ጥሩነሽ ሁለት ልጆች ከወለደች በኋላ ወደ ሩጫ ልትመሰል መሆኑን ባለቤቷ ተናገረ

ጥሩነሽ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ጥሩነሽ በለንደኑ ኦሊምፒክ በ10ሺህ ሜትር የወርቅ ሜዳሊያ አሸናፊ ነበረች

የኦሊምፒክ እና የዓለም ሻምፒዮኗ ጥሩነሽ ዲባባ ከአራት ዓመት በኋላ ወደ አትሌቲክሱ መድረክ ልትመለስ መሆኗን ባለቤቷ ለቢቢሲ አረጋገጠ።

የአትሌት ጥሩነሽ ዲባባ ባለቤት ስለሺ ስህን ጥሩነሽ ከሳምንት በኋላ በአሜሪካ በሚደረገው የግማሽ ማራቶን እንደምትመለስ ለቢቢሲ ተናግሯል።

ጥሩነሽ ለመጨረሻ ጊዜ ውድድር ያደረገችው ከአራት ዓመታት በፊት በአውሮፓውያኑ 2018 መጨረሻ ላይ ነበር።

ባለፉት አራት ዓመታት ጥሩነሽ ሁለት ልጆችን መውለዷን የተናገረው ስለሺ፤ በአሁኑ ወቅት ጥር 07/2015 ዓ.ም. በሂዩስተን በሚደረገው የግማሽ ማራቶን ለመሳተፍ ልምምድ እያደረገች መሆኑን ባለቤቷ ገልጿል።

ጥሩነሽ ዲባባ እና እንደ እሷው ታዋቂ አትሌት የሆነው ባለቤቷ ስለሺ ስህን በአጠቃላይ ሦስት ልጆች አሏቸው።

ጥሩነሽ ዲባባ የሦስት ጊዜ የኦሊምፒክ፣ አምስት ጊዜ የዓለም ሻምፒዮን ስትሆን አንድ ጊዜ የዓለም ቻምፒዮንሺፕ የብር ሜዳሊያ አሸናፊ ስትሆን፣ ሦስት ጊዜ ደግሞ የኦሊምፒክ ጨዋታዎች የነሐስ አሸናፊ ናት።

ከጥሩነሽ ይፋዊ የፌስቡክ ገጽ እና ከዓለም አትሌቲክስ ድርጅት ይፋዊ ገጽ ላይ በተገኘው መረጃ መሠረት፣ አትሌቷ ለመጨረሻ ጊዜ በውድድር ላይ ተሳትፎ ያደረገችው ሰኞ ታኅሥሣ 22/2011 ዓ.ም. በማድሪድ ስፔን የ10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ ላይ ነበር።

ጥሩነሽ በዚህ ውድድር ሦስተኛ ደረጃን ይዛ ማጠናቀቋን እና የወደፊት ትኩረቷ ማራቶን እንደሚሆን ገልጻ ነበር።

አትሌት ጥሩነሽ በ2008 ቤጂንግ ኦሊምፒክ በ5 ሺህ እና በ10ሺህ ሜትር የወርቅ ሜዳሊያ ማሸነፏ በብዙዎች ዘንድ የሚታወስ አስደናቂ ድሏ ነው።

በሄልሲንኪ የዓለም ሻምፒዮና በ5ሺህ እና በ10ሺህ ሜትር እንዲሁ የወርቅ ሜዳሊያዎችን ያጠለቀች አንጋፋ አትሌት ነች።

ከሳምንት በኋላ በሚካሄደው የግማሽ ማራቶን ውድድር ጥሩነሽ ከአሜሪካዊቷ ኢሚሊ ሲሶን እና ከኢትዮጵያዊቷ ሕይወት ገ/ኪዳን ጠንካራ ፉክክር ይጠብቃታል።

ኢሚሊ ሲሶን በግማሽ ማራቶን የግል ምርጥ ሰዓቷ 67፡11 ሲሆን በቅርቡ በተካሄደው የቺካጎ ማራቶን ለአሜሪካ ሪኮርድ የሆነ ሰዓት በማስመዝገብ ሁለተኛ ሆና ጨርሳለች። 

ጥሩነሽ ዲባባ በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ታሪክ ስማቸው ጎልቶ ከሚጠቀሱ ጥቂት ሴት አልትሌቶች መካከል አንዷ ናት።

ጥሩነሽ ከባለቤቷ በተጨማሪ እጅጋየሁ፣ ገንዘቤ እና አና የተባሉት እህቶቿም በተለያየ አትሌቲክስ ዘርፍ እውቅና ያላቸው ሯጮች ናቸው።

በተጨማሪም በኢትዮጵያም ሆነ በአፍሪካ ታሪክ በኦሊምፒክ ውድድር ላይ የወርቅ ሜዳሊያ በማግኘት ታሪክ የሠራችው ደራርቱ ቱሉም የጥሩነሽ ዲባባ የቅርብ ቤተሰብ መሆኗ ይታወቃል።

ደራርቱ በተለያዩ ዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ ውድድሮች ላይ በማሸነፍ ዝናን ያተረፈች ሲሆን በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ናት።