የአዳዲስ ክልሎች መመሥረት ጥቅም እና አሉታዊ ውጤት

ከደቡብ ብሔረሰቦች አባላት መካከል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

አሁን የከሰመው ኢሕአዴግ በ1983 ሥልጣን ከያዘ በኋላ የኢትዮጵያን የአስተዳደር ሥርዓት ከአሃዳዊ ወደ ፌዴራል ቀየረው።

ኢሕአዴግ ይህን የፖለቲካ ሥርዓት የመረጠው ሁሉም የአገሪቱ ዜጎች በተለይ ደግሞ ተረስተዋል የሚባሉ ብሔሮች ተሰሚነት እንዲኖራቸው በማሰብ እንደሆነ የፓርቲው መሪዎች ሲናገሩ ተደምጠዋል።

ኢሕአዴግ ባዋቀረው አዲስ የፌደራሊዝም ሥርዓት ውስጥ የነበሩ አምስት ክልሎች ተዋህደው የደቡብ ኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች የተባለው ክልል ተመሠረተ።

ይህ ግን ሁሉንም ያስደሰተ አልነበረም በዚህም በክልሉ ውስጥ ያሉ የተለያዩ ማኅበረሰቦች የራሳቸውን ክልል ለመመስረት ሲጠይቁ ቆይተዋል።

በተለይ የሲዳማ ዞን ጥያቄ ለዓመታት የቆየ ሲሆን፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አስተዳደር ወደ ሥልጣን ከመጣ ወዲህ ከደቡብ ክልል የወጡ ሁለት አዳዲስ ክልሎች ተዋቅረዋል።

ከብዙ ውጥረትና የሰው ሕይወት ከቀጠፈ ግጭት በኋላ ሲዳማ ከደቡብ ክልል ተለይቶ ራሱን በራሱ ማስተዳደር ጀምሯል።

በተጨማሪ ምዕራብ ኦሞ፣ ቤንች ሸኮ፣ ከፋ፣ ዳውሮና ሸካ አንድ ላይ ተዋቅረው አስራ አንደኛው ክልል ከተመሠረተ ወራት ተቆጥረዋል።

ቢሆንም ከደቡብ ክልል ዞኖች አሁንም ክልል መሆን ይገባናል የሚል ጥያቄ መነሳቱ ቀጥሏል።

ክልል የመመሥረት ጥያቄን አጥብቀው ከሚያነሱ የደቡብ ክልል አካባቢዎች መካከል የወላይታ ዞን የሚነሳ ሲሆን ይህን ተከትሎ በተፈጠረ ግርግር በዞኑ ከፍተኛ ውጥረት እንደነበር አይነዘጋም።

ኢትዮጵያ የምትከተለውን የፌዴራሊዝም ሥርዓት አጥብቀው የሚደግፉና ብቸኛው አማራጭ ነው የሚሉ እንዳሉ ሁሉ፤ አሁን አገሪቱ ላለችበት ቀውስ ተጠያቂ ነው ብለው የሚሞግቱም በርካቶች ናቸው።

ለመሆኑ ክልል የመሆን ጥያቄን የሚያነሱ ዞኖች የሚያቀርቡት አመክንዮ ምንድነው? አዳዲስ ክልሎች መመሥረታቸው አደጋ ነው የሚሉስ መከራከሪያቸው ምን ይሆን?

የኢትዮጵያ ፌዴራሊዝም

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ኢሕአዴግ ወደ ሥልጣን መጥቶ ያዋቀረው ፌደራላዊ ሥርዓት እና ተከትሎም ተግባራዊ የሆነው የአገሪቱ ሕገ-መንግሥት በኢትዮጵያ ያሉ ብሔሮች ራሳቸውን ማስተዳደር፣ አልፎም የመገንጠል መብትን ይሰጣል።

ኢትዮጵያ የፌዴራሊዝም ሥርዓትን በመከተል ከአፍሪካ ሁለተኛዋ አገር ናት ይላሉ በደቡብ አፍሪካ የኬፕ ታውን ዩኒቨርሲቲ የሕግ ፕሮፌሰሩ ዮናታን ተስፋዬ ፍሰሃ።

ናይጄሪያ እና ኢትዮጵያ በግልፅ ፌዴራሊዝምን እንከተላለን የሚሉ የአፍሪካ አገራት ቢሆኑም ሌሎችም አገራት ይህን ሥርዓት እንደሚተገብሩ ይጠቅሳሉ።

