ዌልስ ለሴት የእግር ኳስ ብሔራዊ ቡድኗ ለመጀመሪያ ጊዜ ከወንዶች እኩል ልትከፍል ነው

ታዋቂዎቹ የዌልስ የሴት እና የወንድ ብሔራዊ ቡድን አባላት (ጄስ ፊሽሎክ፣ አሮን ራምሴይ፣ ሶፊ ኢንግል እና ብሬናን ጆንሰን)

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ታዋቂዎቹ የዌልስ የሴት እና የወንድ ብሔራዊ ቡድን አባላት (ጄስ ፊሽሎክ፣ አሮን ራምሴይ፣ ሶፊ ኢንግል እና ብሬናን ጆንሰን)

የዌልስ የወንድ እና የሴት ዋና ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች አገራቸውን ወክለው በሚጫወቱበት ጊዜ ለመጀመሪያ ጊዜ ተመሳሳይ ክፍያ ሊሰጣቸው ነው።

የዌልስ የእግር ኳስ ማኅበር በክፍያው ላይ ከስምምነት መድረሱን እና ለሁለቱም ጾታዎች የአገሪቱ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን አባላት ክፍያው ወዲያው ተግባራዊ እንዲሆን ወስኗል።

የሴቶቹ ተጫዋቾች ክፍያ ከወንዶቹ ዝቅ ያለ ስለነበር አሁን ተመሳሳይ እንዲሆን ሲወሰን፣ ክፍያውን ለማመጣጠን የወንዶቹ ቡድን አባላት ከሚያገኙት ላይ 25 በመቶው ተቀንሶ ለሴቶቹ እንዲከፈል ተስማምተው ውሳኔው ተግባራዊ እንዲሆን ተባብረዋል።

የዌልስ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ጌማ ግራይነር “በእኩል ክፍያው ውሳኔ በጣም ተደስቻለሁ፤ ይህም የእኩልነት ጉዳይ ነው” ስትል ተናግራለች።

የዌልስ እግር ኳስ ማኅበር ባወጣው መግለጫ ለእኩልነት እንደሚጥር ጠቅሶ “ከወንድ እና ከሴት ቡድኖቻችን ጋር በመሆን እኩል ክፍያ እንዲፈጸም ስንስማማ ኩራት ይሰማናል። ይህም በቀጣይ የእግር ኳስ ውድድሮች ተግባራዊ ይሆናል” ብሏል።

የዌልስ ሴት ብሔራዊ ቡድን አባላት በዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ ሲሳተፉ ከወንድ አቻዎቻቸው ጋር ተመሳሳይ ክፍያ አግኝተው አያውቅም።

“እኩልነት እና ሁላችንም እኩል መሆናችንን ማረጋገጥ በጣም ጠቃሚ ነው። የሴቶች እግር ኳስ እያደገ ሲሆን አሁንም ማደጋችንን እንቀጥላለን” ስትል የቡድኑ አሰልጣኝ ጌማ ግራይነር ተናግራለች።

በዚህ ውሳኔዋ ዌልስ ለዓለም አቀፍ የእግር ኳስ ውድድሮች ለወንዶች እና ለሴቶች ብሔራዊ ቡድኖቻቸው እኩል ከሚከፍሉት ከአሜሪካ፣ ከእንግሊዝ፣ ከብራዚል፣ ከአውስትራሊያ፣ ከኖርዌይ እና ከኒው ዚላንድ ጋር ለመቀላቀል በቅታለች።

የስኮትላንድ የሴቶች ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን በእኩል ክፍያ እና በአጠቃላይ ሁኔታዎች ላይ ከአገሪቱ የእግር ኳስ ማኅበር ጋር ሲያደርግ የነበረው ድርድር ሳይሳካ በመቅረቱ ማኅበሩን በሕግ ለመጠየቅ ክስ ከፍቷል።

ለዌልስ የሴት ብሔራዊ ቡድን አባላት አዲስ ክፍያ ላይ የተካሄደው ድርድር ከአንድ ዓመት በላይ ነበር የተካሄደው።

የዌልስ እግር ኳስ ማኅበር ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኖኤል ሙኒ ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥተው ከብሔራዊ ቡድኑ አባላት ጋር ለተከታታይ ጊዜያት ውይይት ሲያደርጉ መቆየታቸውም ተነግሯል።

የዌልስ ሴት የብሔራዊ ቡድን አባላት በዓለም አቀፍ ጨዋታዎች ከወንዶች እኩል ክፍያ እንዲያገኙ የተደረገው ጥረት የተሳካው፣ የወንዶቹ ቡድን ከራሳቸው ላይ ተቀንሶ ለሴቶች እንዲጨመር ሙሉ በሙሉ በመስማማታቸው ነው።