመከላከል አካባቢያዊ ዕቅድ አውጥተዋል።
ባለፈው ዓመት በዓለም የምግብ እና እርሻ ድርጅት እንዲሁም በአፍሪካ ሕብረት በታተመ ሪፖርት መሠረት በቂ የሆነ እርምጃ አልተወሰደም።
ከስብሰባው ቀደም ብሎ ይፋ በተደረገ ሌላ ሪፖርት መሠረት ከ4 እስከ 20 በመቶ የሚሆነው የታላቁ የአረንጓዴ ግንብ ዕቅድ (Great Green Wall initiative) ግብ ብቻ ነው የተሳካው።
ሃሳቡ ይፋ የሆነው በ2007 ሲሆን በ2030 በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዛፎችን፣ ሳር እና አትክልቶችን ከምዕራብ አፍሪካዋ ሰኔጋል እስከ ምሥራቅ አፍሪካዋ ጅቡቲ ድርስ ባሉ 11 አገራት በመትከል 100 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በደን ለመሸፈን ያቀደ ነው።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የዎርልድ ቪዥን የአየር ንብረት አማካሪ ቶኒ ሪናውዶ ከመንግሥት ሃሳብ በመቃረን መንግሥታት በአርሶ አደሮች እጅ የሚገኘውን የአርሻ መሬት ማሳደግ አለባቸው ይላሉ።
"የገጠር የኅበረተሰቦች የራሳቸው ያልሆነን እና በሕግ እንደሚጠቀምበት ያልተገለጸላቸው መሬትን እንዲንከባከቡ መጠበቅ የሚያስገርም ነው" ብለዋል።
ባለቤትነት ብቻ ግን ችግሩን አይፈታውም። የአየር ንብረት ለውጥም ለድርቁ ምክንያት እየሆነ ነው።
አሁን እንኳን በምሥራቅ አፍሪካ እና በአፍሪካ ቀንድ የተከሰተው ድርቅ 20 ሚሊዮን ሰዎችን ለከፋ ረሃብ ሊያጋልጥ ይችላል።
ችግሩ ከተከሰተባቸው መካከል አንዷ ኢትዮጵያ ናት። ድርቁን ለመከላከል ብዙ ዝግጅቶችን ብታደርግም ካለፉት ሃምሳ ዓመታት የከፋው ነው በተባለለት ድርቅ እየተፈተነች ነው።
"ምስጋና ወደነበረበት ለተመለሰው እና የመቋቋም አቅም ለነበረው መሬቷ ይሁንና፣ ኢትዮጵያ ለአምስት ዓመታት ያህል ድርቅን መቋቋም ችላለች" ያሉት የዩኤንሲዲዲ ኃላፊዋ ሉዊዝ ቤከር ናቸው።
"አሁን በአፍሪካ ቀንድ ያለው ድርቅ በጣም ከባድ ነው። ስለዚህም መሬቱ መቋቋም አልቻለም። በአንድ በኩል ለውጥ ማምጣት ቢቻልም የአየር ንብረት ወደነበረበት የተመለሰው መሬት ላይ ከፍተኛ ጫና ፈጥሯል" ብለዋል።