ምሁሩ፤ ፌዴራሊዝም ሁለት መንግሥታት ማለትም የፌዴራል እና የክልል መንግሥት በጋራ አገር የሚያስተዳድሩበት ሥርዓት ነው ይላሉ።

“የኢትዮጵያ ፌዴራሊዝም ዋና መለያው የብሔር አወቃቀሩ ነው። የብሔር ማንነት በከፍተኛ ደረጃ እውቅና ተሰጥቶት፤ ለክልሎች አመሠራረትም መሠረት ሆኖ የምናየው ነው። ይህን በሌሎች ፌዴራሊዝምን በሚከተሉ አገራት ውስጥ ላናየው እንችላለን።”

ሌላኛው መለያው ‘የራስን ዕድል በራስ መወሰን እስከ መገንጠል’ የሚለው የሕገ-መንግሥት አንቀፅ እንደሆነም ያስረዳሉ።

ሌሎች አገራት ‘የራስን ዕድል በራስ መወሰን’ የሚለውን አማራጭ ቢሰጡም፣ መገንጠል የሚለውን ሐሳብ ሲያንፀባርቁ አይስተዋልም ይላሉ።

ኢትዮጵያ የምትከተለውን የፌዴራሊዝም ሥርዓት የማይደግፉ ወገኖች ‘ሥርዓቱ አሁን ላለንበት የፖለቲካ ቀውስ ተጠያቂ ነው’ ሲሉ ይደመጣሉ።

በሌላ በኩል ለኢትዮጵያ የሚበጃት ይህ ሥርዓት ነው የሚሉ ‘ፌዴራሊዝም በርካታ ብሔሮች ለሚኖሩበት አገር የሚበጅ ነው’ ባይ ናቸው።

የሕግ ፕሮፌሰሩ ሁለቱም ሐሳቦች ውሃ ያነሳሉ ይላሉ።

“ሕገ-መንግሥቱ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ባለመሆኑ የፖለቲካ ነፃነት አለ ማለት ባንችልም በፌዴራሊዝሙ ምክንያት ብሔር ብሔረሰቦች የራሳችን ለሚሉት ሰው ድምፅ መስጠት ችለዋል። ብሔሮች የራሳቸውን ዕድል በራሳቸው መወሰን፤ መሪዎቻቸውን የመምረጥ፣ በራሳቸው ቋንቋ መተዳደር እንዲችሉ አድርጓል።”

ዮናታን እንደሚሉት በርካታ ቋንቋዎች ሥራ ላይ መዋል የቻሉት አልፎም በትምህርት ቤት እንዲሰጡ የሆኑት ፌዴራሊዝሙ በሰጠው ዕድል ምክንያት ነው።

በሌላ በኩል ፌዴራሊዝምን የሚወቅሰው ሐሳብም ሥርዓቱ በብሔር መዋቀሩ የፈጠረው ነው ይላሉ።

“ብሔር ላይ የተመረኮዘ ክልል አሊያም ዞን ሲፈጠር ባለቤትና መጤ አሊያም እንግዳ የሚል ስሜት ይወልዳል። በአንዳንድ ክልሎች እንዲያውም በግልፅ በሕገ-መንግሥታቸው የተቀመጠ ነው።”

ተንታኙ አክለውም በዚህ ምክንያት ሰዎች “ይህ የእኛ ክልል ነው። እናንተ መጤ ናችሁ እና መብት ሊኖራችሁ አይገባም፤ ከኖራችሁም በእኛ ይሁንታ ነው የሚል ስሜት እንዲያዳብሩ አድርጓል” ይላሉ።

ኢትዮጵያ ውስጥ የብሔር መከፋፈል ከ83’ በፊት የነበረ ቢሆንም፣ የፌዴራሊዝም ሥርዓቱ የበለጠ አባብሶታል ይላሉ።

የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት

ፌዴራሊዝም ሥርዓቱን የሚተቹ

የኢትዮጵያ ሕገ-መንግሥት ኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች በፈቃደኝነት የመሠረቷት አገር ናት ሲል ይገልጣል።

ሕገ-መንግሥቱ ሕዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው ከማስተዳደር አልፎ እስከ መገንጠል ድረስ መብት አላቸው ይላል።

ፌዴራሊዝም ሥርዓት የሚከተለውን ሕገ-መንግሥት አጥብቀው ከሚተቹ ቡድኖች መካከል አንዱ በአሜሪካ የአማራ ማኅበር ነው።

የማኅበሩ አድቮኬሲ ዳይሬክተር ሆነ ማንደፍሮ ደቡብ ክልል ከመከፋፈሉ በፊት ከሌሎች ክልሎች ጋር የሚገዳደር ፖለቲካዊ አቅም ነበረው ይላሉ።

