የጣልያን ፖሊስ የማፊያ መሪውን መደበቂያ ከቁም ሳጥን ጀርባ አገኘ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በጣልያን ፖሊስ በጥብቅ ይፈለግ የነበረው የማፊያ መሪ ማቴዎ ሜሲና ዴናሮ ይደበቅባቸው ከነበሩ ቦታዎች ሁለተኛው ተገኘ።
ከቁም ሳጥን ጀርባ ያለና ከሥሩ ተንሸራታች መደበቂያ ያለው ቦታ ነው ፖሊስ ያገኘው።
በመሣሪያ የተከበበው ይህ መደበቂያ የተገኘው የማፊያ ቡድን መሪው በሲሲሊ፣ ካምፖቤሎ ዲ ማዛራ ካዘጋጀው የመጀመሪያ መደበቂያው በ300 ሜትር ርቀት በሚገኝ ቤት ውስጥ ነው።
ፖሊስ ናቴዎ ሜሲና ዴናሮን ለ30 ዓመታት ሲያሳድደው ቆይቶ ከቀናት በፊት በሲሲሊ በሚገኝ ፓሌርሞ ሆስፒታል በቁጥጥር ሥር አውሎታል።
የማፊያ ቡድን መሪው የካንሰር ሕክምና እየተከታተለ ነበር። ለሆስፒታሉ ያስመዘገበውም ሐሰተኛ ስም ነበር።
አንድሪያ ቦናፌድ የተባለ ሐሰተኛ ስም አስመዝግቦ ሲታከም ፖሊስ ጥርጣሬ አድሮበታል።
ይህ ስም የሟች የማፊያ ቡድን መሪ ሊዮናርዶ ቦናፌድ የአጎት ልጅ ስም ነው።
ፖሊስ የሊዮናርዶ ቦናፌድን የስልክ እንቅስቃሴ ሲከታተል ግለሰቡ እአአ ከ2020 እስከ 2021 በፓሌርሞ እንዳልነበረ ተገነዘበ።
በሱ ስም ሕክምና እያደረገ ያለው ማነው? የሚል ጥያቄም አጭሯል።
ከዚያም በተደረገው ምርመራ በጥብቅ ሲፈለግ የነበረው የማፊያ ቡድን መሪ ተይዟል።

ኮሳ ኖስትራ የተባለው የወንጀል ቡድን ከፍተኛ አመራር ሳለ ሕገ ወጥ ልውውጥ፣ ሕገ ወጥ ገንዘብን ሕጋዊ መስመር ማስገባት እና ዕፅ ዝውውርን ጨምሮ በሌሎችም ወንጀሎች ተሳትፏል።
እአአ በ2002 ግለሰቡ በሌለበት በብዙ ግድያዎች ፍርድ አስተላልፎበታል።
ከመታሰሩ በፊት ከፓሌርሞ በ116 ኪሎ ሜትር ርቀት በሚገኝ ስውር ቤት ሲኖር ነበር። ከጎረቤቶቹ ጋርም ሰላምታ ይለዋወጥ እንደነበር የአካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል።
ፖሊስ ባገኘው የመጀመሪያ መደበቂያው ምንም መሣሪያ ባይገኝም ውድ ሽቶዎች፣ ቅንጡ ልብሶችና የቤት ውስጥ መገልገያዎች ተገኝተዋል።












