የኢኳቶሪያል ጊኒ ፕሬዝዳንት ልጅ የመንግሥት አውሮፕላን በመሸጥ ተጠርጥረው ታሰሩ

የፎቶው ባለመብት, AFP
የኢኳቶሪያል ጊኒ ፕሬዝዳንት ልጅ የሆኑት ሩልሳን ኦቢያንግ ኑሴ የመንግሥት አየር መንገድ ንብረት የሆነ አውሮፕላን ሸጠዋል ተብለው በመከሰሳቸው ታሰሩ።
እንዲታሰሩ ትዕዛዙን የሰጡት የአገሪቱ ምክትል ፕሬዝዳንት እንዲሁም የታሰሩት ግለሰብ ወንድም ናቸው።
የታሰሩት የምክትል ፕሬዝዳንቱ ወንድም እንዲሁም ምክትል ፕሬዝዳንቱም የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ቴዎዶሮ ንጉዌማ ኦቢያንግ ማንጉዬ ልጆች ናቸው።
የታሰሩት የፕሬዝዳንቱ ልጅ የቀድሞው የሴቢያ ዓለም አቀፍ አየር መንገድ ዳይሬክተር የነበሩ ሲሆን፣ ኤቲአር72-500 ያለ ተቋሙ ቦርድ ፈቃድ ለስፔን ድርጅት በመሸጥ ነው የተከሰሱት።
ከሽያጩ የተገኘውን ገንዘብ ወደ ግል ኪሳቸው ማስገባታቸውም ተገልጿል። የፕሬዝዳንቱ ልጅ እስካሁን ስለ ክሱ በይፋ የተናገሩት የለም።
ፕሬዝዳንት ቴዎዶሮ ንጉዌማ ኦቢያንግ ማንጉዬ ለ43 ዓመት ኢኳቶሪያል ጊኒን መርተዋል። ረዥም ዓመታት አገር በመግዛትም በዓለም ግንባር ቀደም ናቸው።
የአገሪቱ ምክትል ፕሬዝዳንት የእንጀራ ወንድማቸው በቁም እስር እንዲቆዩ ከዚያም እንዲታሰሩ ማዘዛቸው ተገልጿል።
የአገሪቱ ፕሬዝዳንት “የመንግሥት ይዞታ ከሆነው ኃላፊነት እንዲያነሳቸው” መጠየቃቸውም ተገልጿል።
አምና አንድ አውሮፕላን ስፔን ውስጥ ጥገና ላይ ሳለ ከጠፋ በኋላ ምርመራ እንዲደረግ ተወስኖ ነበር።
የአገሪቱ ፕሬዝዳንት አብዛኞቹን ቁልፍ ሥልጣኖች ለቤተሰቦቻቸው ሰጥተዋል።
እአአ በ1979 ከአጎታቸው ሥልጣን ከቀሙ በኋላ ብዙ መፈንቅለ መንግሥቶችን ተቋቁመዋል።
ያለፈውን ምርጫ 95% እንዳሸነፉ ቢናገሩም ምርጫው ነጻና ፍትሐዊ እንዳልነበረ ተተችቷል።
የፕሬዝዳንቱ ልጅ የሆኑት ምክትል ፕሬዝዳንቱ ከአባታቸው ሥልጣን እንደሚረከቡ ይጠበቃል።
“ቴዎዶሪን” በሚል ስም የሚታወቁት ምክትል ፕሬዝዳንቱ በአሜሪካና አውሮፓ ቅንጡ ሕይወት አሳልፈዋል። የማይክል ጃክሰን ጓንትን እንደገዙም በዩናይትድ ኪንግደም ባለሥልጣኖች ተገልጿል።
በ2014 ከሙስና ክስ ጋር በተያያዘ አሜሪካ ወደ 30 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ ማልቡ የሚገኝ ቅንጡ መኖሪያ እና ፌራሪ መኪናን ጨምሮ ሌሎችም ንብረቶቻቸውን በቁጥጥር አውላለች።
ይህ ከሆነ ከሁለት ዓመት በኋላ ደግሞ ስዊዘርላንድ 11 ቅንጡ መኪናዎችን በቁጥጥር አውላለች።
በ2021 የሕዝብን ንብረት ለግል ጥቅም በማዋል በፈረንሳይ ፍርድ ቤት ፍርድ ተላልፎባቸዋል። ምክትል ፕሬዝዳንቱ ግን ሁሉንም ክሶች ይክዳሉ።