ዳይሬክተሩ “ያልጎለበቱ ክልሎች እየተፈጠሩ ሲሄዱ ችግር ይፈጠራል” ሲሉ ስጋታቸውን ለቢቢሲ ይናራሉ።

“ወደፊት አገሪቱ በአማራ እና በኦሮሞ መካከል የሚታይ ትልቅ ፖለቲካዊ ፉክክር ይገጥማታል፤ ሌሎች ደግሞ አንዱ ከአንዱ ጋር ወዳጅነት መመሥረት [አላያንስ] ይጀምራሉ።”

በሌላ በኩል ይላሉ አቶ ሆነ፣ አሁን እንደ አዲስ የሚቋቋሙት ክልሎች “በውስጣቸው ለሚገኙ አናሳ ብሔሮች [የሌሎች ክልሎች ተወላጆች] እውቅና ካልሰጡ ለበለጠ የሰብዓዊ መብት ጥሰትና መድልዎ ሊያጋልጥ ይችላል።”

በዚህም ክልሎቹ የነባር ማኅበረሰቦች የብቻ ይዞታዎች [ኤክስክሉሲቭ ሆምላንድ] እየሆኑ ስለሚመጡ ሌሎች እንዲገለሉና ለአደጋ እንዲጋለጡ ያደርጋል ይላሉ።

“አገሪቱ አንድ ናት ብለን የምናስብ ከሆነ እና ክልሎች ደግሞ አስተዳደራዊ ወሰን ናቸው የምንል ከሆነ ከፍትሃዊ የምጣኔ ሃብት ሥርጭት አንፃር ምን ዓይነት አከላለል ብንከተል ይሻላል የሚለው ወሳኝ ጥያቄ ነው።”

አቶ ሆነ እንደሚሉት “ክልልሎች የተራራቀ የሕዝብ ቁጥር እና መልክዐ-ምድር [ጂኦግራፊ] እንዳይኖራቸው በማድረግ ይህን ጥያቄ መመለስ ይቻላል። ነገር ግን ይህንን ለማድረግ አገሪቱ አንድ ናት የሚል አስተሳሰብ ማስረጽ ያስፈልጋል” ይላሉ።

ክልል መሆን ጥቅሙ ምንድነው?

ክልል መሆን ይገባናል ጥያቄን በተደጋጋሚ ከሚያነሱ ብሔሮች መካከል ወላይታ ይጠቀሳል።

የወላይታ ብሔር ተወላጅ የሆኑትና ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉት ምሁር ይህን ጥያቄ ከግብ ለማድረስ የፖለቲካ ፓርቲ ካቋቋሙ ሰዎች መካከል የሆኑት ግለሰብ “ወላይታን በክልል የማደራጀት ጥያቄ ፍትሃዊ ነው” ሲሉ ለቢቢሲ ይናገራሉ።

"ወላይታ በታሪክ በራሱ ሲተዳደርበት የነበረው ሥርወ-መንግሥት [ዳይናስቲ] ከወደቀ በኋላ ለበርካታ ዘመናት እንደ አናሳ ብሔር ተቆጥሮ እኩልነትና የአገር የጋራ ባለቤትነት ተነፍጎ ነበር።”

በዚህም በሌሎችም ምክንያቶች እንዲሁም በደቡብ ክልል ውስጥ ከተካተተ በኋላ ያጋጠሙ ግጭቶች፣ የፍትሐዊ ተጠቃሚነት ጥያቄ እና አጋጠሙ ባሏቸው ችግሮች ሳቢያ የክልል እንሁን ጥያቄ መጠናከሩን ያወሳሉ።

በአሁኑ ወቅት “አብላጫ ድምፅ ያላቸው ሕዝቦች የበላይነት ሥርዓት ተፈጥሯል” የሚሉት እኚህ የወላይታ ፖለቲከኛ፣ ዋናው ጥያቄ “እንደ ብሔር ፍትሐዊና በእኩልነት ላይ የተመሠረተ ልማት፣ ፖለቲካዊ ተሳትፎና የምጣኔ ሃብት ተጠቃሚነት ማጣት ነው” ይላሉ።

“በምጣኔ ሃብት፣ ፖለቲካና ደኅንነት ጥቅሙን ማስከበር የማይቻልበት ደረጃ ላይ ስለተደረሰ ይህን ለመቀልበስ መጀመሪያ ማድረግ ያለብን ራስን በራስ ማስተዳደርና በፌዴራል መንግሥት ቀጥተኛ የሆነ ተሳትፎ ማግኘት ነው። ይህ ደግሞ በክልል ስንደራጅ ይገኛል።”

