ኬንያ 1ሚሊዮን ዶላር ሽልማት አዘጋጅታለት የነበረውን የዱር እንስሳት ‘አዘዋዋሪ’ ያዘች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የኬንያ ፖሊስ በድንበር ተሻጋሪ ሕገ ወጥ የዱር አራዊትና አደንዛዥ ዕፅ ዝውውር ላይ ከተሰማራ ቡድን ጋር ግንኙነት አለው ተብሎ ተጠርጥሮ በአሜሪካ ፍርድ ቤት ክስ የተመሰረተበትን ግለሰብ በቁጥጥር ስር አዋለ።
አብዲ ሁሴን አህመድ ወይም በቅጽል ስሙ አቡ ካዲ፤ በማዕከላዊ ኬንያ ሜሩ ተብሎ በሚጠራ አካባቢ ነበር ማክሰኞ ዕለት በቁጥጥር ስር መዋሉን ፖሊስ የገለጸው።
አሜሪካ ግለሰቡን ለማግኘት የሚረዳ መረጃ ላለው ሰው የአንድ ሚሊዮን ዶላር የወሮታ ክፍያ አዘጋጅታ ነበር።
ተከሳሹ አህመድ እ.ኤ.አ. በ2019 በኒውዮርክ ፍርድ ቤት የአውራሪስ ቀንድ እና የዝሆን ጥርስን በሕገ ወጥ መልኩ ለማዘዋወር በማሴር ወንጀል ክስ ተመስርቶበት ነበር።
ከዚህ በተጨማሪም ቢያንስ አንድ ኪሎ ሄሮይን ለማዘዋወር በማቀድ ወንጀልም ሌላ ክስም ቀርቦበት ነበር።
ከእርሱ በተጨማሪ ሌሎች ሦስት ሰዎች ክስ ተመስርቶባቸው ነበር።
ለሰባት ዓመታት ያህልም ከኬንያ፣ ከኡጋንዳ፣ ከዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ ከጊኒ፣ ከሞዛምቢክ፣ ከሴኔጋል እና ከታንዛኒያ ሰባት ሚሊዮን ዶላር የሚገመት 190 ኪሎ ቀንድ እና 10 ቶን የዝሆን ጥርስ በድብቅ ለማዘዋወር ማሴራቸው ተዘግቧል።
ለዚህም ሲባል ከ35 በላይ አውራሪሶች እና ከ100 በላይ ዝሆኖችን በሕገ ወጥ አደን ኢላማ ማድረግን ይጠይቃል።
ቀንዱ እና የዝሆን ጥርሱ ለአሜሪካ እና ደቡብ ምሥራቅ እስያ ላሉ ገዥዎች ለመሸጥ ያሰበ እንደነበርም ተዘግቧል።
ከሦስት ወራት በፊትም የአሜሪካ እና የኬንያ ባለሥልጣናት ተከሳሹን አህመድ በቁጥጥር ስር ለማዋል የሚያስችል መረጃ ለማግኘት ያሰበ ጥሪ ለኬንያውያን አቅርበው ነበር።
አሜሪካ አህመድን እና በሌላ በሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር የተጠረጠረ በድሩ አብዱል አዚዝ ሳሌህ የተሰኘ ግለሰብን ጨምሮ እያንዳንዳቸውን ለመያዝ የሚረዳ መረጃ ላለው ሰው አንድ ሚሊየን ዶላር ሽልማት እንደምትሰጥ ቃል ገብታ ነበር።
ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር የተጠረጠረው ሳሌህ ከሳምንት በኋላ በቁጥጥር ስር ውሎ ነበር።
ይህ የአውራሪስ ቀንድ ለማግኘት የሚደረጉት አደኖች የእንስሳቱን ቁጥር ለመመናመን ምክንያት እንደሆነ ይታመናል።
ቀንዱ የቻይና ባሕላዊ መድኃኒትን ለማዘጋጀት ይጠቅማል ተብሎ መታሰቡ አደኑን ለመከላከል የሚደረጉ የመንግሥት ሙከራዎችን አስቸጋሪ ሆነው እንዲቀጥሉ አድርጓል።
እንዲሁም የዝሆን ጥርስ የመደብ እና የሃብት መገለጫ ሆኖ እስካሁን ድረስ መወሰዱ አደኑ ተጠናክሮ ለመቀጠሉ ምክንያት ነው።
ባለፈው ዓመት የተደረገ አንድ ጥናት እንደሚያሳየው በሞዛምቢክ የዝሆን ጥርስን ለማግኘት በሚደረጉ ተግባራት ምክንያት ጥርስ አልባ ዝሆኖች እንዲበራከቱ ምክንያት ሆኗል ብሏል።












