ከ10 ሚሊዮን በላይ የአፍሪካ ቀንድ ሕዝብ ለከፋ ረሃብ ተጋልጧል-የዓለም ምግብ ፕሮግራም

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በአፍሪካ ቀንድ በተከሰተው ድርቅ ምክንያት 13 ሚሊዮን ሰዎች ለከፋ ረሃብ መጋለጣቸውን የተባበሩት መንግሥታት የዓለም ምግብ ፕሮግራም አስታወቀ።
በድርቁ ምክንያት ምርት በመታጣቱና በምግብ እጥረት በርካታ ቤተሰቦችን እንዲፈናቀሉ ምክንያት ሆኗል ያለው የዓለም ምግብ ፕሮግራም፤ ሰብዓዊ ቀውስን ለመከላከል አፋጣኝ እርዳታ ያስፈልጋል ብሏል።
በአፍሪካ ቀንድ ባጋጠመው ሦስት ተከታታይ የዝናብ ወቅቶች መጨናገፍ በተከሰተ ድርቅ በርካታ እንስሳት ሞተዋል እንዲሁም ሰብሎች ወድመዋል ብሏል ተቋሙ።
በኢትዮጵያ፣ በሶማሊያ እና በኬንያ 13 ሚሊዮን ነዋሪዎች ለረሃብ ተዳርገዋል።
የምግብ ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ ማሻቀብና የሚሰበሰብ ምርት አናሳ በመሆኑ ነዋሪው ምግብ ለማግኘት ከፍተኛ ጫና አሳድሮባቸዋል።
አፋጣኝ ዕርዳታ ከሌለ ሰብዓዊ ቀውስ ማስቀረት አይቻልም ሲል የዓለም ምግብ ፕሮግራም ተናግሯል።
ለዚህ ድርቅ ምላሽ ለመስጠት ድርጅቱ 327 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ የጠየቀ ሲሆን ይህም በአጭር ጊዜ ውስጥ የምግብ እና የገንዘብ ድጋፎችን ለማቅረብ ያስችላል ብሏል።
ለረጅም ጊዜም አነስተኛ ዝናብ እና ድርቅ በሚከሰትባቸው በአርሶ አደሩ ማኅበረሰቦች መካከል የመቋቋም አቅምን ለመጨመር እንዲያስችልም ድጋፍ እንደሚያስገው ገልጿል።
በአፋር፣ በኦሮሚያ፣ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና እና ሕዝቦች እንዲሁም በሶማሌ ክልሎች የከፋ ድርቅ በማጋጠሙ ሚሊዮኖች ለችግር መጋለጣቸውን ዩኒሴፍ ከሰሞኑ መግለጹ የሚታወስ ነው።
በአራት አስርት ዓመታት ውስጥ ለከፋ ድርቅ መጋለጣቸው የተገለጸው ደቡብ፣ የኦሮሚያና የሶማሌ ክልልን ጨምሮ በአራቱ ክልልሎች 7 ሚሊዮን በሚሆኑ ነዋሪዎች ላይ አስከፊ ችግር በመደቀኑ አስቸኳይ ሰብዓዊ እርዳታ ሊደርስላቸው እንደሚገባ ተገልጿል።