ወላይታ ክልል በመሆኑ ምን ጥቅም ያገኛል የሚል ጥያቄ ከዚህ በፊት ቀርቦላቸው እንደነበር አስታውሰው “ሌላው ብሔር ለዘመናት ክልል ሆኖ ሲተዳደር ተጎድቻለሁ፤ ይህ አደራጀጀት አልሆነኝም፤ ይቅርብኝ ባላለበት ሁኔታ ወላይታ ምን ይጠቀማል የሚለው ጥያቄ ስሜት አይሰጥም።”

ከደቡብ ብሔረሰቦች አባላት መካከል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የደቡብ ክልል እንደ ማሳያ

አቶ ደያሞ ዳሌ የፖለቲካ ሳይንስና የዓለም አቀፍ ግንኙነት ምሁር ናቸው። በደቡብ ክልል የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ ሆነው አገልግለዋል። አሁን በክልሉ በአንድ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ውስጥ ይሠራሉ።

ሲዳማ ክልል ከሆነ በኋላ በተቀወረው የደቡብ ክልል ውስጥ ያሉ ዞኖች ተመሳሳይ ዕድል እንዲሰጣቸው ሲጠይቁ እንደቆዩ በማስታወስ፣ ከገዥው ፓርቲ የተሰጣቸው ምላሽ ግን “በክላስተር ተደራጁ” የሚል ነው ይላሉ።

“በዚህ መሠረት የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች በሚል የተወሰኑ ዞኖች ተስማምተው ክልል ተመሠረተ። የተቀሩት ይህን ሐሳብ ተቃወሙ።”

አቶ ደያሞ አንዳንዶች በብሔራቸው መሠረት ክልል እንሁን ሲሉ ጥያቄ እንዳቀረቡ ይናገራሉ። የተወሰኑ ዞኖች ደግሞ በውስጣቸው የተለያየ ብሔር ይዘው ክልል እንሁን ሲሉም ጠይቀዋል ይላሉ።

“አሁን የቀሩት ጉራጌ እና ደራሼ ናቸው። ጉራጌ ዞን ያሉ የብልጽግና ፓርቲ አባላት ገና አልተስማሙም። ካልተስማሙ ፓርቲውን ለቀው እንደሚወጡ እገምታለሁ። ነገር ግን የፓርቲ ተሿሚዎች እምቢ ይላሉ ብዬ አላምንም።”

ክልል ከተመሠረተ በኋላም አለመስማማት የሚፈጥሩ ሌሎች ጉዳዮች እንዳሉ በመጥቀስ፣ አዲስ የተቋቋመውን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልልን በዋቢነት ያነሳሉ።

“የክልሉ መሥሪያ ቤቶች በተለያዩ ከተሞች ይሁኑ የሚል ሐሳብ አለ። በዚህ ጉዳይ ላይ ከስምምነት ስላልተደረሰ ለጊዜው ቦንጋ ማዕከል ሆኗል። በዚህ ይጽና የሚል ወገን አለ። ይህን የሚቃወሙም አሉ” በማለት ክልሎች የማዋቀሩ ሂደት የተወሳሰቡ ጉዳዮችን የያዘ ነው ይላሉ።

አሁን በተጀመረው መልሶ የማዋቀር ሂደት የተቀሩት የደቡብ ክልል ዞኖች ስምምነት ላይ ደርሰው አዲስ ክልሎች የሚመሠረቱ ከሆነ የደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰብ እና ሕዝብ ህልውና ያከትማል።

አቶ ደያሞ የደቡብ ክልል በአዲስ ሲዋቀር የተለያዩ ብሔሮች ከትልቁ የደቡብ ክልል ወደ ትናንሽ ክልሎች ነው የሚካተቱት፣ ይህም አስካሁን ያለውን ችግር ከመሠረቱ የሚፈታው አይደለም ይላሉ።

“እንደ ሲዳማ ተመሳሳይ ቋንቋ ለሚናገሩ ብሔሮች መፍትሔ ሊሆን ይችላል። ሌሎች ዞኖች ግን አሁንም ቀድሞ እንደተደረገው በጋር እንዲደራጁ ነው የሆኑት። በእኔ ዕይታ ይህ ለውጥ አያመጣም። የነበረውን አለመግባባት ወደ ትናንሽ አለመግባባት ይቀይረዋል እንጂ።”

