የቀድሞውን ፕሬዝዳንት የእስር ጊዜ ለመቀነስ በተደረገ ጥረት በብራዚል ምክር ቤት ግብግብ ተነሳ

በምክር ቤት ውስጥ የተነሳው ግብግብ

የፎቶው ባለመብት, EPA

የብራዚል ወግ አጥባቂ የሕዝብ እንደራሴዎች የቀድሞው ፕሬዝዳንት ዣሂር ቦልሶናሮን የእስር ጊዜ የሚቀንስ ሕግ ለማጽደግ ጫና ሲያደርጉ በምክር ቤት ውስጥ ግብግብ ተነሳ።

የፀጥታ ኃይሎች ምክር ቤቱን ለማረጋጋት ሲሞክሩ ግብግቡ የተነሳ ሲሆን፤ አንድ ግራ ዘመም ሕግ አውጪ ከምክር ቤቱ በፖሊስ ታጅበው እንዲወጡ ተደርጓል።

ቦልሶናሮ እአአ በ2022 የተደረገውን ምርጫ ተከትሎ መፈንቅለ መንግሥት አሲረዋል በሚል ክስ የ27 ዓመት እስር ተፈርዶባቸዋል።

የቀድሞው ፕሬዝዳንት ከያዝነው ወር ጀምሮ የተፈረደባቸውን የእስር ጊዜ ጀምረዋል።

የቦልሶናሮ ወግ አጥባቂ ደጋፊዎች ከመፈንቅለ መንግሥት ጋር በተያያዘ የሚቀርቡ ክሶች የሚያስከትሉትን የእስር ጊዜ የሚቀንስ ሕግ ለምክር ቤት አቅርበዋል።

ሕግ አውጪዎቹ፤ ቦልሶናሮ ከሥልጣን ሲወርዱ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችን ጥሰው የገቡ ደጋፊዎቻቸው ነጻ የሚወጡበትን መንገድ ለማግኘትም እየሞከሩ ነው።

የቦልሶናሮ ጠበቆች እንዳሉት የቀድሞው ፕሬዝዳንት ቀዶ ሕክምና ለማድረግ ከእስር ቤት እንዲወጡ የቀረበው ጥያቄ አወንታዊ ምላሽ አላገኘም።

ቦልሶናሮ የጤና እክል ስለገጠማቸው የተፈረደባቸውን የእስራት ጊዜ በቁም እስር እንዲያሳልፉ ጠበቆቹ ጠይቀዋል።

እአአ በ2018 በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ሆዳቸውን በስለት የተወጉት ቦልሶናሮ የአንጀት ቀዶ ሕክምና ተደርጎላቸዋል።

ከሦስት ዓመት በፊት በተደረገው ምርጫ ሉዊዝ ኢናሲዮ ሉላ ዳ ሲልቫ በጠባብ የድምጽ ልዩነት ቦልሶናሮን አሸንፈዋል። የቦልሶናሮ ጉዳይ ብራዚላውያንን የከፋፈለ ነው።

የቦልሶናሮ ደጋፊዎች፤ በሕዝብ የተመረጡ ፖለቲከኞች በወንጀል ክስ ምክንያት የሚጣልባቸውን የቅጣት ጊዜ ለማሳጠር የሚውል ረቂቅ ሕግ አቅርበዋል።

ከሕግ አውጪዎቹ አንደኛው ለኤኤፍፒ የዜና ወኪል እንደገለጹት፤ ሕጉ ከፀደቀ ቦልሶናሮ ለሁለት ዓመት ከአራት ወር ብቻ ይታሰራሉ።

በምክር ቤት የተነሳውን ውዝግብ ተከትሎ ግራ ዘመሙ ፖለቲከኛ ጋሉበር ብራጋ ለተወሰነ ጊዜ የአፈ ጉባዔውን ማይክራፎን ቀምተዋል።

በምክር ቤት ውስጥ የተነሳው ግብግብ

የፎቶው ባለመብት, EPA

ፖለቲከኛው ማይክራፎኑን ከመቀማታቸው በፊት በምክር ቤት ባስነሱት ሁከት ምክንያት እንዲታገዱ ለመወሰን ድምጽ ሊሰጥ ነበር።

ፖሊስ ፖለቲከኛውን በኃይል ከምክር ቤቱ ካስወጣ በኋላ በቀጥታ ቴሌቭዥን እየተላለፈ የነበረው ሥርጭት ተቋርጧል።

የቀጥታ ሥርጭቱ መቋረጡ መረጃን ሳንሱር ማድረግ ነው ብለው ጋዜጠኞች ተቃውመዋል።

የሕዝብ እንደራሴዎችዎን ግብግብ ውስጥ የከተተው ረቂቅ ሕግ እስካሁን ድረስ አልፀደቀም።

ቦልሶናሮ መፈንቅለ መንግሥት ለማድረግ ከመሞከር በተጨማሪ ሉላ ደ ሲልቫን ለማስገደል አሲረዋል በሚል ነበር የተፈረደባቸው።

የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራው ቢከሽፍም ደጋፊዎቻቸው የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችን ጥሰው በመግባት ውድመት አድርሰዋል። ሁከቱን ተከትሎ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ታስረዋል።

ሁለት የቀድሞ የመከላከያ ሚኒስቴር አመራሮችን ጨምሮ ከፍተኛ ወታደራዊ መሪዎችም የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ በማድረግ ተከስሰዋል።

የቦልሶናሮ ደጋፊዎች ክሱን አጣጥለዋል። ሊበራል ፓርቲያቸው በምክር ቤት አብላጫውን መቀመጫ የያዘ ሲሆን፤ የሉላ ደ ሲልቫ ደጋፊዎችን በቁጥር ይበልጣሉ።