ከዌልስ እስከ ሪያል ማድሪድ - የጋሬዝ ቤል አስደናቂ የእግር ኳስ ሕይወት

ጋሬዝ ቤል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በቢቢሲ ዌልስ የምስል ማከመቻ ክፍል ተገኝተው የቪድዮ ካሴት ቢያገላብጡ የ16 ዓመቱ ጋሬዝ ቤል ቤተሰቦቹን ተሰናብቶ ሲጓዝ ሊመለከቱ ይችላሉ።

ቤተሰቦቹ ከሚገኙበት የካርዲፍ ከተማ ወደ ሳውዝሃምፕተን የሥልጠና ማዕከል።

ጋሬዝ ቤል ዛሬ እንዲህ ፀጉሩ ረዝሙ ‘አምፖሎ’ መጎንጎን ከመጀመሩ በፊት ፊቱ ላይ ምስኪንነት የሚነበብበት ታዳጊ ነበር።

ቤል፤ ቤተሰቦቹን አቅፎ ከተሰናበተ በኋላ በመኪናው የኋላ ወንበር ተሳፍሮ ያደገበትን ከተማ ለቆ ሲወጣ ወደፊት ስሙ የሚገን ተጨዋች ይሆናል ብሎ የገመተ አልነበረም።

እነሆ ከ17 ዓመታት በኋላ የአምስት የአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ ሜዳሊያ ባለቤት እና የበርካታ የግል እና የቡድን ድሎችን ተጎናጽፏል።

ጋሬዝ ቤል ከ58 ዓመታት በኋላ አገሩን በአምበልነት እየመራ በዓለም ዋንጫ የተጫወተ የመጀመሪያው ዌልሳዊ ሆኗል።

የ33 ዓመቱ እግር ኳሰኛ የዌልስ ከፍተኛው ጎል አስቆጣሪ ነው፤ ከቶተንሃም እስከ ሪያል ማድሪድ አውሮፓ ውስጥ ኃያል ለሚባሉ ክለቦች ተጫውቷል።

እውን ቤል የዩናይትድ ኪንግደም የምንም ጊዜ ታላቁ ተጫዋች ነውን?

ጋሬዝ ቤል በ2006 (እአአ) ለሳውዝሃምፕተን የመጀመሪያውን ግብ ባስቆጠረበት ጊዜ

የፎቶው ባለመብት, Rex Features

የምስሉ መግለጫ, ጋሬዝ ቤል በ2006 (እአአ) ለሳውዝሃምፕተን የመጀመሪያውን ግብ ባስቆጠረበት ጊዜ

ታዳጊው ቤል

በፈረንጆቹ 2006/07 የውድድር ዘመን - በእንግሊዝ ቻምፒዮንሺፕ ደርቢ ካውንቲ ከሳውዝሃምፕተን ይፋለማሉ።

ደርቢ ካውንቲዎች ጨዋታው አንድ ለምንም እየመሩ ተደላድለው ሳለ አንድ ታዳጊ ከ22 ሜትር ግድም ቅጣት ምት ካልመታሁ ሲል ተነሳ።

ይህ ለ17 ዓመቱ የግራ እግር ተጫዋቹ ጋሬዝ ቤል ገና ሁለተኛ ፕሮፌሽናል የእግር ኳስ ጨዋታው ነበር።

ቤል ኳስን አጥመልምሎ ወደ መረቡ ላካት፤ የደርቢው በረኛ ሊ ካምፕ ተንጠራርቶ ሊያድናት ቢሞክርም እጅ አጠረው።

ከሦስት ቀናት በኋላ በተመሳሳይ ኮቨንትሪ ሲቲ የተሰኘው ክለብ ላይ ከቅጣት ምት ጎል አስቆጠረ።

ይሄኔ ነው የ17 ዓመቱ ታዳጊ የእግር ኳስ ደጋፊዎችን ቀል ይገዛ የጀመረው።

ቤል በዚህ ዕድሜው ለዌልስ መሰለፍ ጀምሮ ነበር። 17ኛ ዓመቱን ሊደፍት ሁለት ቀናት ሲቀሩት አገሩ ዌልስ ከትሪንዳድ ኤንድ ቶቤጎ ስትፋለም ለመጀመሪያ ጊዜ የአገሩን ማሊያ ለብሶ ተጫወተ።