ዋናው ጉዳይ መሆን ያለበት አዳዲስ ክልሎች ሲቋቋሙ ሕዝቡ የበጀት ተጠቃሚ እንዲሆን ማድረግ እንዲሁም መልካም አስተዳደር እንዲሰፍን መሥራት ነው ሲሉ ያስረዳሉ አቶ ደያሞ።

ለኢትዮጵያ ምን አይነት ፌደራሊዝም

ለመሆኑ የዘርፉ ባለሙያዎች ለኢትዮጵያ የሚበጀው ሥርዓተ-መንግሥት የትኛው ነው ይላሉ? ከፌዴራሊዝም አሊያም ከአሃዳዊው ውጪ ለኢትዮጵያ የሚበጅ ሥርዓተ-መንግሥት ይኖር ይሆን?

ፖለቲከኞችና የፖለቲካ ሳይንስ ምሑራን ፌዴራሊዝምን ብንከተል እንኳ ብሔር ተኮር መሆን የለበትም ይላሉ።

የሕግ ፕሮፌሰሩ ዮናታን ተስፋዬ ፍሰሃም በዚህ ይስማማሉ።

“የፌዴራሊዝም ሥርዓተ-መንግሥት ለኢትዮጵያ አማራጭ የሌለው ሥርዓት እንደሆነ ግልጽ ነው። ጥያቄው የትኛው ዓይነት የፌዴራሊዝም ሥርዓት ይሁን የሚለው ነው።”

ምሑሩ እንደሚሉት ክርክሩ ያለው ብሔር ተኮር ፌዴራሊዝም ይሁን ወይስ መልክዐ ምድራዊ ይሁን የሚለው ላይ ነው።

መልክዐ ምድራዊ ማለት ለአስተዳደር እንዲመች ተደርጎ ይዋቀር እንደማለት ነው ሲሉ ያስረዳሉ።

“ምንም ዓይነት የፌዴራሊዝም ሥርዓት ይሁን የብሔር ጥያቄዎችን የሚመልስ መሆን አለበት ብዬ አስባለሁ። ይህን ጥያቄ የማይመልስ ሥርዓት ኢትዮጵያ ውስጥ ተቀባይነት አይኖረውም። የፌዴራሊዝም ሥርዓቱን አሁን ካለው በተለየ መልኩ በማዋቀር ይህን ጥያቄ መመለስ ይቻላል።”

አክለውም “የምንከተለው የፌዴራሊዝም ሥርዓት አሁን እንዳለው የብሔር ማንነት ላይ ብቻ ያተኮረ መሆን የለብትም” ይላሉ።

ከፖለቲከኞች እንዲሁም ከማኅበረሰብ አንቂዎች የሚሰማው ሌላኛው ሐሳብ “አሁን እየተከተልን ያለነው ሥርዓት ለኢትዮጵያ ሕልውና አስጊ ነው” የሚል ነው።

ዮናታን “እንዲህ ብሎ ለመደመደም መጀመሪያ ሕገ-መንግሥቱ በትክክል ተግባር ላይ መዋል አለበት” ይላሉ።

“ባለፉት 30 ዓመታት ምንም እንኳ በፌዴራል ሕገ-መንግሥት ብንመራም ሥርዓቱን በደንብ ከተመለከትነው እንደ አሃዳዊ ሥርዓት ነበር የሚንቀሳቀሰው። ክልሎች መብታቸውን ተጠቅመው የራሳቸውን ዕድል በራሳቸው የሚወስኑበት ሁኔታ ላይ አይደለም ያሉት።”

ሥርዓቱ በትክክል ሳይተገበር የፌዴራሊዝም ሥርዓት ለኢትዮጵያ ሕልውና አስጊ ነው ማለት በመረጃ የተደገፈ አይሆንም ሲሉ ዮናታን ሐሳባቸውን ያስረግጣሉ።

“ነገር ግን ስጋቶች አሉ። ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው የብሔር ማንነት የፖለቲካው ቁልፍ መሆኑ በኅብረተሰቡ መካከል ውጥረት ፈጥሯል። ዜጎች በነፃነት መንቀሳቀስ አለመቻላቸው፤ ያላቸው መብት ከብሔር ማንነት ጋር የተያያዘ መሆኑ. . . የፈጠረው ስጋት አለ። ይህን መሠረት አድርገን የፌዴራል ሥርዓቱ ለሕዝቦች በሰላም መኖር ስጋት ሆኗል ማለት እንችላለን።”