በዓለም ዋንጫ የፍጻሜ ጨዋታ ምክንያት የአርጀንቲና ቡድን በፊፋ ምርመራ ሊደረግበት ነው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የኳታሩ ዓለም ዋንጫ ሻምፒዮኗ የአርጀንቲና ተጫዋቾች በፍጻሜው ጨዋታ ላይ ባሳዩት “ያልተገባ ባህሪይና” እና “ስፖርታዊ ጨዋነትን በመጣስ” ምርመራ ሊደረግበት ነው።
የቡድኑ “ተጫዋቾች እና ኃላፊዎች ተገቢ ያልሆነ ጠባይ በማሳየት” ክስ የቀረበባቸው ሲሆን በዚህም የዲሲፕሊን ቅጣት እንደሚጠብቃቸው ፊፋ አስታውቋል።
በተጨማሪም የአርጀንቲና እግር ኳስ ማኅበርም በዓለም ዋንጫ ውድድር ወቅት የመገናኛ ብዙኃን እና የማስታወቂያ ደንቦችን በመጣስ ተከሷል።
የአርጀንቲና ብሔራዊ ቡድን በከባድ ፈተና ውስጥ አልፎ የፈረንሳይ ብሔራዊ ቡድንን በመለያ ምቶች በማሸነፍ ነው ከአውሮፓውያኑ 1986 ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ የዓለም ዋንጫን ያነሳው።
ፊፋ ባቀረበው ክስ ላይ በፍጻሜው ጨዋታ የትኞቹ የአርጀንቲና ቡድን አባላት ምን አይነት ገቢ ያልሆነ ድርጊት እንደፈጸሙ ወይም ባህሪይ እንዳሳዩ አልገለጸም።
በፍጻሜው ዕለት አርጀንቲናዊው የአስቶን ቪላ ግብ ጠባቂ ኤሚሊዮ ማርቲኔዝ ተገቢ ያልሆነ ምልክት ማሳየቱ እና በፈረንሳዩ ኮከብ ተጫዋች ኪሊያን ምባፔ ላይ መልበሻ ክፍል ውስጥ ሲሳለቅ ታይቷል።
ፊፋ በአርጀንቲና ብሔራዊ ቡድን ላይ ሦስት የሥነ ምግባር ደንቦችን የመተላለፍ ክስ መቀረቡን አመልክቷል። እነዚህም አንቀጽ 2 የስፖርታዊ ጨዋነትን መርኅ የሚጥስ ጎጂ ባህሪይ ማሳየትን የሚመለከተው፣ አንቀጽ 12 የተጫዋቾች እና የኃላፊዎች ያልተገባ ባህሪይ እና አንቀጽ 44 የማስታወቂያ ደንብን መተላለፍን የሚመለከቱ ናቸው ተብሏል።
በቀረቡት ክሶች ላይ ፊፋ አስፈላጊውን ምርመራ የሚያደርግ ሲሆን፣ በዚህ ወቅትም አርጀንቲና ለክሶቹ መልስ መስጠት ትችላለች።
በግማሽ ፍጻሜው በአርጀንቲና የተሸነፈችው የክሮሺያ ብሔራዊ ቡድን አባላትም የተለያዩ ጥሰቶችን በመፈጸም በፊፋ ምርመራ ተደርጎባቸዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በምድብ ጨዋታ ወቅት ሰርቢያ በስዊትዘርንድ 3 ለ 2 በተሸነፈችበት ጊዜ የሰርቢያ ደጋፊዎች እና የቡድኑ አባላት ባሳዩት ባህሪይ የተነሳ ሰርቢያ 44,000 ፓወንድ እና በቀጣይ የቡድኑ ጨዋታ ስታዲየሙ በከፊል ዝግ እንዲሆን ፊፋ ቅጣት አስተላልፏል።
በተመሳሳይም ሜክሲኮ እና ኤኳዶር በተጋጠሙበት ጊዜ ደጋፊዎች ባሳዩት ያልተገባ ባህሪይ የሜክሲኮ ቡድን የ88,000 ፓወንድ ቅጣት እና ቀጣይ ጨዋታ በዝግ ስታዲየም እንዲያደርግ ሲያዝ፤ ኤኳዶር ደግሞ 17,650 ፓወንድ እና ቀጣይ ጨዋታ በከፊል ዝግ በሆነ ስታዲየም እንዲካሄድ ወስኗል።