እያጠማዘዘ ወደ መረብ የሚሰዳቸው ኳሶች ለበረኞች የጭንቀት መንስዔ ናቸው። በግራ እግሩ የሚተኩሳቸው ኳሶች ወደላይ ከፍ ብለው ቁልቁል ተምዘግዝገው ሲበሩ በረኛ ያታልላሉ።

ቤል በጥቅምት ወር 2006 ከቅጣት ምት ያገኛትን ኳስ ከመረብ በማገናኘት በዌልስ ታሪክ በዕድሜ ትንሹ ጎል አስቆጣሪ መሆን ቻለ።

ከ19 ዓመት በኋላ በፈረንጆቹ 2016 ቤል በቅጣት ምቱ ዌልስን በአውሮፓ ዋንጫ ወደ ግማሽ ፍፃሜ አሻገራት።

ጋሬዝ ቤል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ከስፐርስ እስከ ቻምፒዮንስ ሊግ

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ጊዜው በፈረንጆቹ 2012። ቤል፤ አሁን ዕድሜው 21 ደርሷል።

ክለቡ ቶተንሃም በቻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታ ከሚላን ይጫወታል። ውጤት፡ ቶተንሃም 0-4 ኢንተር ሚላን።

3 ቁጥር ማሊያ የለበሰው ቤል ከራሱ የግብ ክልል ኳሷን እየገፋ ወደ ኢንተር ቀጣና አቀና። ኳሷን በግራ እግሩ እያንከባለለ ዘለቀ። ጎል!

በመጀመሪያው የቤል ጎል የተደነቁ ሰዎች እጃቸውን ከአፋቸው ሳያነሱ ቤል ደገመው። በተመሳሳይ ስልት በግራ እግሩ የኢንተርን ተከላካይ መስመር ሰባብሮ ሁለተኛዋን ጎል አስቆጠረ።

ቤል በዚህ ጨዋታ ሃት-ትሪክ ቢሠራም ቶተንሃም 4 ለ 3 ተሸነፈ። ነገር ግን የቤል ጎሎች ባክነው አልቀሩም።

በመልሱ ጨዋታ ቤል የኢንተር ሚላኑን ተከላካይ ማይኮን ቁም ስቅል ሲያሳየው አምሽቶ፤ ሁለት ጎል አስቆጥሮ ስፐርስ 3 ለ 1 አሸነፈ።

ቤል በቶተንሃም የነበረው ቆይታ አልጋ በአልጋ አልነበረም። ብዙውን ጊዜ ጉዳት ያጋጥመዋል። ከጉዳት አገግሞ ሲጫወት ደግሞ ጎል ያጥረዋል።

እንደ ማንቸስተር ዩናይትድ ያሉ ክለቦች ዓይናቸውን ቢጥሉበትም በተደጋጋሚ የመጎዳቱ ነገር ሐሳባቸውን እንዲያጤኑ አደረጋቸው።

የወቅቱ የቶተንሃም አሰልጣኝ የነበሩት ሃሪ ሬድናፕ ከኢንተር ሚላን ጋር ለነበራቸው ጨዋታ ቤልን ላጫውተው አሊያስ ይቅርብኝ ሲሉ አመንትተው እንደነበር ከጨዋታ በኋላ አምነዋል።

ከዚህ ጨዋታ በኋላ ቤልን የሚቆጣጠረው ጠፋ። በግራ እግሩ እያቆራረጠ ወደ ጎል ቀርቦ ኳሷን በመለጋት እንዲሁም ከቅጣት ምት የሚያስቆጥራቸው ጎሎች መለያው ሆኑ።

በ2011 ቤል፤ የፕሮፌሽናል ተጫዋቾች የዓመቱ ምርጥ፣ የዓመት ምርጥ ታዳጊ፤ አልፎም የእግር ኳስ ፀሐፊዎች የዓመቱ ምርጥ ሆኖ ተመረጠ።

የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግን የነገሰበት ቤል ወደ አውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊያቀና ወደደ።

ቤል በ2014 (እአአ) ሪያል ማድሪድ እና አትሌቲኮ ማድሪድ ሲጫወጡ ግብ አስቆጥሮ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ቤል በ2014 (እአአ) ሪያል ማድሪድ እና አትሌቲኮ ማድሪድ ሲጫወጡ ግብ አስቆጥሮ

ወደ ጋላክቲኮ መንደር

በ2013 ከቶተንሃም ሪያል ማድሪድን የተቀላቀለው ቤል ያወጣው 85.3 ሚሊዮን ፓውንድ የዓለማችን ውድ ተጫዋች እንዲሆን አደረገው።

ቤል ለአገሩ እና ለክለቡ ድንቅ ድንቅ ጎሎች ማስቆጠር ልማዱ አደረገው።

የወዳጅነት ጨዋታ እንኳ ቢሆን ወደኋላ የሚል ሰው አይደለም። ዌልስ ከአይስላንድ ጋር ስትጫወት ያደረገውም ይህንኑ ነበር።

ከዌልስ የሜዳ አጋማሽ ኳሷን እየገፋ ሲገሰግስ የተመለከተው የአይስላንድ ተከላካይ ቤልን ከመስመር ውጪ እንዲወጣ ቢጎሽመውም አልተሳካለትም።

ቤል ወደ ሜዳ ተመልሶ ኳሷን እያንቀረቀበ በጨዋታው ለዌልስ ሦስተኛዋን ግብ አስቆጠረ።

ስለጋሬዝ ቤል ሲነሳ በርካቶች የማይረሷት አንድ ድንቅ ጎል አለች።

በስፔን ኮፓ ዴል ሬይ የፍፃሜ ጨዋታ፣ ሪያል ማድሪድ ከባርሴሎና ተፋጠዋል። ጨዋታው ሊጠናቀቅ አምስት ደቂቃዎች ቀርተውታል። ውጤቱ ደግሞ ባርሴሎና 1 - 1 ሪያል ማድሪድ።

ቤል በለተመደው ግስጋሴው በግራ እግሩ ኳሷን ከማድሪድ ሜዳ አሻግሮ ወደ ባርሴሎና የግብ ክልል ይገሰግስ ገባ።

የባርሴሎናው ተከላካይ ማርክ ባርትራ ቤልን ገፍቶ ከሜዳው ውጪ ቢያደርገውም ተመልሶ ገብቶ በሩጫ ቀድሞት ኳሷን እየገፋ ወደ ወደ በረኛው በማምራት ግብ አስቆጠረ።

በዚህች ጎል ምክንያት ቤል የመጀመሪያ ዋንጫውን ከሪያል ማድሪድ ጋር አነሳ።

ከአንድ ወር በኋላ በቻምፒዮንስ ሊግ ፍፃሜ ጎል አስቆጥሮ ሁለተኛ ዋንጫውን አንስቶ ሳመ።

ቤል ለቶተንሃም ሆትስፐርስ ሲጫወት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ቤል ለቶተንሃም ሆትስፐርስ ሲጫወት

በማድሪድ የተጠላ፤ በአገሩ የተወደደ

ቤል ከሪያል ማድሪድ ጋር ሦስት የላሊ ጋ ዋንጫ እና አምስት ቻምፒዮንስ ሊግ አንስቷል። ሌሎች አገራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ድሎችን ተቀዳጅቷል።

በመጀመሪያው የውድድር ዘመኑ 22 ጎሎችን፤ በሁለተኛው ደግሞ 18 ጎሎችን ከመረብ አሳርፏል።

ነገር ግን በጉዳት ምክንያት የወትሮው አቋሙን ማሳየት የተሳነው ቤል፣ ከማድሪድ ጋር ያለው ግንኙነት እየሻከረ መጣ። አልፎም የስፔን ጋዜጦች ጥርስ ውስጥ ገባ።

እንዲያም ሆኖ አንዳንድ ጊዜ የሚያስቆጥራቸው አስደናቂ ጎሎች የተጫዋቹን ኃያልነት የሚያሳዩ ናቸው።

ለምሳሌ በ2018 የቻምፒዮንስ ሊግ ፍፃሜ ሊቨርፑል ላይ ያስቆጠራት ‘የመቀስ ምት’ ግብ ልዩ ነበረች።

ነገር ግን ቤል በማድሪድ ቤት ደስተኛ እንዳልሆነ በግልፅ ይናገር ጀመር። ነገር ግን ከማድሪድ ጋር ፈፅሞ እስኪለያይ አራት ዓመት ወስዶበታል።

ቤል የዌልስ ማሊያን የለበሰ የምንም ጊዜም ምርጡ ተጫዋች የሚለውን ስምም ተጎናፅፏል።

አገሩ ዌልስ ፊታቸው ከጨለመ የሪያል ማድሪድ ደጋፊዎች መሸሸጊያው፤ ሲከፋው የሚፅናናባት መጠለያው ናት።

የዌልስ ደጋፊዎች ቤልን የሚነካባቸው ደመኛቸው ነው። ይህ የገባው ቤል በግላጭ ለአገሩ ያለውን ፍቅር እያሳየ መጣ።

በፈረንጆቹ 2020 ለአውሮፓ ዋንጫ ለማለፍ ከአዘርባጃን ጋር ከነበረው የማጣሪያ ጨዋታ በኋላ ቤል፤ “እኔ ቀለል ብሎ የምጫወተው ለአገሬ ብቻ ነው” ሲል በመናገሩ የስፔን መገናኛ ብዙኃን ጨርቃቸውን ጣሉ።

ዌልስ ሃንጋሪን አሸንፋ ለአውሮፓ ዋንጫ ስታልፍ ለጎልፍ ጥልቅ ፍቅር ያለው ቤል “ዌልስ፣ ጎልፍ፣ ማድሪድ” የሚል ፅሑፍ ይዞ ቅድሚያ ለማን እንደሚሰጥ ይፋ አደረገ።

ይህ የቤል እና የማድሪድ ፍፃሜን አጣደፈው።

ቤል ለዌልስ ብሔራዊ ቡድን ግብ በማስቆጠር የሚስተካከለው የለም

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ቤል ለዌልስ ብሔራዊ ቡድን ግብ በማስቆጠር የሚስተካከለው የለም

የአገሩ ጀግና

ዌልስ በጋሬዝ ቤል እየተመራች ከ1958 በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ለዓለም ዋንጫ መድረስ ችላለች።

ቤል በ33 ዓመቱ ጫማ ሰቅሏል። ብዙዎች ገና ጫማውን ለመስቀል አልበቃም ቢሉም እሱ ግን እግር ኳስ በቃኝ ብሏል።

እርግጥ ነው በተደጋጋሚ የሚያጋጥመው ጉዳት ቤል ከዚህም በላይ ተዓምር እንዳያሳየን ምክንያት ሆኗል።

ቢሆንም አገሩን ከማስጠራት አላገደውም።

ቤል ከኳታር ዓለም ዋንጫ በፊት ትልቁ ሕልሙ በዓለም ትልቁ የእግር ኳስ መድረክ መጫወት እንደሆነ ተናግሮ ነበር።

እነሆ እሱን አሳክቷል።

ዌልስ፤ ቤል ጫማ ሰቅሏል ብላ አታዝንም። ይልቁንስ ጀግናዋ አድርጋ ታከብረዋለች።